Connect with us

ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማሳካት እንችል ይሆን?

ምርጫ ቦርድ ለኦነግ የአመራር ምርጫ ዕውቅና ነፈገ
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማሳካት እንችል ይሆን?

ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማሳካት እንችል ይሆን?

(ፍሬው አበበ)

ተራዝሞ የቆየው 6ኛው ዙር ብሔራዊ ምርጫ ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለታል፡፡ በምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ፓርቲዎች የምርጫ መወዳደሪያ ምልክታቸውን መርጠው ተረክበዋል፡፡ የያዝነው የካቲት ወርም ለምርጫው ወሳኝ ክንውኖች የሚካሄዱበት ነው፡፡ 

ከየካቲት 8 እስከ 21/2013 ዓ.ም የዕጩዎች ምዝገባ የሚከናወንበት ሲሆን ከየካቲት 8 እስከ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም የምረጡኝ ቅስቀሳ ወይንም የምርጫ ዘመቻ የሚካሄድበት ጊዜ ይሆናል፡፡

ብዙዎች ከምርጫ ዝግጅቱ በላይ መጪው ምርጫ እንደሚነገርለት ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ በህዝብ ዘንድ ተአማኒ ሆኖ ይጠናቀቅ ይሆን ወይ የሚለው ያሳስባቸዋል፡፡ በእርግጥም የምርጫ ጣጣ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሀገራትም የግጭትና ብጥብጥ መነሻ በመሆኑ ቢሰጉ አይፈረድባቸውም፡፡

ሩቅ ሳንሄድ በሀገራችን የ1997 ቱን ምርጫ ተከትሎ የተፈጠረው ቀውስ ለብዙዎች ሞት፣ ጉዳት፣እስር፣ መሰደድ እና መፈናቀል መንስኤ መሆኑን አንረሳውም፡፡

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ዲፓርትመንት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ፋንታሁን አየለ ስለመጪው ምርጫ ከማውራት አስቀድሞ ያለፉት ምርጫዎች ሒደት ምን ይመስል ነበር የሚለውን መገምገምና ከእሱም መማር ይገባል ይላሉ፡፡ ባለፉት ምርጫዎች ትልቁ ችግር የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አለመሆን ነበር ሲሉ ያስታውሳሉ፡፡

 የቦርዱ ገለልተኛ አለመሆን መንግስት ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ከወሬ ባለፈ በተግባር ያሳየውን ቁርጠኝነት ማጓደሉን ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ባለፉት አምስት ምርጫዎች ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊ በሕዝብ ዘንድ ተአማኒ ሆነው መጠናቀቅ አልቻሉም፡፡ አንዳንዶቹም የግጭትና ብጥብጥ መንስኤ ሆነውም ታይተዋል፡፡

በቀጣዩ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ከማንም በላይ የመንግስት ቁርጠኝነት እጅግ ወሳኝ ያሉት ዶ/ር ፋንታሁን መንግስት ታሪክ ለመስራት ዝግጁ ከሆነ በእርግጥም ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ሆኖ በሰላም ሊጠናቀቅ የሚችልበት ዕድሉ ሰፊ ነው ይላሉ፡፡

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮምኒኬሽን የሶስተኛ ዲግሪ  ተማሪ እና የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆነው ዕጩ ዶክተር አየለ አዲስ መጪው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ገዥው ፓርቲ ምህዳሩን ማስፋት እንደሚጠበቅበት ጠቅሰዋል፡፡ እንደከዚህ ቀደሙ ገዥው ፓርቲ የመንግስት ሀብት (ሪሶርስ) እየተጠቀመ ለምርጫ ቅስቀሳ የሚያውልበት አካሄድ መታረም እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ 

በሚዲያ አጠቃቀም ረገድም ገዥው ፓርቲ በሞኖፖል በመያዝ የሚስተናገድበት ስራ ቀርቶ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ፍትሐዊ በሆነ ስሌት ተጠቃሚ የሚሆኑበትና ለአባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው መልዕክቶቻቸውን የሚያደርሱበት ሁኔታ በተግባር መመቻቸት እንደሚገባው ያስረዳሉ።

የዕጩ ዶክተር አየለ ንግግር፤ በ1997 ምርጫ ጋር ተያይዞ የተከሰተ ነገር እንዳስታውስ ረድቶኛል፡፡ አንድ ዕለት በምርጫ ቦርድ ቅጥር ግቢ በምርጫ ጉዳይ ንግግር እየተካሄደ ነበር፡፡ 

እናም የገዥው ፓርቲ በመወከል አቶ በረከት ስምኦን የነበሩ ሲሆን በቅንጅት በኩል ደግሞ እነፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ነበሩ፡፡ በኃላም በንግግሩ ወቅት አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር “ለምሳሌ አቶ በረከት እዚህ ስብሰባ እንኳን የመጣው የመንግስት መኪና ይዞ ነው፣ ይሉኝታ እንኳዋ አያውቁም” ብሎ ይተቻል፡፡  አቶ በረከት ምን አደረጉ? ከሰአት በኃላ በነበረው ስብሰባ  መኪና ቀይረው መጡ፡፡ የመኪናው የሰሌዳ ቁጥሩም መነሻው ኮድ 2 ነበር፡፡ እንግዲህ ነገሩ ጊዜያዊ ሽወዳ በመሆኑ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡  ዋናው ነገር የመንግስት ንብረት ለምርጫ ስራ አለመጠቀም እንጂ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 4 ወይንም ኮድ 2 መሆኑ አልነበረም፡፡

ዶ/ር ፋንታሁን መጪው ምርጫ ነጻና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ተቀናቃኝ ፓርቲዎችና ሕዝቡ ከመንግስት ባልተናነሰ ሚና እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ 

