Connect with us

“ጉድ አለ ሰማይ ጉድ አለ መሬት ላልነበረ ሰው ይመስላል ተረት”

"ጉድ አለ ሰማይ ጉድ አለ መሬት ላልነበረ ሰው ይመስላል ተረት"
አብመድ

ነፃ ሃሳብ

“ጉድ አለ ሰማይ ጉድ አለ መሬት ላልነበረ ሰው ይመስላል ተረት”

“ጉድ አለ ሰማይ ጉድ አለ መሬት

ላልነበረ ሰው ይመስላል ተረት”

ላላዩት ተረት፣ ለሚሰሙት ውሸት፣ ለነበሩበት ምትሃት ይመስላቸዋል። ነጭ ጉም በተራራው ላይ ይትጎለጎላል። የአካባቢው ብርድ እጅ ያሳስራል። ተራራው እንኳን በጦርነት በሰላም ጊዜ ልብ ይፈትናል። ጀግና እንጂ ፈሪ አይሞክረውም። ቢሞክረውም አይወጣውም። ወደላይ ሲያዩ አቀበት ወደታች ሲመለከቱ ቁልቁለት፣ በዚያ ላይ ከባድ መሳሪያ፣ የተጠናበት ምሽግ፣ አሰፈሪ ዱር፣ የተጥመዘመዘ መንገድ፣ የተወሳሰበ ምድር ነው – ግራካሶ። ምድር ራደች፣ ድብልቅልቁ ወጣ። በምድር ሲሉት በሰማይ፣ በቀኝ ሲሉት በግራ ፣ በፊት ሲሉት በኋላ ፋታ የማይሰጥ ውጊያ ተደረገ። የደፈረ ሲቀርብ የራቀ ይሸሻል።

                 “አየር በሰማይ ያንዣበበ ለት

                 ታንክ በምድር የተንኳኳ ለት

                 ወንዱ አባ ደፋር በለው ያለለት

                 ፈሪና ደፋር የተለየለት

                 ጉድ አለ ሰማይ ጉድ አለ መሬት

                 ላልነበረ ሰው ይመስላል ተረት” እንዳለ በቦታው ላልነበረ ተረት ይመስላል። ግን እውነት ነው። በተራራው ግርጌ አድሮ ለመዋጋት ብርዱ እጅ ያሳስራል ይሉታል። ልቡ ለጋለ ግን እጁ ከምላጩ ጋር ሲስማማ ያድራል። በዚያ አቀበት ስንቅና ትጥቅ ይዞ በእግር መውጣት ሌላ ጀግንነት ነው። ከላይ ያለን ጠላት ከታች ሆኖ እየደመሰሱ ወደላይ መውጣት ደግሞ ሌላ ወደር የለሽ ጀግንነት ነው። በአካባቢው የሚኖረው ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን በግራካሶ የሚገኙ አዕዋፋትና የዱር አራዊት ተጨንቀዋል።  የትኛው አይሎ ምሽግ እንደሚሰብር ጉጉት ፈጥሯል። የሚያጓራው የከባድ መሳሪያ ደምፅ ተራራውን የናደው እስኪመስል ድረስ ድምፁ ያስፈራል። ከራያ ቆቦ በተጠንቀቅ ቦታ ይዞ የሰነበተው የአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ ወደፊት ሂድ የሚባልበትን ቀን እየተጠባበቀ ነው። የትህነግ ታጣቂ በሰው ቁመት ልክ ምሽግ ቆፍሮ ተዘጋጅቷል። ሕዝቡ ተጨንቋል። ትዕዛዝ ሲጠብቅ የነበረው የአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ ትዕዛዝ ተሰጥቶት እንቅስቃሴ ጀመረ። ትህነግ በቁመት ልክ ያስቆፈረችው ምሽግ ዋስትና እንደማይሆናት ስታውቅ ፈረጠጠች። ትህነግ ስትሸሽ የጀግናው ስብስብ ሲከተል የዋጃ፣ ጥሙጋና አላማጣን ከተሞችን ያዘ። እንደ መዳፍ የለሰለሰው የራሃ ምድርም የሰላም አየር መተንፈስ ጀመረች።

ትህነግ በእግር በመኪና እየፈረጠጠ ግራካሶ መሰግሰግ ጀመረ። በዚያ ተራራ የሞት ሽረት ውጊያ ታቅዶበታል። የግራካሶ ተራራ ተፈጥሮ ለጦርነት ካሰመረው በላይ ትህነግ ዓመታት ያሻግራል ያለችውን ምሽግ ቆፍራለች። ትህነግን እያበረረ ከተራራው የሰቀላት ጀግና ሜዳውን ጨርሶ ወደ ዳገቱ መውጣት ጀመረ። ጥይት አጓራ። በተራራው ጫፍ ጀምሮ እስከታች የተሰገሰገው የትህነግ ታጣቂ ከታች የሚመጣውን ሰራዊት የጦር ሜዳ መነፀር ሳያስፈልገው በደንብ ይመለከተዋል። ከታች ወደላይ የሚወጣው ግን መልከዓምድሩ አይፈቅድለትም።

የአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ ጥሻ እየጣሰ፣ ምሽግ እያፈረሰ፣ ጠላቱን እየደመሰሰ ገሰገሰ። ምን አለ ግራካሶ ያን ዕለት? እንዴትስ ተጨነቀ? ወደላይ የሚወጣው ጀግና ምንም ሊመልሰው አይችልም። ከባድ መሳሪያ እየተወረወረበት፣ የጥይት በረዶ እየዘነበበት፣ የዳገቱ የእግር ጉዞ ጠንቶበት ወደፊት እንጂ ወደኋላ አይመለከትም። እንኳን ወዳጁን ጠላቱን ገረመው። የጠላት ልብ ተሸበረ። ምሽጉ ተሰበረ። በግራ ካሶ ውጊያ የተሳተፉና ጠላትን ያሳፈሩ የአማራ ልዩ ኀይል አባላት ያን ጀግንነት አይረሱትም።

ምክትል ሳጅን በቀለ ይግዛውና ኮንስታብል ሰፊው ዓባይ በግራካሶ ውጊያ ተሳትፈዋል። ትህነግ በመከላከያ ሰራዊትና በአማራ ክልል ላይ ጥቃት ከመክፈቷ አስቀድሞ የአማራ ልዩ ኀይል የነበረው ትዕግስትና ትህትና ልዩ ነበር ይሉታል። ትህነግ የሚያደርገውን ትንኮሳ በትዕግሥት ያልፉት ነበር። ፅንፈኛው ግን ትዕግሥቱን ፍርሃት አስመሰለው። የጀግና ልጆች መሆናቸውን ረሳ። አርፈው ከተቀመጡበት አስነስቶ ነብር ሊያደርጋቸው እሳት ይዞ ይዞራቸዋል። ዝም አሉት። አላረፈም። የእጁን እሳት ለኮሰው። አዳፍነውት እንጂ ከእነሱም ከጀመረ የማይጠፋ፣ ከነደደ የማያንቀላፋ እሳት እንዳላቸው አሳዩት። በእነርሱ ብቻ ሳይሆን ሲያዞረው የነበረውን እሳት ከእጁ ላይ እየነጠቁ ያቃጥሉት ጀመር። ነዲዱ አስፈራው። በግርማው ገረፈው። አሻግሮ አቃጠለው። ቀርቦ አከሰለው። የግራካሶ ውጊያ ከባድ ነበር ፤ ነገር ግን ከልባችን ላይ የታጠቅን ስለነበር በድል ተወጥተነዋል።  ምሽግ ቢደረደር፣ መሳሪያ ቢወደር ካለ ልብ ሁሉም ባዶ ነው ሲሉ ነበር  እነዚያ ጀግኖች የነገሩኝ። ሰራዊቱ ተራራውን ሲወጣ አስደማሚ ነበር ነው ያሉት። ከቦታው አመችነት ባለፈ ከባድ መሳሪያ ይጥሉብን ነበር ፤ ነገር ግን ከማሸነፍ ያቆመን አልነበረም ሲሉ ያስታውሱታል።

የአካባቢው ነዋሪዎችና የልዩ ኀይል አባላት የነገሩኝ አንድ አስደናቂ ታሪክ አለ። የትህነግ ታጣቂ ዋጃ፣ ጥሙጋና አላማጣን ፈርጥጦ ሲለቅ የአማራ ልዩ ኀይል ሲከተል ያጣቸዋል። በዚህ ወቅት የአማራ ልዩ ኀይል ሸሹልኝ ብሎ አልተደሰተም።ለምን ሳይገጥሙን ሸሹ የሚለው አበሳጨው። በእልህና በንዴት ነበር ወደ ግራካሶ ተራራ የወጣው። አማራ እንኳን ወዳጁ ጠላቱም ሲፈራ ይናደዳል። ደርሶ አይነካም እንጂ ከነኩት በኃላ ተፈትኖ ማሸነፍን ነው የሚወደው። ወንድነቱን ሊያሳያቸው ይፈልጋልና ጠንከር ብለው እንዲገጥሙት ነው ፍላጎቱ። ልፍስፍስ አይወድም።  ምሽጉ ከአላማጣ ራስጌ እስከ ኮረም ግርጌ ድረስ ነበር። ከአስራ ሰምንት ያላነሰ ኃይለኛ ምሽግ ነበረው ያ ለታሪክ የተፈጠረ ተራራ። ሁሉም ፈረሰ። ከተራራው ጫፍ አስፓልት በግሬደር ቆፍራ ታገለች። ያም አልተሳካላትም።

