Connect with us

ራያ በድል ማግስት

ራያ በድል ማግስት
አብመድ

ነፃ ሃሳብ

ራያ በድል ማግስት

ራያ በድል ማግስት

ከዓመታት በኋላ የራያ አባቶች ተገናኝተዋል፤ ራያዎችም ደስታቸውን አክብረዋል፡፡ ትናንት አልፎ ዛሬ አዲስ ተስፋ ይዞ መጥቷል። ከባልንጀራ ጋር ያለ ስጋት ማውጋት፣ ያለ ሰቀቀን መጫዎት፣ በባሕል መደሰት፣ በእሴት መኩራት ዳግም ተመልሷል። ከግራ ካሱ ግርጌ በለምለሙ የራያ ምድር ደስታ አለ፤ ፍቅር አለ፤ መተሳሰብ አለ፤ በነፃነት መንቀሳቀስ፣ በነፃነት ማሞገስና መውቀስ ተጀምሯል።

ጊዜ ጀግናው “አንገፋም” ያሉትን ገፋቸው፤ “አንወድቅም” ያሉትን ጣላቸው፤ “አናልፍም” ያሉትን አሳለፋቸው፤ “ማን ከኛ በላይ ያሉትን” በላያቸው ሰው እንዳለ አሳያቸው፡፡ “መከራ ሲመጣ አይነግርም አዋጅ፣ ሲገሰግስ አድሮ ቀን ይጥላል እንጂ” እንዳሉ ለሰው የደገሱት መከራ ለራስ ይሆናል። ጊዜ ሆሆ… ብሎ ሰቅሎ እሪ… ብሎ ያወርዳል።

በተሰጠ ጊዜ መልካም ነገር መሥራት ለስምም ለወገንም ይበጃል። ከዋጃ ወደ አላማጣ መለስ ድንበር ተበጅቶለት፣ ክልል ተከልሎበት ለሁለት ተከፍሎ ዓመታትን የተሻገረው የራያ ምድር የጋራ ሕይወት ናፍቆት ቆይቷል። እብሪተኛው ትህነግ ሲወድቅ፣ አዲስ ጀንበር ስትወጣ ራያዎች ደስታቸውን በጋራ ማክበር ጀምረዋል።

የራያ አባቶች ዘ ወልድ፣ ስንዬ ሰገድ፣ ክፍሎና መዛርድ ዳግም ተገናኝተዋል። በዘመነ ትህነግ መዛርድ ከወንድሞቹ ተለይቶ፣ በናፍቆት ተጎድቶ፣ መከታ አጥቶ ቆይቷል። እኒህ አራቱ የራያ ወንድማማች የእርቅና የሠላም አባቶች ከዓመታት በኋላ በአማላጣ ተገናኝተው ደስታቸውን አክብረዋል። በጋራ መርቀዋል። ስለመጪው ዘመንም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ራያዎች ከነፃነት ማግስት በአላማጣ ድግስ ደግሰው በጋራ አክብረዋል። ውቡ ባሕላዊ ጭፈራቸውን ጨፍረዋል፤ በሚስረቀረቀው ድምፃቸው “ላሌይ ጉማ” ብለዋል። መሰባሰብ ናፍቋት የነበረችው የራያ ምድር አላማጣ ከተማ በደስታ ዘላለች። ለካስ በኢትዮጵያ የተነፈገው መጫዎት፣ መሳቅና መደሰት ነው። አመስጋኙን ደግ ሕዝብ በተሰጠው አመስግኖ እንዳይደሰት ተከልክሎ ኖሯል ለካ። የታፈነው ደስታ ሲወጣ ምን ያክል በደል እንደነበር ያሳያል።