ተገቢ ካልሆኑ ውንጀላዎች መራቅ አለባቸው፡፡ ችግሮች ቢኖሩም እንኳን በመነጋገር ለመፍታት ረጅም ርቀት መጓዝ ከተቀናቃኞቹ የሚጠበቅ ነው፡፡ ህዝቡም ራሱን ከተለያዩ ውዥንብሮች በማራቅ ለምርጫው ሒደት አዎንታዊ እገዛ ሊደርግ ይገባል፡፡ በተለይ በማህበራዊ ሚደያ የሚለቀቁ ሐሰተኛ ወሬዎችና ውዥንብሮች ጆሮ ባለመስጠት እኩይ ተግባራትን ሊያከሽፍ ይገባል ብለዋል፡፡

ዕጩ ዶ/ር አየለ አዲስ መገናኛ ብዙሀንም ከውግንና ነጻ ሆነው ለምርጫው ዴሞክራሲያዊነት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ፤ በተለይ በማህበራዊ ድረገጾች የሚለቀቁ ሐሰተኛ መረጃዎች በማጋለጥና ትክክለኛውን በማቅረብ ጋዜጠኞች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርዋ ዶ/ር ጌጤ በላይነህ መጪው ምርጫ ብሔርን መሰረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ድርጅቶች በብዛት የሚሳተፉበት እንደመሆኑ ባለፉት ሶስት ዓመታት የታዩ ብሔር ተኮር ግጭቶች ምርጫውን ታከው ዳግም እንዳያገረሹ ሁሉም ወገን በኃላፊነት ስሜት ሊንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል፡፡

ሰሞኑን ገዥውን ፓርቲ የሚደግፉ ሰልፎች በአንዳንድ ክልሎች ሲታዩ በተቃራኒው በአዲስአበባ ከተማ በአንድ ተቀናቃኝ ፓርቲ ለተቃውሞ የቀረበ ሰልፍ እንዳይካሄድ መከልከሉ አሁንም የፖለቲካ ምህዳሩ ለሁሉም ወገን እኩል ክፍት አለመሆኑን ስለሚጠቁም በፍጥነት ሊታረም የሚገባና መደገም የሌለበት ስህተት ነው ይላሉ፡፡

ከምንም በላይ ደግሞ መንግስትን በሚደግፉ ሰልፎች ላይ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን በአደባባይ ማውገዝና በጠላትነት የመፈረጅ ምልክቶች እጅግ አሳፋሪና  ምርጫው ነጻና ዴሞክራሲያዊ እንዳይሆን የራሳቸውን አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳርፉ በመሆናቸው የብልጽግና ፓርቲ ሰዎች ጭምር በጥብቅ ሊያወግዙት የሚገባ ድርጊት ነው ሲሉ ዶ/ር ጌጤ አስተየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ጋዜጠኛና አክቲቪስት አንዱዓለም መብርሃቱ መጪው ምርጫ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል የሚል ተስፋው ገና ከአሁኑ መሟጠጡን ያስረዳል፡፡ 

በባለፉት ጊዜያት በተለይ በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል ክልሎች አንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በተከታታይ መፈጸሙ ብቻ ሳይሆን ወንጀሉ በነጻና ገለልተኛ ወገን ተጣርቶ በአጥፊነት የሚጠረጠሩ እስከበላይ አመራር የሚገኙ ሰዎች ለሕግ ባልቀረቡበት ሁኔታ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት በምርጫ እንዳይወዳደሩ ታቅዶ በታሰሩበት ሁኔታ፣ በሕግ ማስከበር ስም በተካሄደ ጦርነት በትግራይ ንጹሀን ወገኖች ለሞት፣ ለረሀብና ለችግር በተዳረጉበት ሁኔታ እውነተኛ የሆነ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንደምን ማሰብ ይቻለናል በማለት ይጠይቃል፡፡

በሌላ በኩል ጠ/ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከወራት በፊት ያደረጉትን ተከታዩ ጥሪ በተለይ በገዥው ብልጽግና ፓርቲ እና በተቀናቃኞች በኩል መተግበር ከቻለ ለሰላማዊ ምርጫ መሳካት ተስፋ ሰጪ ይመስላል የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡

“….መጪውን ምርጫ ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና ተአማኒ ለማድረግ በጋራ በቂ ዝግጅት እያደረግን እንቆያለን። አንዱ ዋናው ዓላማችን መጪውን ምርጫ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵውያን የሚመጥን ማድረግ መሆኑ ሊሠመረበት ይገባል። በዚህ ረገድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪክ ማኅበራት፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከታዋቂ ሰዎች፣ ከሚዲያ ልሂቃን፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከጎሳ መሪዎችና ከሌሎች ከሚመለከታቸው ሁሉ ጋር፤ የኮሮና መከላከል ርምጃችንን በማያውክ መልኩ በመወያየትና በመመካከር እንሠራለን። ይኽን የምናደርገው እንዲሁ አደረግን ለማለትና ለይስሙላ መሆን የለበትም። 

ሁላችንም በታሪክ ፊት ድምጻችን ጎላ ብሎ የምንናገረው በአንደበታችን ሳይሆን በተግባራችን ነው። ስለሆነም እያንዳንዳችን ለተግባራዊነቱ ከወዲሁ ቆርጠን እንድንነሳ ጥሪዬን አቀርባለሁ።…”(ጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ)

አዎ!.. ይኸ የጠቅላዩ ጥሪ መሬት ወርዶ ይተገበር ዘንድ የሁሉንም ወገኖች ቀናነትና አዎንታዊ ተሳትፎ የግድ ይላል፡፡ (ማስታወሻ፡- ይህ መጣጥፍ በኢንተር ኒውስ ድጋፍ የተዘጋጀ ነው፡፡)

 

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top