የአማራ ልዩ ኀይል እንደ አማራነት ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያዊነት እንደሚያስብ ነው የሚናገሩት። ስራቸውም ይህንኑ ነው የሚያሳይ። ለኢትዮጵያ መኖር ከጥንት የመጣ ከአባቶቻቸው የወረሱት መሆኑንም ነግረውኛል። የአማራ ልዩ ኀይል አዛዦች ጀግንነት አባላቱን አስደምሟል። አዛዦቹ ጦር እየመሩ ይገቡ ነበር። ማዋጋትም መውጋትም ነበር ስራቸው። የጦርነት ስልታቸው ጠላት አያስበውም ነው የሚሏቸው። አማራ ተፈታኝ ነው። ታሪኩ ተፈትኖ ማለፍ፣ ተወዳድሮ ማሸነፍ መሆኑንም ነግረውኛል።  “እኛ የወጣነው ለሕዝብ ነው። የምንኖረውም ለሕዝብ ነው። ጀግና የጀግና ልጆች ነን ይሄን ደግሞ ወደፊትም እናስመሰክራለን” ነው ያሉት።

በአማራ ልዩ ኀይል የዓባይ ብርጌድ ምክትል አዛዥ ኮማንደር ጌታቸው ተፈራ የክልሉ መንግሥት ግዳጅ ከሰጣቸው ጊዜ ጀምሮ የክልሉን ሰላም ለመጠበቅና ጠላት አደጋ እንዳያደርስ ሲጠባበቁ መቆየታቸውን ተናግረዋል። ትህነግ ጥቃት ስትጀምርም ገዢ የሚባሉ ሥፍራዎችን በመያዝ አስፈላጊ የሆኑ ቦታዎችን መቆጣጠር መቻላቸውንም አስታውሰዋል። ግራካሶ እልህ አስጨራሽ ውጊያ ነበር፣ ነገር ግን በጠላት ላይ እርምጃ ወስደን ቦታውን አስለቅቀን ነው የገሰገስነው ብለዋል። ግራካሶን አስለቅቀው በኮረም ሕዝብን በማረጋጋት ባሉበት ጊዜ በዋጀራት ትንኮሳ ሲያደርግ ተከታትለው መደምሰሳቸውንም ያስታውሳሉ። በግራካሶ የተገኜው ጀብድ ለሠራዊቱ በቀጣይ ለተደረጉት ውጊያዎች መነሳሳት ፈጥሮ እንደነበርም ተናግረዋል። የአማራ ልዩ ኀይል ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን አስደናቂ ጀብዱ መፈፀሙንም ነግረውኛል። ልዩ ኀይሉ የአማራን ሕዝብ ክብር ከፍ ለማድረግ የማይከፍለው መስዋትነት እንደማይኖርም ገልፀዋል።

የትህነግ ቡድን በአማራ ሕዝብ ላይ ያልፈፀመው በደል አለመኖሩንም አስታውሰዋል። በትህነግ ላይ የተወሰደው ርምጃ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሞራል የሚጠብቅ ስለመሆኑም ተናግረዋል። ሕዝቡ ደግፎናል፤ በከፈልነው መስዋዕትነትም ኮርተናል ነው ያሉት።

የአማራ ልዩ ኀይል አማራን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንም ለመጠበቅ ዝግጁ መሆኑ መታወቅ አለበት ነው ያሉት ኮማንደር ጌታቸው። “ከኢትዮጵያ በላይ ምንም ነገር የለም፣ የሚያዋጣንም ኢትዮጵያዊነት ነው። ኅብረተሰቡ ሀገሪቱ ሰላም እንድትሆን ርብርብ ማድረግ አለበት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጠንን አደራ በሙሉ ልብና በታማኝነት ማንንም ከማንም ሳንለይ ለመፈፀም ዝግጁ ነን። እናደርገዋለንም” ነው ያሉት ኮማንደር ጌታቸው።

አዕዋፋትና አራዊት ተረጋግተዋል። ግራካሶ ዝምታን መርጧል። ግራካሶ በተለያዩ ዘመናት እልህ አስጨራሽ ውጊያ ተካሂዶበታል። ጀግና ተፈትኖበታል። ተፈትኖም አሸንፎበታል። ከታች እስከ ላይ በትዝብት ቃኘሁት ያስደምማል። ያን ሁሉ ጉድ እንዳላዬ አሁን ላይ አረንጓዴ ካባውን ለብሶ ሰውን የሚታዘብ ይመስላል። አስፈሪው አልፏል። ሰላምም መጥቷል። ጀግናው አሁንም በንቃት ሕዝቡን እየጠበቀ ነው።

(በታርቆ ክንዴ ~ አብመድ)

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top