Connect with us

ኢቲቪ እና ዋልታ የመታፈን (ጃሚንግ) አደጋ ገጠማቸው

ኢቲቪ እና ዋልታ የመታፈን (ጃሚንግ) አደጋ ገጠማቸው
Photo: ሸገር

ዜና

ኢቲቪ እና ዋልታ የመታፈን (ጃሚንግ) አደጋ ገጠማቸው

ኢቲቪ እና ዋልታ የመታፈን (ጃሚንግ) አደጋ ገጠማቸው

 

በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) እና በዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት በሳተላይት የሚተላለፉት ETV News HD እና Walta TV የሽበባ ወይም የጃሚንግ ጥቃት እንደተካሄደባቸው ሸገር ሰምቷል፡፡

በጣቢያዎቹ ላይ ለተፈፀመው የሽበባ ጥቃት በይፋ ኃላፊነት የወሰደ አካል ባይኖርም፣ የሕወሓት እጅ ሊኖርበት ይችላል የሚል ግምት እንዳለ ሰምተናል፡፡

የሽበባ ወይም የጃሚንግ ጥቃቱ በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በSD (ወይም ስታንዳርድ ዴፊኒሽን) የሚያሰራጨውን የሳተላይት ስርጭት ዒላማ ያደረገ ነበር፡፡

ጥቃቱ ለሦስት ቀናት፣ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያው በSD የሚያሰራጨው መረጃ ለሕዝብ እንዳይደርስ አድርጎ እንደነበር ሸገር ሰምቷል፡፡

ይህ ችግር አሁን የተፈታ ሲኾን፣ ሐሙስ ከቀኑ 7፡00 ገደማ ጀምሮ ጣቢያው በHD (High Definition) የሚያሠራጨው ETV News HD የሽበባ ጥቃት ተፈጽሞበት እንደነበር ታውቋል፡፡ የሽበባ ጥቃቱ መፈፀሙን የነገሩን አንድ የኢቢሲ የሥራ ኃላፊ አሁን ችግሩ ሙሉ በሙሉ ተቀርፎ፣ ስርጭቱ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በHD የሚያስተላልፈው ስርጭት ሐሙስ አመሻሹ ላይ ዳግም ወደ አየር ተመልሷል፡፡ 

አሁን የኢቢሲ ስርጭቶች በሁለቱም አማራጮች ማለትም በSD እና በHD መሰራጨት የቀጠሉ ሲኾን፣ መሰል ችግር ዳግም ቢከሰት ጣቢያው የሚያስተላልፋቸው ስርጭቶች ያለችግር እንዲቀጥሉ የሚያደርግ ሥራ መሠራቱን ሸገር ከጣቢያው የሥራ ኃላፊ ሰምቷል፡፡  

በተመሳሳይ፣ በዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት በሳተላይት የሚተላለፈው የWalta TV ስርጭትም፣ በተካሄደበት የሽበባ ጥቃት ሐሙስ ዕለት ከምሽቱ 12፡00 ገደማ ጀምሮ ለተወሰኑ ሰዓታት ከአየር ላይ ጠፍቶ እንደቆየ ታውቋል፡፡ 

ይሁንና ድርጅቱ ዋልታ ቲቪን ከሰዓታት በኋላ መልሶ አየር ላይ ማስገኘት ችሏል፡፡ ጣቢያው ዳግም መሰል ጥቃት ቢፈፀም፣ ስርጭቱ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ማድረግ የሚችልበትን መላ መዘየዱንም ሸገር ሰምቷል፡፡ 

ምናልባት ስርጭቱ ምስልን ሳይጨምር ድምጽ ብቻ የሚሰማበት ከሆነ፣ ተጠቃሚዎች እንደ አዲስ የቻናል ፍለጋ በማድረግ ችግሩን ማስወገድ እንደሚችሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያለው ምንጭ ለሸገር ነግሯል፡፡

