ከአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት፡-
የሶማሊ ክልል መንግስት በአፋር ክልል ላይ ስላወጣው ፀብ አጫሪ መግለጫ የተሰጠ ምላሽ
“ሀገራችን ባለችበት በዚህ ምጥ ወቅት የጦርነት ጉሰማ ማሰማት ሀገርን ከማፍረስ አይተናነስም!”
በቅድሚያ በትናንትናው እለት ገዋኔ ወረዳ ፍሪትሊ እና ሪፎ ቀበሌ ላይ የሚገኙ በመንደር የተሰባሰቡ የአርብቶ አደር ማህበረሰብ ላይ ከሌሊቱ 11:00 ሰዓት ጀምሮ ከዚህ ቀደም ይደርስ የነበረው መሰል የሽብር ጥቃት ደርሷል። በዚህም ጥቃት በሁለቱም በኩል ስለደረሰው ህልፈተ ህይወትም የክልሉ መንግስት የተሰማውን ሀዘን ይገልፃል።
የሶማሊ ክልላዊ መንግስት አንድ ሉአላዊ በሆነ በጋራ ሀገር ውስጥ እየኖርን ግልፅ የሆነ የጦርነት አዋጅ በይፋ ማወጁን ቀጥሏል።
ካሁን በፊት በ2007 በቀድሞ የሁለቱ ክልል መሪዎች እና በፌደራል መንግስት ስምምነት መሰረት በአካባቢው አልፎ አልፎ ይከሰቱ የነበሩ ግጭቶች ለማስቆም እና የአርብቶ አደር ማህበረሰቡን በአብሮነትና በጋራ ህይወቱን እንዲቀጥል ለማስቻል የተደረሰበትን ስምምነት ወደ ጎን በመተው በቀን 25/08/2011 ግልፅ የጦርነት አዋጅ በወንድማማች ማህበረሰብ ላይ ማወጁ በይፋ በክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ በቁጥር XXAD/503/2011/EC የተፃፈ ደብዳቤ በተለያዩ ሚዲያዎች ማሰራጨቱ እና አዋጁም ማወጁ ይታወሳል።
ከዛ ጊዜ ጀምሮ ባለፉት ዘመናት አልፎ አልፎ ይከሰት ከነበረው ግጭት መልኩን በቀየረ ሁኔታ ግጭቶች እየተባባሱ መጥተዋል።ለአብነትም በዞን አንድ አፋምቦ ወረዳ ኦብኖ ቀበሌ የአርብቶ አደር ማህበረሰብ ላይ የዘር ማጥፋት በሚመስል መልኩ ሴቶች፣ ህፃናትና አዛውንቶችን ማእከል ያደረገ አሰቃቂ የሆነ የሽብር ጭፍጨፋ ጥቅምት ወር 2012 ከሌሊቱ 10:00 ሰዓት ጀምሮ ተፈፅሟል።
ከዚህም ቀጥሎ በዞን ሶስት ሀንሩካ ወረዳ ሰርካሞና ቴሌ ቀበሌ ላይ በመንደር የተሰባሰቡ አርብቶ አደር ማህበረሰብ እንዲሁም በክልሉ በተከሰተው ጎርፍ ሀብት እና ንበረታቸው የወደመባቸው ማህበረሰብ ላይ ከሌሊቱ 11:00 ሰዓት የሽብር ጥቃት በማድረስ ሴቶችና ህፃናት የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል።
በተደጋጋሚ በአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ላይ የሚደርሰው ጥቃት እየጨመረ ከመሄዱም ባሻገር የፌደራል የፀጥታ መዋቅር አካላት፣ የፌደራል የትምህርት ሚኒስቴር የስራ ባልደረቦች፣ ለክልሉ በጎርፍ ለተጎዱ ማህበረሰብ ከድሬዳዋ የሰብአዊ ድጋፍ ይዘው በመጡ የድሬዳዋ ፖሊስ አባላት እና በአካባቢው በሚኖሩ እና በሚተላለፉ ማህበረሰብ ላይ መሰል ጥቃት በተደጋጋሚ መድረሱ ይታወቃል።
በትናንትናው እለትም በዞን ሶስት ገዋኔ ወረዳ ሁለት ቦታዎች ፍሪትሊ እና ሪፎ ቀበሌ ከላይ የሚገኙ በመንደር የተሰባሰቡ የአርብቶ አደር ማህበረሰብ ላይ ከሌሊቱ 11:00 ሰአት ጀምሮ ከዚህ ቀደም ይደርስ የነበረው መሰል የሽብር ጥቃት ደርሷል።
