Connect with us

በኦሮሚያ ክልል የፍርድ ቤቶች ትዕዛዝ  አለመከበሩ አሁንም አሳሳቢ ነው

በኦሮሚያ ክልል የፍርድ ቤቶች ትዕዛዝ አለመከበሩ አሁንም አሳሳቢ ነው
ፎቶግራፍ:- ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የኢሰመኮ ኮምሽነር

ዜና

በኦሮሚያ ክልል የፍርድ ቤቶች ትዕዛዝ  አለመከበሩ አሁንም አሳሳቢ ነው

በኦሮሚያ ክልል የፍርድ ቤቶች ትዕዛዝ  አለመከበሩ አሁንም አሳሳቢ ነው

~ ሙሃመድ ዴክሲሶ በአፋጣኝ ከእስር ሊለቀቅ ይገባል፣

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከየካቲት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በጅማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወረዳ 1 ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ የሚገኘውን ሙሃመድ ዴክሲሶ በተመለከተ የጅማ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት የካቲት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በዋስ እንዲለቀቅ ያሳለፈውን ውሳኔ በመተላለፍ ከእስር አለመለቀቁ እንዳሳሰበው ገልጾ፣ ሙሃመድ ዴክሲሶን ጨምሮ ሌሎችም በፍርድ ቤት የዋስትና መብት ተከብሮላቸው በእስር ላይ የሚገኙ እስረኞች በአፋጣኝ እንዲለቀቁ አሳስቧል።

የካቲት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. በጅማ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀው የተማሪዎች የምረቃ መርኃ ግብር የዩኒቨርሲቲው ተመራቂ በመሆኑ ታዳሚ የነበረው ሙሃመድ ዴክሲሶ፣ በዝግጅቱ ላይ በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን እና አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን በማስመልከት መፈክሮችን ማሰማቱን ተከትሎ በፌደራል ፖሊሶች ተይዞ በጅማ ከተማ ወረዳ 1 ፖሊስ ጣቢያ መታሰሩን  ሙሃመድ ዴክሲሶ ለኢሰመኮ አስረድቷል። 

ኢሰመኮ የካቲት 10 ቀን 2013 ዓ.ም. እስረኛውን በጎበኘበት ወቅት እስረኛው ለኢሰመኮ እንደገለጸው፤ በዩኒቨርስቲው የተማሪዎች ምረቃ ሥነ ሥርዓት በዓል ላይ የዘፈን ፕሮግራም ሲጀመር በመድረክ ላይ ሆኖ ከሚዘፍኑ ሌሎች ተመራቂዎች ጋር እየጨፈረ እንደነበረና ከዘፋኙ የድምጽ ማጉያ ተቀብሎ ‘ጀዋር መሐመድ ይፈታ’፣ ‘ፍትሕ ለሀጫሉ ሁንዴሳ’ በማለት ድምጹን ማሰማቱን፣ የምርቃት ፕሮግራሙ እንዳለቀ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ፖሊሶች በግቢው ውስጥ ወዳለው ካምፕ እንደወሰዱትና ፖሊሶቹ በጥፊ እንደመቱት፣ ከጥቂት ቆይታ በኃላ ከዩኒቨርስቲው ግቢ ውጪ ወስደውት በዱላ ሁለቱን እግሮቹን እንደደበደቡት፣ በጎኑ አካባቢም እንደመቱት አስረድቷል።

ሙሃመድ ዴክሲሶ አክሎም ለኢሰመኮ እንደገለጸው ‹‹በጅማ ዩኒቨርሲቲ የነበሩ ፖሊሶች ለአንድ ሰዓት ያክል ካቆዩኝና ከደበደቡኝ በኃላ ወደ ጅማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወሰዱኝ፣ በፖሊስ ጣቢያው ከደረስኩ በኋላ ግን የተፈጸመብኝ ድብደባ የለም፣ ፖሊሶች የተጠረጠርኩበትን ወንጀል ካስረዱኝ በኃላ የካቲት 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ጅማ ከተማ ፍርድ ቤት ወስደውኛል›› ብሏል። 

ኢሰመኮ እስረኛውን በጎበኘበት የካቲት 10 ቀን 2013 ዓ. ም. በእግሮቹ ላይ መጠነኛ እብጠት የሚታይ መሆኑንና የሚያነክስ መሆኑን ተመልክቷል። ይህንኑ መሰረት በማድረግ አስረኛው ሕክምና እንዲያገኝ ለፖሊስ ጣቢያው ምክረ ሃሳብ ተሰጥቶ መግባባት ላይ ተደርሶ የነበረ ቢሆንም እስከ የካቲት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ሕክምና ያላገኘ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል።

የጅማ ወረዳ ፍርድ ቤት የካቲት 16 ቀን 2013 ዓ.ም.  ሙሃመድ ዴክሲሶ በብር 2000 (ሁለት ሺሕ ብር) የገንዘብ ዋስትና ከእስር እንዲለቀቅ የወሰነ እና እስረኛውም አስፈላጊውን የዋስትና መስፈርት ያሟላ ቢሆንም፣ እስከ የካቲት18 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በእስር ላይ የሚገኝ መሆኑን ኢሰመኮ አረጋግጧል። 

ሙሃመድ ዴክሲሶ በተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የፈጸመው ተግባር ከነገሩ ሁኔታ አንጻር ምናልባት ሊነቀፍ ወይም ሊያስወቅስ ከሚችል በስተቀር፣ ከመነሻውም ለወንጀል ክስና አስር ምክንያት ሊሆን አይገባም ነበር። ፖሊስ ወይም ዐቃቤ ሕግ በበቂ ምክንያት ሊያስከስስ የሚገባ ነገር አለ ብለው ካመኑም፣ ማስረጃዎችን አሰባስቦ ክስ ከማቅረብ ዉጪ ተጠርጣሪውን ከፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት ወይም በምርመራ ሰበብ ለማሰር የሚያበቃ ምክንያት አልነበረም። 

ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲለቀቅ ከወሰነና የዋስትናው መስፈርት ከተሟላ በኋላ ወዲያወኑ ከእስር ሊለቀቅ ሲገባ፤ ይህ ሪፖርት እስከተዘጋጀበት ወቅት ድረስ በእስር ላይ የነበረ መሆኑ የተደራረበ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ነው። 

ስለሆነም ኢሰመኮ እስረኛው ሙሃመድ ዴክሲሶ በአፋጣኝ ከእስር ሊለቀቅ የሚገባ መሆኑን እያሳሰበ፤ እስረኛው ወደ ጅማ ፖሊስ መምሪያ ከመወሰዱ አስቀድሞ በፖሊሶች ተፈጽሞብኛል ያለውን ድብደባ በተመለከተ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ኢሰመኮ ያሳስባል። በተመሳሳይ መልኩ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል እስር ቤቶች የዋስትና መስፈርቶችን  አሟልተው አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ እስረኞች ከእስር እንዲለቀቁ ኮሚሽኑ በድጋሚ  ያሳስባል። 

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ጉዳዩን አስመልክቶ “በኦሮሚያ ክልል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የፍርድ ቤቶች ትዕዛዝ አለመከበር እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ አፋጣኝ ትኩረትና እልባት ይሻል” ብለዋል።

ፎቶግራፍ:- ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የኢሰመኮ ኮምሽነር

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top