Connect with us

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ህግና ስርዓትን ያልተከተለ የፋይናንስ ስርዓቱ ተገመገመ

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ህግና ስርዓትን ያልተከተለ የፋይናንስ ስርዓቱ ተገመገመ

ህግና ስርዓት

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ህግና ስርዓትን ያልተከተለ የፋይናንስ ስርዓቱ ተገመገመ

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ህግና ስርዓትን ያልተከተለ የፋይናንስ ስርዓቱ ተገመገመ

በቂ የበጀት ዝግጅት ጥናት ያለማድረግ እና የህግ ማእቀፍና መመሪያን ያልተከተሉ አሠራሮችን መተግበር ለህገወጥ የበጀት አጠቃቀምና ለብልሹ የፋይናንስ ሥርዓት እንደሚዳርጉ ተገለፀ ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የዋቸሞ ዩኒቨርስቲን የ2011 በጀት ዓመት የሂሳብ ኦዲት ግኝት ላይ ታህሳስ 23 ቀን 2013 ዓ.ም ይፋዊ ስብሰባ አካሄደ፡፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደውና በበጀት ዓመቱ በዩኒቨርስቲው የታዩ የበጀት አጠቃቀምና የፋይናንስ አሠራር ክፍተቶች ላይ ትኩረት ባደረገው የግምገማ መድረክ የዩኒቨርሲቲውን አመራሮች ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

የተካሄደው የሂሳብ ኦዲት ግኝት ግምገማ በቋሚ ኮሚቴው ለዩኒቨርሲቲው አመራሮች የቀረቡ ዋነኛ ጥያቄዎችን መሠረት ደረገ ሲሆን ለቀረቡት ጥያቄዎች በዩኒቨርሲቲው አመራሮች ምላሾች ተሰጥተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው በታዩ ህገ ወጥ የበጀት አጠቃቀምና ደንብና መመሪያን ባልተከተሉ የሂሳብ አያያዝ አሠራሮች ሳቢያ የኦዲት አስተያየት መስጠት ያለመቻሉን የኦዲት ግኝት ሪፖርቱ ማመላከቱን የጠቆመው ቋሚ ኮሚቴው ይህንኑ መሠረት ያደረጉ ዋና ዋና የኦዲት ግኝቶችን ባቀረባቸው ጥያቄዎች ውስጥ አንስቷል፡፡

