ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞችን ተቀብላ የምታስተናግድ ግንባር ቀደም ሀገር መሆኗ ተገለጸ
ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞችን ተቀብላ የምታስተናግድ ግንባር ቀደም ሀገር መሆኗን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለጸ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው በትግራይ ክልል የተካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻ መንግሥት ተገዶ የገባበት እርምጃ እንደነበር የህወሃት ቡድን ከሁለት ዓመት በላይ ትንኮሳዎችን ሲፈጽም መቆየቱን፣ መንግሥት በከፍተኛ ትግስት ሲያልፍ መቆየቱን፣ በመጨረሻ ግን ቡድኑ በሀገር መከላከያ የሰሜን እዝ ሰራዊት ላይ ጥቃት ፈጽሞ በአሰቃቂ ሁኔታ ባልታጠቁና በእንቅልፍ ላይ በነበሩ ሰራዊት ላይ አሳፋሪ ጭፍጨፋ መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡
የሀገር ክህዴት ወንጀል ፈጽሞ ቀይ መስመር ሲተላለፍም መንግሥት የሀገር ህልውና እና ሉዓላዊነት አደጋ ላይ በመውደቁ ተገዶ የገባበት ህግ የማስከበር እርምጃ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የህግ የበላይነት ለማስከበር የተደረገው ዘመቻ በአጭር ጊዜ እንዲገባደድ ማድረግ መቻሉንም ነው የገለጹት፡፡
በትግራይ ክልል የሚደረግ የሰብአዊ እርዳታ የማድረስ ሥራ የህወሃት ቡድን በመሰረተ ልማቶች ላይ ባደረሰው ጉዳት ምክንያት ፈታኝ እንደነበር ጠቅሰው በክልሉ የስልክ፣ የመብራት፣ የመንገድና ድልድዮች፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን፤ እንዲሁም የጤና ተቋማት ሳይቀር የህወሃት ቡድን በማፈራረሱ በክልሉ ያሉ ዜጎችን ለከፍተኛ ችግር ዳርጓል ነው ያሉት፡፡
በመሰረተ ልማቶች ላይ የማፈራረስ ተግባር ሲፈፅሙ በሲሲቲቭ ካሜራ ጭምር የተያዙ መረጃዎች መኖራቸውንም ገልፀዋል።
በትግራይ ክልል እየተደረገ ያለው የሰብአዊ እርዳታ የማድረስ ርብርብ፣ በክልሉ የህወሃት ቡድን ያፈራረሳቸውን የመሰረተ ልማቶች መልሶ ግንባታና ወደ አገልግሎት ማስገባት፣ የመልሶ ማቋቋም፣ በክልሉ ባሉ የመጠሊያ ጣቢያዎች ያሉ የኤርትራ ስደተኞች ሁኔታ፤ እንዲሁም በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት አድርገዋል፡፡
እንደ አቶ ደመቀ ማብራሪያ የህወሃት ቡድን በክልሉ የነበሩ አስራ ሶስት ሺ ያህል ፍርደኞችን ከእስር ቤት እንደለቀቃቸውና እነሱም በክልሉ በወንጀል ተግባር ላይ መሰማራታቸውን፣ የክልሉ የፖሊስ ኃይልንም በውጊያ እንዲሳተፉ ስለተደረገ በራሱ ሌላ ችግር የፈጠረ እንደነበር፣ በአሁን ጊዜ እንደ መቀሌ ከተማ ባሉ ቦታዎች ተሃድሶ የወሰዱ ፖሊሶችን ወደ ሥራ የመመለስ እርምጃ መጀመሩ ተስፋሰጪ መሆኑንም ተገልጻዋል፡፡
የኤርትራ ስደተኘች ከመጠሊያ ካምፖቹ መካከል በጣም ለድንበር ቅርብ የሆኑ መኖራቸውንና በተፈጠረው ሁኔታ ከመጠሊያ የወጡ መኖራቸውን ጠቁመው፣ አሁን ወደ መጠለያው ተመልሰው ድጋፍ እንዲደርሳቸው እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ለድንበር ቅርብ የሆኑ መጠሊያዎች ጉዳይ መፍትሄ እንደሚያስፈልገው በውይይታቸው አንስተዋል።
የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲ በበኩላቸው ለተደረገቻለው ገለፃ አመስግነው፣በትግራይ ክልል ጉብኝት አድርገው ሁለት የስደተኞች መጠሊያ ጣቢያዎችን መጎብኘታቸውን፣ ስልክ ወደ አገልግሎት መመለስ ያልተዳረሰባቸው ቦታዎች ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው፣ የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦትን የበለጠ ለማስፋት በክልሉ የሚደረግ እንቅሥቃሴና ክሊራንስ አሰጣጥ አፋጣኝ መልስ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
ኮሚሽነሩ አያይዘው ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰደተኞችን ተቀብላ የሚታስተናግድ ሀገር በመሆኗ ከድርጅታቸው ጋር ተባብራ በመሥራት ግንባር ቀደም ሀገር ናት ብለዋል፡፡ ለድንበር የቀረቡ የስደተኞች መጠሊያ ጣቢያዎች ጉዳይ መፍትሄ ለመስጠት ድርጅታቸው እንደሚሰራም ቃል ገብተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ከውይይታቸው በኋላ በጋራ መግለጫ መስጠታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡(አብመድ)