በዚህም የሽብር ጥቃት በአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ላይ ጥቃት የፈፀሙ የተደራጁ የኢሳ ቡድን አባላት እና የደረሰበትን ጥቃት በተከላከለው የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ በኩል የህይወት መጥፋት እና የመቁሰል አደጋ ደርሷል።
የሶማሊ ክልል ባለፉት ሁለት አመታት በተደጋጋሚ የሚያወጣቸውን ግጭት አባባሽ የሆኑ መግለጫዎች የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሆደ ሰፊነት እያለፈ እና በተለይም በጋራ የሚኖሩ ሰላም ወዳድ የአርብቶ አደር ማህበረሰብ አንድነት እንዳያናጋ የተለያዩ ስራዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሲሰራ ቆይቷል።
ሆኖም የሶማሊ ክልል መንግስት ግጭቶችንና ትንኮሳዎችን ቀድሞ በማስፈፀምና ከተጠያቂነት ለማምለጥ መግለጫዎችን ቀድሞ በማውጣት ወንጀለኞችን በመግለጫ ሽፋን ለመደበቅ የሚያደርገውን ሴራ በግልፅ አሳይቷል።
የሶማሊ ክልል በረጅም እጆቹ ጣልቃ ገብነት እና አካባቢው እንዳይረጋጋ ለማድረግ የሚደረግ ሴራ እና እንቅስቃሴ በክልሉ መንግስት ምንም አይነት ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ከድርጊቱ ሊታቀብ ይገባል።
የአፋር ክልል መንግስት በተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት የሚፈፀምባቸው አካበቢዎች በተለይም በኡንዳ ፎኦ እና ገዳማይቱ ላይ ልዩ ተልእኮ ተሰጥቷቸው የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች በቁጥጥር ስር ለማዋል ከፌደራል ፖሊስ ፣ከሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ከሰላም ወዳድ የአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን በመሰራት ላይ ይገኛል።
በተለይም በክልሉ አብረው የሚኖር የአርብቶ አደር ማህበረሰብ መካከል ጥርጣሬና አለመግባባት እንዲፈጠር የሚደረግ ሙከራዎች መኖሩን በተደጋጋሚ ሲስተዋሉና ስንገልፃቸውም መጥተናል።
ለዚህም ማሳያ የሚሆኑ የተደራጁ ልዩ ሀይል በማስገባት እና በክልላችን ወሰን ውስጥም የልዩ ሀይል ካምፖችን በመመስረት የተለያዩ የሽብር ጥቃት ሲፈፀም እንደመጣ በተለያዩ አጋጣሚ ስንገልፅ የነበረ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን አሁንም ቢሆን ይህን ሴራ እና እኩይ አላማ ለማስፈፀም የሚደረግ ሙከራ የቀጠለ መሆኑ የሶማሊ ክልል ያወጣው መግለጫ ማሳያ ነው።
ሆኖም የሶማሊ ክልል መንግስት ክስተቱን በተዛባ ሁኔታ በመግለፅ ሀላፊነት ከጎደላቸው የሶሻል ሚዲያ እብሪተኞች ሲደሰኩሩ የዋሉትን ቃል በቃል በመድገም በአፋር ክልል ህዝብና መንግስት ላይ ይፋዊ ጦርነት አሁንም አውጇል ፣ ክልሉንም አላስፈላጊ የሆነ ውንጀላ ወንጅሏል።
ይኸውም ሀገር ወዳዱ የአፋር ልዩ ሀይል እና ሚሊሺያ የሀገሩን ሰላም እና ደህንነት ለማስከበር ከጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ ደጀን ሆኖ ኢትዮጵያውያንን ያኮራ ጀብድ በመፈፀም ግዳጅ ላይ የሚገኘውን የክልሉ ፀጥታ ሀይል ስም ጥላሸት ለመቀባት ተራ ውንጀላ ወንጅሏል።