የዩኒቨርስቲውን ዋና ግቢ ጨምሮ በስሩ በሚገኙ በህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና በዱራሜ ካምፓስ በድምሩ ብር ብር 23,561,465.48 ባልተፈቀደ የሂሳብ መደብ የተመዘገበና ከበጀት በላይ የወጣ ገንዘብ መገኘቱና ብር 17,166,465.69 የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ የተመዘገበ መሆኑ፣ የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ ሳይቀርብ የህክምና መሳሪያዎችን ጨምሮ ለተለያዩ እቃዎችና ለመድሀኒት ግዥ እንዲሁም ለአገልግሎት የተከፈለ ብር 1,510,466.67 መገኘቱ፣ በ2010 በጀት ዓመት ለተሰጠ አገልግሎት የተከፈለ ብር 1,455,823.61 በ2010 በጀት ዓመት ለተሰጠ አገልግሎት ከ2011 በጀት ዓመት ተወራርዶ መገኘቱ፣ ከመንግስት ደንብና መመሪያ ውጪ ብር 1,619,684.30 የውሎ አበል መከፈሉና ያለክፍያ ተመን ብር 9,554,645.35 በጊዜያዊነት ለተቀጠሩ ባለሙያዎች ክፍያ መፈፀሙ፣ ከመመሪያ ውጪ ብር 2,735,945.50 የአኑላይዜሽን፣የሀላፊነትና የቤት አበል መከፈሉ፣ መመሪያን መሰረት ሳያደርግና የተሟሉ ማስረጃዎች ሳይቀርቡ የብር 2,002,920.00 የትርፍ ሰዓት ክፍያ ለሀኪሞች መከፈሉና ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መመሪያ ውጪ ብር 1,267,836.36 ለመምህራን ጥቅማጥቅም ተብሎ ወጪ መሆኑ፣ በመንግስት የተፈቀደ የክፍያ መመሪያና ተመን ሳይኖር ከውስጥ ገቢ በጀት ብር 3,499,156.95 ተከፍሎ መገኘቱ እና በአጠቃላይ ብር 20,630,188.36 ከደንብና መመሪያ ውጪ ክፍያ መፈፀሙ በበጀት ዓመቱ በዩኒቨርሲቲው የበጀት አጠቃቀምና የፋይናንስ አሠራር ላይ የታዩ ክፍተቶች መሆናቸው ቋሚ ኮሚቴው ባቀረባቸው ጥያቄዎች ውስጥ ተነስተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሳይወስንና በገንዘብ ሚኒስቴር ሳይፈቀድ ከተለያዩ የውስጥ ገቢ ምንጮች ከተሰባሰበ ገቢ ውስጥ ብር 14,256,612.83 ወጪ መደረጉ፣ የውል ቁጥሮችን የያዙ መረጃዎች ያልቀረቡባቸው ለውሃ፣ ለመብራትና ለስልክ የተከፈለና ክፍያው ለዩኒቨርሲቲው አገልግሎት ስለመዋሉ ማረጋገጥ ያልተቻለ የብር 499,512.56 ክፍያ መፈፀሙ፣ ቋት ያልተከፈተላቸው በመሆናቸው በተከፋይ ሂሳብ የተያዙበት ጊዜ እንዲሁም ከማን እንደሚሰበሰብና ለማን እንደሚከፈል በቀላሉ ማወቅ ያልተቻሉ የብር  204,705,465.11 ተሰብሳቢና የብር  143,331,260.59 ተከፋይ ሂሳቦች መገኘታቸው እና ለየፕሮግራሞቹ ከተፈቀደው በጀት  ብር 70,506,361.18 ስራ ላይ ያልዋለ በጀት መገኘቱ በሌላ በኩል ደግሞ ብር 8,392,181.65 ከተደለደለው በጀት በላይ ወጪ ሆኖ መገኘቱ በኦዲት ሪፖርቱ የተመለከቱ በመሆናቸው ማብራሪያ እንዲሰጥባቸው በቋሚ ኮሚቴው ተጠይቋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የታዩትን የንብረት አያያዝና አስተዳደርን በተመለከተ በታዩት ክፍተቶች ዙሪያም በቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ ቀርቧል፡፡ በተለይም ዓመታዊ የንብረት ቆጠራ በወቅቱ ያለመጠናቀቁ፣ ቋሚ ንብረቶች መለያ ቁጥሮች ያልተሰጣቸው መሆኑ እና ቋሚና አላቂ እቃዎች ለረጅም ጊዜ በመጋዘን ውስጥ ተከማችተው መገኘታቸውን በተመለከተም የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ምላሽ እንዲሰጡ ተጠይቋል፡፡ ከዚህም ሌላ በ2010 በጀት ዓመት በኦዲት ለተገኘው ብር 54,558,490.32 በኦዲት አስተያየት መሠረት እርምጃ ያለመወሰዱን በ2011 በጀት ዓመት የተካሄደው ኦዲት የሚያሳይ በመሆኑ እርምጃው ለምን እንዳልተወሰደ ተጠይቋል፡፡

በቋሚ ኮሚቴው ለቀረቡት ዋና ዋና ጥያቄዎችና እያንዳንዳቸውን የኦዲት ግኝቶች አስመልክተው ዝርዝርና ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ሀብታሙ አበበ ግኝቶቹን መሠረት ያደረጉ የእርምት እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችል ግብረ ሀይል በማቋቋምና በቋሚ የመኔጅመንት ስብሰባዎች ላይ የእርምጃዎቹን ሂደት በመገምገም ወደ ፊት በ2012 የኦዲት ሪፖርት ሊረጋገጡ የሚችሉ ጠንካራ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንና በዚህም ጥቂት የማይባሉ ክፍተቶችን ማስተካከል መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

የኦዲት ግኝቶቹን ለ2012 በጀት ዓመት ስራ እንደ ግብአት በመውሰድ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ ተመላሽ ሊሆኑ የሚገባቸውን ሂሳቦች ተመላሽ በማድረግና ከህግ ውጪ የሆኑ ክፍያዎችን በማስቆም ፍሬያማ ስራ መሰራቱን አመላክተዋል፡፡ ለተለያዩ ወጪ ሂሳቦች ያልተያያዙ ማስረጃዎችን በማሟላትና ከሰነዶች ጋር በማያያዝ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸውን በሚመለከተው አካል በማስወሰንና በማፀደቅ ክፍተቶችን ማስተካከል መቻሉን ያብራሩት ፕሬዚዳንቱ የበጀት ዓመቱ ሂሳብ በመዘጋቱ የተወሰኑ የኦዲት ግኝቶችን ማስተካከል ያለመቻሉን ጠቁመው የ2010 በጀት ዓመት የኦዲት ግኝቶችን በተሰጠው አስተያየት መሠረት ለማስተካከልም 73% እርምጃ መወሰዱን ገልፀዋል፡፡