ራያዎችም የተነጠቁት ደስታ፣ የተከፈለው የጋራ ሕይወት አሁን ላይ ተመልሶላቸዋል። ደስ ብሏቸዋልና በራያ ባሕል ታላቅ አክብሮት የሚሰጣቸው የራያ አባቶች በጋራ ሲመርቁ፣ ልጆች በደስታ ሲቦርቁ፣ እናቶች ከሀዘን ወጥተው ሲሳሳቁ ከማዬት የሚቀድም ለዛች ምድር የለም። ቀዳሚው ይሄ ነበር ያገኙት ይመስላል። በአላማጣ ድግስ ተደግሶ ራያዎች ተሰባስበው አክብረውታል። “ራያ ወደ ሚመስለው ተመልሷል” ብለዋል። የግፍ ዘመን አብቅቷል፣ አሁን ሌላ ቀን መጥቷል። ራያም ደስታ ላይ ናት።

በዚህ የደስታ ቀን መልዕክት ያስተላለፉት የአላማጣ ከተማ ጊዜያዊ ከንቲባ አቶ ካሳ ረዳ “በማንነታችን ኮርተንና በአደባባይ ወጥተን በዚህ መልክ ለመሰባሰብ ላበቁን ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ምስጋና ይድረሳቸው” ብለዋል። የራያ ሕዝብ ከሕግ ውጭ በጉልበት ተገዶ ከወሎ ተሰዶ ወደ ትግራይ እንዲካለል ተደርጎ መቆየቱን አንስተዋል።

በትህነግ ዘመንም የራያ ሕዝብ በምጣኔ ሀብት እንዲጎዳ፣ ወጣቱ ትውልድ እንዲሰደድ፣ የራያ ባሕል እንዲጠፋ ሲደረግ መቆቱንም ጠቅሰዋል። የራያን ሕዝብ በማንነቱ እንዳይኮራና አንገቱን እንዲደፋ ትህነግ ሲሠራ መቆየቱንም ተናግረዋል። ከዚህ በኋላ የራያ ሕዝብ ወደ ቀደመው ወደ ወሎ ተመልሶ መተዳደርና ከወሎ ጋር መኖር ፍላጎቱ መሆኑንም አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት የራያ ሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄ እንዲሳካ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግም ከንቲባው ጠይቀዋል።

ሌላኛው በደስታው ቀን የተገኙት ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ የራያ ሕዝብ ለነፃነቱ ከምንም በላይ መታገሉን እና መስዋዕትነት መክፈሉን ጠቅሰዋል። ትህነግ ራያን ወደ ትግራይ ክልል ሲያካልል የተቃወሙ መገደላቸውንም አስታውሰዋል።

ትህነግ ለራያ ሕዝብ ታገልክ በሚል ምክንያት የእርሳቸውም ቤተሰቦች በስብሰባ እንዳይካፈሉ እና ሌሎች ጫናዎች ይደርሱባቸው እንደነበርም ተናግረዋል። የተገኘው ድል የረጅም ጊዜ ትግል ክምች መሆኑንም ዶክተር ሲሳይ አንስተዋል። በትግሉ ዘመን ሰላማዊ ሰልፍ በማድረጋቸው ብቻ የተገደሉ ወጣቶች መኖራቸውንም አስታውሰዋል።

“የተገኘው ድል በከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘ እንጂ በቀላል ነገር አልመጣም” ነው ያሉት ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ፡፡ በተለያየ መልኩ ሕዝቡን ለማንቃት ሲጥሩ መቆየታቸውንም አንስተዋል። “የራያ ሕዝብ ትግል ፍሬ አፍርቷል፤ ነፃነቱ ልማት እንዲያመጣ ማድረግ ይገባል፤ በተፈጥሮ የታደለውን አካባቢ ማልማትና ማደግ ያስፈልጋል” ብለዋል። የነበሩ ችግሮችን ማንሳት ብቻ ሳይሆን ወደፊት መራመድ እንደሚገባም አሳስበዋል።

“ለዘመናት አብሮት ከኖረው የወሎ አማራ ሕዝብ ጋር መኖር መቻል አለበት፤ ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት ማደስ ያስፈልጋል፤ ለ30 ዓመታት ግንኙነቱ ተቋርጦ ቢቆይም በመንፈስ አንድ ነበር” ነው ያሉት ዶክተር ሲሳይ። ከግራ ካሱ ተራራ ግርጌ ራያዎች በጋራ ደምቀዋል። ናፍቆታቸውን እየተወጡ ነው።

(ታርቆ ክንዴ – አብመድ)

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

To Top