Connect with us

“እረፉ!”

"እረፉ!"
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

“እረፉ!”

“እረፉ!”

(ጫሊ በላይነህ)

የሱዳን ጦር ከወራት በፊት ጀምሮ በጎንደር በኩል የፈጸመው የተስፋፊነት ጥቃት ልብ የሚሰብር ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ አንዳንድ የሱዳን የጦር መሪዎችና ሚዲያዎች “መሬታችንን አስመልሰናል”  ወደሚል ጉሮ ወሸባዬ መሸጋገራቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስትን ትግዕስትና አርቆ አሳቢነት እንደፍርሀት መቁጠራቸው የሚያሳዝን ነው፡፡ “የኢትዮጵያ መንግስት በውስጥ ችግሩ ተጠምዷል፣ ተዳክሟል፣ አብቅቶለታል” በሚል የጠላት አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ የተሳሳተ ስሌት ይዞ በድንገት ወረራ በመፈጸም የሰፈር ሚሊሽያ እና ሰላማዊ ሰዎችን ላይ ጉዳት ማድረስ እንዲሁም በኃይል የአንድ ሀገር ሉዐላዊነት መድፈር  ዓለም አቀፍ ሕጉን ትተነው ከሞራል አንጻር አስነዋሪ ድርጊት ነው፡፡ ክስተቱ የለየለት ክህደትም ነው፡፡

ወረራዎቹ ቢገባቸው በያዝነው 21 ኛው ክፍለዘመን  ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ ሞትና እልቂት ብቻ መሆኑን በተረዱ ነበር፡፡  የጦርነት ትርፉ መፈናቀል፣ ስደት፣ ረሐብ እና ድህነት ነው፡፡ የሱዳን  የድንበር ይገባኛል ጥያቄ  ሱዳን ከቅኝ ግዛት ከተላቀቀችበት ከ1950 ዎቹ ጀምሮ ሲነሳና ሲወድቅ የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ ጥያቄው በኢትዮጵያ እና በሱዳን በኩል በሚደረጉ ውይይቶች፣ ድርድሮች እንጂ በጉልበት ሊፈታ አይችልም፡፡ የጉልበት ትርፉ ደም መፋሰስ ነው፡፡ የጉልበት ትርፉ የኢኮኖሚ ኪሳራ ነው፡፡ የጉልበት ትርፉ  ተከባብረው የሚኖሩ ሕዝቦችን አለያይቶ ሆድና ጀርባ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ ይኸን እውነታ ከማንም በላይ የሱዳን ሕዝብ ጠንቅቆ እንደሚያውቀው በግሌ አምናለኹ፡፡

ግጭቱን አስመልክቶ በሱዳን መንግስት ደረጃ የሚታወቅ ወረራ አለመፈጸሙ መነገሩ በበጎ የሚታይ ነው፡፡ ይኸ የሱዳን መንግስት አቋም የሚያሳየው ጉዳዩ የሱዳን መንግስትና ሕዝብ ሳይሆን የጥቂት ፖለቲከኞችና ወታደራዊ ሹማምንት ግላዊ ፍላጎት መሆኑ አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡ በተለይ የሱዳን ወታደራዊ ኃይሎች ጀርባ ላይ ተፈናጥጠው የሚጋልቡ የኢትዮጵያ ጠላቶች ዛሬም ለጥፋት ብቻ ላባቸውን እየዘሩ መሆናቸውን መደበቅ እንኳን አለመቻላቸው ብዙ የሚነግረን ነገር አለ፡፡

የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳደር በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው የኢትዮጵያ መንግስት በህወሓት ከሀዲ ቡድን ላይ የሕግ ማስከበር እርምጃ መውሰድ በጀመረ በጥቂት ቀናት ልዩነት ማለትም ከጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የሱዳን ወታደሮች በዞኑ አርሶ አደሮች የእርሻ ካንፕ የመውረር ፣የማቃጠል፣ንብረት የመዝረፍ፣ ህይወት የማጥፋትና ባልተለመደ ሁኔታ  በርካታ መካናይዝድ ጦር በማዝመት በሞርታር፣ዙ 23ና መድፍ ቀጠናውን  በማወክ በተስፋፊነት ስሜት  በርካታ ጉዳት አድርሰዋል፡፡  በዚህም  በአርሶ አደሩ  ካንፕ ለዘመናት የተከማቹ የእርሻ  ማሽነሪዎች፣ሰብልና እንስሳት  ሳይቀር አውድመዋል፡፡  በቢሊየን ብር የሚገመት ንብረቶች ዘርፈዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ አባውራና እማውራዎች ተፈናቅለዋል። ንጹሀን  ዜጎችንም ምንም ባላጠፉበት ሁኔታ ለእስርና መንገላታት ተዳርገዋል፡፡ ይኸ ችግር አሁንም ሞቅ በረድ እያለ እንደቀጠለ ነው፡፡

ለወረራ ኃይሎች ድርጊቱ ዓለም አቀፍ ሕግን መጻረር ስለመሆኑ፣ በጎረቤት ሀገራት መካከል ሊደረግ ቀርቶ መታሰብ የሌለበት ጥፋት መሆኑን ማስረዳት በከንቱ ጉንጭን ማልፋት ይሆናል፡፡

አሁን መፍትሔው ቁልጭ ያለና ግልጽ ነው፡፡ የሱዳን ወታደሮች ያለምንም ማንገራገር በወረራ የያዙትን አካባቢዎች በአስቸኳይ ለቀው ይውጡ፡፡ የተጎዱ መሰረተ ልማቶችና የኢኮኖሚ አውታሮች ተገቢውን ካሳ ይስጡ፡፡ ሰላማዊ ጉርብትናውም በይቅርታ ታድሶ እንደትላንቱ ይቀጥል፡፡ ሰላማዊ መንገዱ ይኸው ነው፡፡

በተቃራኒው እምቢታን ከመረጡ ና በጉልበት መሬት ይዘን  እያቅራራን እንቀጥላለን ካሉም ምርጫው የእነሱ ነው፡፡ በኢትዮጵያዊያንን ጀግኖች ተደቁሰው ወደመጡበት ይመለሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ድንበር አለመግባባቱ የሚፈታው በሁለቱ ሀገራት ውይይት ብቻ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ መግለጫ የሰጠችበትና የታወቀ አቋምዋ ነው፡፡ ግን ወደጦርነት ተገድዳ የምትገባ ከሆነ ሰላምና ፍቅር ያልገዛውን በኃይል ልትገዛው ትችላለች፡፡

አባቶች፡-

“እንኳን አሁንና ሙሉ ትጥቅ እያለን

በጦር በጎራዴ ታንክ እንማርካለን” እንዲሉ፤ የጠገበን ኃይል ቆንጥጦ፣ አስተምሮ መመለስን ታውቅበታለች፡፡ እንደአንድ ኢትዮጵያዊ  ምክር የምለግሰው በተሳሳተ መስመር ውስጥ የገቡ የሱዳን ወንድሞችና እህቶች ፈጥነው ወደልቦናቸው እንዲመለሱ ነው፡፡  ከጦር አውርድ ፋከራቸው መለስ እንዲሉ ነው፡፡ በአጭሩ  “እረፉ” ማለት እፈልጋለኹ፡፡

እዚህ ላይ የእያዩ ፈንገስ “እረፉ” ጋብዤ ልሰናበት፡፡

“እረፉ!…

ዘመመ ብላችሁ የሰው ቤት አትግፉ

እሾህ ለማሳመር አበባ አታርግፉ፤

እረፍ!..

ቆሜያለሁ ለማለት አጥሬን አትደገፍ

ለአመዳም ወዘናህ ቆዳዬን አትግፈፍ…”

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top