,እንደ ሀገርም ጭምር የህግ ማዕቀፍ የሌላቸው በዩኒቨርስቲ ማስተማሪያ ሆስፒታሎች የሚሰሩ ሀኪሞች ክፍያዎች መኖራቸው፣ የማስተማሪያ ሆስፒታሎች የፋይናንስ አሠራር የተለየና ከዩኒቨርሲቲዎች አሠራር ወጣ ያለ መሆኑ፣ በዩኒቨርሲቲው ስር ያለው የንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ሆስፒታል ቀደም ሲል በክልል አስተዳደር ስር የነበረ በመሆኑ የነበረበትን የፋይናንስ አሠራር ይዞ የመጣና የራሱ የሆነ የውስጥ ገቢ አስተዳደር ስርዓትና የሀኪሞች ጥቅማጥቅም አተገባበር ያለው መሆኑ፣ ለዩኒቨርሲቲው የተመደበው በጀት፣ ግበአቶችና የአደረጃጀት መዋቅር ባለብዙ ኮሌጆች ካምፓሶችን ከሚሸፍነው የዩኒቨርሲቲው የፋይናንስ፣ የቁጥጥር እና አስተዳደራዊ ተግባራት ጋር የማይጣጣሙ መሆናቸው እና በአሁን ሰዓት ማስተካከያ ቢደረግም በኦዲቱ ወቅት የነበሩት በርካታ የዩኒቨርሲቲው የአመራር ቦታዎች ክፍት የነበሩ መሆኑና ብዙዎቹም የፋይናንስና ሌሎች ተግባራት የሙያው ባለቤት ባልሆኑ ሰዎች ሲመሩ የነበሩ መሆናቸው ለክፍተቶቹ መነሻ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ከፕሬዚዳንቱ ምላሽ በኋላ ሌሎች የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ማጠናከሪያ ሀሳቦችን ያቀረቡ ሲሆን በመድረኩ ላይ የተገኙ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በቀረቡት ጥያቄዎችና በተሰጡት ምላሾች ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶችን ሰንዝረዋል፡፡

የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ክቡር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ  በቀረቡት ነጥቦች ዙሪያ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን በተለይም በዩኒቨርሲቲው አመራሮች የተነሱ የአሠራርና የህግ ማዕቀፍ ችግሮችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን የጋራ የሆኑ የማስተማር፣ የምርምርና የእውቀት ሽግግር  ሶስት ተልዕኮዎችን እንዲወጡ የሚጠበቅባቸው መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ በማስተማሪያ ሆስፒታሎች የሚገኙ ሀኪሞች ከሌሎች መምህራን በተለየ መልኩ ለህብረተሰቡ የህክምና አገልግሎት የመስጠት አራተኛ ተልዕኮ የሚፈፅሙ በመሆናቸው በአሠራር ባህሪያቸው የሚለዩ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በዚህም ከህክምናና የህክምና ባለሙያዎች ጋር ያለውን የጥቅማጥቅምና ሌሎች ተዛማጅ ክፍተቶች ለማስተካከል የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር ለማስቻል ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ከጤና ሚኒስቴር ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች የፋይናንስ፣ የአደረጃጀትና መዋቅራዊ ችግሮችን ለመፍታት የትምህርት ተቋማቱን የአሠራር ስታንዳርዶችን ከመፈተሽ ጀምሮ ከሌሎች የመንግስት ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የትምህርት ተቋማት በበኩላቸው አሰራራቸውን ወደ ዲጂታልና አውቶሜሽን የቴክኖሎጂ ስርዓት በአፋጣኝ ማስገባት እንደሚገባቸው እና  ለሚታዩ ክፍተቶች ዋነኛ መነሻ የሆነውንና በሰፊው የሚታየውን የአመራር ክህሎት ክፍተት ለመቅረፍ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስልጠና መርሀ ግብሮችን አዘጋጅቶ ተከታታይ የአመራር ክህሎት ስልጠናዎችን ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የኦዲት ግኝቶችን ለማስተካከልና ክፍተቶችን በተደራጀ መልኩ ለማረም እያደረገ ያለውን ጥረት በበጎ ጎኑ የሚመለከቱት መሆኑን ጠቅሰው የዩኒቨርሲቲው አመራር በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በአካል ተገኝቶ የሀሳብ ድጋፍ ለማግኘት ያደረገው ጥረትም ተገቢ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

የኦዲት ግኝት ማስተካከያ መርሀ ግብርና ሪፖርቶች ለመስሪያ ቤቱ በወቅቱ ያለመድረሳቸው  ክፍተት መሆኑን የጠቆሙት ዋና ኦዲተሩ በዩኒቨርሲቲው የታዩ አብዛኞቹ ክፍተቶች ከቁጥጥርና ክትትል አቅም ማነስ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ገልፀው በውስጥ ገቢ አሰባሰብ፣ አስተዳደር እና አጠቃቀም ላይ ህጋዊነትን የተከተለ አሠራር መኖር እንደሚገባውም  አሳስበዋል፡፡ በቂ የበጀት ዝግጅት ጥናት ያለማድረግ ለብልሹ የበጀት አጠቃቀም እንደሚዳርግ ያመላከቱት ክቡር አቶ ገመቹ ከበጀት በላይ መጠቀም፣ አግባብ ያልሆኑ የኮንትራት የአበልና የትርፍ ሰዓት ክፍያዎችም ህጋዊ አካሄድ ሊኖራቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በየዩኒቨርሲቲዎች የተቋቋሙት ኢንተርፕራይዞች እስካሁን ድረስ ህጋዊ መሰረት የሌላቸው ናቸው ያሉት ዋና ኦዲተሩ ህጋዊ መሰረት እንዲኖራቸው መሰራት እንዳለበትና የሚሰማሩበትንም የስራ መስክ በአግባቡ መለየት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡ መመሪያና ደንብን  ባልተከተለ ሁኔታ የተከፈሉ ክፍያዎችን ተመላሽ በማድረግ ለገንዘብ ሚኒስቴር ገቢ ማድረግ እንደሚገባ  አመላክተዋል፡፡

በአደረጃጀትና መዋቅራዊ ክፍተቶች ሳቢያ የተከሰቱ የሂሳብ አሠራር ጫናና ሌሎች ተዛማጅ ችግሮችም የፋይናንስ አሠራሩን ያልተማከለ ማድረግን ጨምሮ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በኩል በሚሰጡ ተገቢ መፍትሔዎች አማካይነት ማስተካከል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የኦዲት ዘርፍ ም/ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የኦዲት ግኝቶችን ለማረም እያደረገ ስላለው ጥረት በመድረኩ ላይ የቀረበውን ሀሳብ አድንቀው በአንዳንድ ክልሎች  የሚገኙ የፌዴራል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በክልሎች የቦታ ግብር የሚጠየቁበት አግባብ ህገ መንግስቱን የጣሰ በመሆኑ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጉዳዩን እንዲፈትሸው አሳስበዋል፡፡ 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስቴር ተወካይ በበኩላቸው ትክክለኛና ዝርዝር የኦዲት ግኝት ማስተካከያ መርሀ ግብር ተቀርጾ በወቅቱ መቅረብ እንደሚገባውና በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አስተያየት መሠረት የሚወሰዱት የእርምት እርምጃዎችም በውስጥ ኦዲት አማካይነት እየተፈተሹና በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ክትትል እየተደረገባቸው ውጤታማነታቸው መረጋገጥ እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው የፋይናንስ ዘርፍ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙ በበኩላቸው የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የኦዲት ግኝቶችን ለማስተካከልና አስተያየት መስጠት ካልተቻለባቸው ክፍተቶች ለመውጣት እያደረገ ያለው ጥረት አበረታች ጅምር መሆኑንና ለሌሎችም በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን  ጠቁመው በሌሎቹም ዩኒቨርሲቲዎች ጭምር በየጊዜው የሚታዩ ተመሳሳይ የኦዲት ግኝቶችን  ለማስተካከል የሁሉም አካላትን ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን አሳስበዋል፡፡

በተለይም የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርሲቲዎችን እንደየአፈፃፀም ደረጃቸው ጥንካሬቸውንና ድክመታቸውን በመለየትና ደረጃ በመስጠት እርስ በእርሳቸው የሚማማሩበትንና ልምድ የሚለዋወጡበትን ሁኔታ ቢያመቻች የተሻለ መሆኑን አመላክተው ዩኒቨርሲቲው በክፍተቶቹ ላይ በመርሀ ድርጊት የተደገፈ እርምጃ በመውሰድ ውጤቶቹንም ለፌዴራል ዋና ኦዲተርና ለሌሎች አካላት በሪፖርት ማቅረብ እንደሚገባው አመላክተዋል፡፡

በመጨረሻም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መሀመድ የሱፍ የተዛቡና ህግን ያልተከተሉ አሠራሮችን ለማስተካከል የውስጥ ኦዲትን በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው የዩኒቨርስቲም ሆኑ የሌሎች ተቋማት አመራሮች የያዙትን የሀላፊነት ቦታና የትምህርት ደረጃ የሚመጥን የስራ ቁርጠኝነት በማሳየት የተሻሉ አሠራሮች እንዲመጡ አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በአሁን ሰዓት ዋናውን ግቢ ጨምሮ የተለያዩ ኮሌጆች ያሏቸው ሶስት ካምፓሶችን የያዘ ሲሆን 5 ሺህ ሠራተኞችን ያቀፈና ከ 27 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡(የፌ/ዋና ኦዲተር)

 

 

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

To Top