የክልላችን ፀጥታ ሀይል መንግስት የጀመረውን ህግ የማስከበርና የህልውና ዘመቻ ከተጀመረበት እለት ጀምሮ እስካሁኗ ደቂቃ ድረስ በሀገር እና በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ክህደት የፈፀመውን የጁንታ ሀይል ወደ ህግ ለማቅረብ እናም ጁንታው በክልላችንና በትግራይ ወሰን አካባቢ ተመሳስሎ እና ሾልኮ እንዳይወጣ በተሰጠው ግዳጅ መሰረት 24 ሰአት በተጠንቀቅ ላይ የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል።
በአካባቢው ምንም አይነት እንቅስቃሴ በሌለው በክልላችን ጁንታ እና ኡጉጉሞን ሽፋን በማድረግ በአርብቶ አደር ማህበረሰብ ላይ የሚደርሰው እና ለማድረስ የሚፈለገው ጥቃት ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ የሶማሊ መንግስት በተደጋጋሚ የሚያወጣቸው ግጭት ቀስቃሽና አባባሽ መግለጫዎች መለስ ብሎ እንዲመለከተው ለማሳሰብ እንወዳለን።
የክልሉ መንግስትም ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሀል እንደሚባለው በሰላማዊ አርብቶ አደር ህዝባችን ላይ ጥቃት ከተፈፀመ በኋላ ጥቃቱን ይበልጥ ለማፋፋም በሚመሰል መልኩ ለቅሶዬን ቀሙኝ በሚል ብሂል በማህበረሰብ ላይ የተጀመረውን ትንኮሳ ለማባባስ ከሚደረግ እንቅስቃሴ ታቅቦ የአፋር ክልል መንግስት የጀመረውን የሰላምና የማህበረሰብ አንድነት ሊያጠናክሩ የሚገቡ የህዝብ ለህዝብ ውይይት ፍሬ እንዲያፈራ እና አሸባሪዎችና ኮንትሮባንዲስቶች በአካባቢው ላይ እንዲስፋፋ የሚፈልጉትን ስርአት አልበኝነት እንዲገታ ሊያግዝ ይገባል።
የሶማሊ ክልል መንግስት ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በአካባቢው መልኩን በቀየረ አካሄድ ኮንትሮባንዲስቶችና አሸባሪዎች የአገሪቱን ሰላም እና መረጋጋት ከማይፈልጉ ሀይሎች ጋር ሆኖ ከውስጥም ይሁን ከውጭ እንደ ሁለተኛ ጁንታ ሆነው የአርብቶ አደር ማህበረሰብ ስጋት ሆነው የሚሰሩ ሀይሎችን በመቆጣጠርና በመመከት ቀጠናው ለማህበረሰቡ የስጋት ሳይሆን በነፃ ተንቀሳቅሶ ውሎ የሚገቡበት ለማድረግ የአፋር ክልል መንግስት የጀመረውን የማህበረሰብ አንድነት የሚጠናከርበት ሁኔታ በጋራ እንዲሰራ ለማሳሰብ እንወዳለን።
በመጨረሻም የሶማሊ ክልል በክልላችን ወሰን ዘልቆ ያስገባውን ልዩ ሀይል በአስቸኳይ እንዲያወጣና ለአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት ፀር የሆኑ ፀብ አጫሪ ኮንትሮባንዲስቶችና ሽብርተኞች ሽፋን ከመሆን እንዲታቀብና ከክልሉ መንግስት ጎን ሆኖ የራሱን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ እናሳስባለን።
ታህሳስ 19/2013
የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት
ሰመራ
(የአፋር ክልል ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ)