Connect with us

ወቀሳው በልክ ይሁን!!ባይሆን እንዋቀስ!

ወቀሳው በልክ ይሁን!!ባይሆን እንዋቀስ!
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ወቀሳው በልክ ይሁን!!ባይሆን እንዋቀስ!

ወቀሳው በልክ ይሁን!!ባይሆን እንዋቀስ!

.~ ለኦርቶዶክሳዊ የሚዲያ ባለሙያዎች እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች

~    እኛም እኛ ላይ እንስራ ቤተ ክርስቲያንም ታግዘን!!

(መስከረም ጌታቸው)

በሰሞኑን የማእተብ ‘’አዉልቂ ተባልኩ’’ መነሻነት የተፈጠረው ጩኸትና ግርግር በእውነት ግሩም ነው፡፡ ዝም ልበል ቢሉም ዝም አያሰኝም!! የአንዳንዶቹ በቅንነት ለቤተ ክርስቲያን ክብር በማሰብ ነገር ግን የሚዲያ ኤድቶሪያል ፖሊሲ ጉዳይን ካለመረዳት ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ እያወቁ ነገር ግን የዩቱዩብና የፌስ ቡክ ገጻቸው ተመልካች ያገኝ ዘንድ በነገሩ ላይ እንቅልፍ አጥተው ሰነበቱ፡፡

በመጀመሪያ ከ10 አመት በላይ በሙያው እንደመቆየቴ የማውቀውን ላካፍል፡፡ ሁሉም በሚባል ደረጃ ሚዲያዎች የራሳቸው ኤዲቶሪያል ፖሊሲና የአለባበስ መመሪያ አላቸው ፡፡ እነዛ ፖሊሲና መመሪያዎች ማን ላይ ይጠነክራሉ? ማን ስልጣን ሲይዝስ ይከብዳሉ፣ ይቀላሉ ሌላ ጥያቄ ኹኖ ሁሉም ባለሙያ ሲገባ ግን ተቋሙ ያሳውቃል ወይም ባለሙያው ይጠይቃል/መጠየቅ አለበት/፡፡ ስለዚህ በቆይታው ተስማምቶና ፈቅዶ የሚያደርገው እንጅ ድንገተኛ ውሳኔ አይደለም/ከሆነም በህግ የሚያስጠይቅ ነው/፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ቴሌቪዠን ፖሊሲም ሆነ አለባበስ መመሪያ የሃይማኖት ምልክቶችን ይከለክላል፡፡ 

በቅርብ አለቆች በራስ መተማመን ችግር ስልጣንን ከመውደድ የተነሳ ማእተባችሁ እንዳይታይ ስንባል ስንደብቅ የነበርንበት ጊዜ ነበር፡፡  በኋላ የማእተብን ዋጋ መረዳት ሲመጣ ግን ለምን ብለን ጠይቀናል፡፡ ምክንያቱም ሙስሊም ጓደኞቻችን ሂጃብ ሲያደርጉ አይከለከሉም ነበርና፡፡ 

እርግጥ ነው፤ አለቆች ከሌላው ቤተ እምነቶች ይልቅ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ላይ ይበረታሉ፡፡ ለምን ቢሉ ጠያቂ አካል ስሌለለ…ስለሆነም ‘’አናወልቅም ክህደት ነው’’ ባልን ጊዜ ተቀብለውን ማእተባችንን እየታየ ሰርተናል፡፡ በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ ደሞ ይሄ ችግር ሲሆን አላየሁም ፡፡ 

በአጭሩ ለመግለጽ ኢቢኤስም ኾነ ሌላ ሚዲያ ያለውን ፖሊሲና መመሪያ አሳውቆ እስከቀጠረ ድረስ ጥፋቱ የእኛ እንጅ የጣቢያው ነው የሚል አቋም የለኝም፡፡ ይህ ግን ጣቢያው በግልጽ አሳውቆ ከቀጠረ ብቻ ነው፡፡

ዋናው ጉዳዬ ግን እኛ ኦርቶዶክሳዊያን የሚዲያ ባለሙያዎች እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በእርግጥ ከሚታየው ማእተብ ውጭ  ቤተ ክርስተያንን አሳልፈን አልሰጠንም ወይ? ቤተ ክርስቲያን አፍ አውጥታ ብትጠይቀንስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ አለን ወይ ?  ልጆቼ ታረዱ፣ ተሰደዱ ብላ ስትጮኽ በየኤድቶሪያል ስብሰባው ዜናው አይሰራም ሲባል አብረን ወይም ከሌላ እምንት ተከታዮች ቀድመን የድጋፍ  እጅ የምናወጣ እኛ አይደለንም ?  

ብሔራችን ከሃይማኖት በልጦብን ብሶቷን መናገር አክራሪ ያሰብለኛል ብለን ጆሯችንን የምንይዘው እኛ አይደለንም? ከሃይማኖት ስልጣን በልጦብን አያዳሉም ለመባል ኦርቶዶክስን የምንጨቁናት ራሳችን አይደለንም? በተከበሩ በዓላቶቿ ሙዚቃ መራጭ እና ጨፋሪ እኛ አይደለንም ?እቅድ አስገቡ ስንባል እሷን የማይመጥኑ ፕሮግራሞችን በእሷው እለት ምንሰራው እኛ አይደለንም ? ከአለባበስ ጀምሮ ከአስተምህሮ በተጻራሪ መንገድ ቆመን ተመልካች ‘’ደስ’’ ይለው ዘንድ ሰውነታችንን አጋልጠን ስክሪን ላይ ተለጥፈን ምንውል እኛ አይደለንም ? 

የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችስ በእውነት የቱን ስክሪፕት ከቅድስት ቤተ ክረስተን አስተምህሮ ጋር ይጋጫል ብላችሁ መልሳችሁ  ይሆን ? የቱ ድርጊትስ አላደርግም ተቃውማችሁ ይሆን? ራሳችንን እንጠይቅ፡፡

 ቤተ ክርስቲያንን ሊቀብሯት እረፍት ሲያጡ አውቀንም ኾነ ሳናውቅ ሚዲያን ያህል መሳሪያ ይዘን የአጥፊዎች ተባባሪ ሁነናልና ዛሬ ማእተቤ ብሎ የመናገር ድፍረት አለን ብዬ አላስብም፡፡ ወይም ይህን ሁሉ ተገደን እያደረግን ከሆነ በአፋችን ከምንጮኽለት ሃይማኖታችን በላይ የበለጠብን አለ ማለት ነው፡፡ 

እሱን ፈጣሪ ይወቀው!! ነገር ግን ሃይማኖት ፖለቲካ አይደለም ሕዝብን ለመያዝ ሲባል የራሳችንን ድክመት አንድ አካል ላይ ለጥፈን ከደሙ ንጹህ ነኝ ማለት አይቻልም!! ባይሆን ስላለፈው ንስሐ ግብተን ለሚመጣው ለእውነት እንኑር!

ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም በየሚዲያው ያሉ ባለሙያዎችን መሰብሰብና ማስተማር አለባት፡፡ ኦርቶዶክሳዊነት በአለባበስ በአነጋገርም በአጠቃላይ በሚታይ ሕይወቱም ነውና  ወንጌልን ሚሰብከው፡፡ 

ስለሆነም ሃይማኖታችንን በእምነት ተቀብለን ብቻ ሳይሆን አውቀነውም እንኖር ዘንድ ባለቤትነቱን ወስዳ መስመር ማስያዝ፣ ትክክል የሆነ እና ያልሆነውን እንዲለዩ በሃይማኖታዊ አስተምህሮ እንዲታነጹ ማድረግ አለባት፡፡ 

ከዳር ኾኖ እሳት ማራገብ ሳይሆን እኛም እንደባለሙያ የራሳችን ሕይወት ላይ እንስራ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያንም በያለንበት ሚዲያ እና በሌሎችም ሙያዎች አምባሳደር እንሁን!!! እሷ ለእኛ ስታስፈልገን የምንጠጋት ብቻ ሳትሆን እሷም በየሰከንዱ እንደምትፈልገን አንርሳ!! ታዲያ ይህ ኹሉ ግን በቤተ ክርስቲያን ላይ በማወቅም ኾነ ባለማወቅ ዘመቱባትን ሚዲያዎች ንጹሕነት አያሳይም!! የልብ ልብ የሰጠናቸው እኛ ነንና ከውስጣችን እንጀምር ለማለት እንጅ!!

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top