ለተፈፀመው የሽበባ ጥቃት በይፋ ኃላፊነቱን የወሰደ አካል ባይኖርም፣ ሸገር ያነጋገራቸው አንድ የጋዜጠኝነት መምህር፣ ጥቃቱ በሕወሓት የተፈፀመ ሊሆን ይችላል ብለው እንደሚገምቱ ነግረውናል፡፡ 

ስሜ አይጠቀስ ያሉን እኒሁ ምሁር፣ በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ በሀገር ክህደት የሚያስጠይቅ ወንጀል መፈፀሙን የተናገረው ሕወሓት፣ በትግራይም ሆነ በሌሎች ክልሎች ያለው ሕዝብ በጉዳዩ ዙርያ እውነተኛ መረጃ የሚያገኝበትን ዕድል ለመዝጋት መሞከሩ ብዙ ሊደንቅ አይገባም ብለዋል፡፡ 

ሕወሓትና ደጋፊዎቹ በአሁኑ ሰዓት መጠነ ሰፊ የሐሰት መረጃ የማሰራጨት ዘመቻ ውስጥ መግባታቸው በግልጽ እየታየ ነው ያሉት እኒሁ ምሁር፣ ለዚህም በሰሜን እዝ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ መከላከያ ሠራዊት ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ከጀመረ በኋላ በሐሳዊ ምስሎች ተደግፈው በማኅበራዊ ሚዲያ የተሰራጩትን የሐሰት መረጃዎች ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ 

የሕወሓት የፕሮፖጋንዳ ሰዎች ሰሞኑን በማኅበራዊ ትስስር ገፆች ላይ፣ ሕወሓት ሩስያ ሰራሹን S-400 እጅግ ዘመናዊ የአየር መቃወሚያ ታጥቋል በማለት ያሰራጩት በፎቶሾፕ በተቀናበረ ምስል የታጀበ የሐሰት መረጃ በቢቢሲ መጋለጡን እኒሁ ምሁር አስታውሰዋል፡፡ 

ባለፈው ሳምንት የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ጌታቸው ረዳ ‹‹የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጀቶችን በአየር መቃወሚያ መትተን ጥለናል›› ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡ ይህን የአቶ ጌታቸው ንግግር ተከትሎ፣ተከስክሶ በመቃጠል ላይ ያለ የጦር አውሮፕላን ምስል በማኅበራዊ ሚዲያ በስፋት ተሰራጨ፡፡ ከምስሉ ጋር፣ ‹‹በትግራይ የአየር ጥቃት ሲፈጽም ተመትቶ የወደቀው አንደኛው የጦር ጀት እነሆ›› የሚል ማብራሪያ ተጽፎበት ነበር፡፡

በብዛት የተሰራጨው ይህ ምስል ግን ከ2 ዓመታት በፊት፣ በሐምሌ 2010 የኢራኑ የሳተላይት ቴሌቪዥን ፕሬስ ቲቪ ለዕይታ ያበቃው፣ የመን ውስጥ ተመትቶ የወደቀ የሳዑዲ አረቢያ የጦር ጀት እንደሆነ ቢቢሲ አጋልጧል፡፡

በተጨማሪም የሕወሓት አቃብያነ ፕሮፖጋንዳ የበርካታ ሰዎች አስከሬን በጥቁር ላስቲክ ተጠቅልሎ ከሚታይበት ምስል ስር፣ ‹‹ትግራይ ድንበር አቅራቢያ በልዩ ኃይላችን የተገደሉ የአማራ ክልል ወታደሮች›› የሚል ማብራሪያ ጽፈው ነበር፡፡ ነገር ግን፣ በድረ ገጽ ለሚሰራጩ ወሬዎች ፍፁም እንግዳ የሆነን ሰው ካልሆነ በቀር፣ምስሉ የማሳሳት አቅሙ በጣም ደካማ ነበር፡፡ በእርግጥም ምስሉ ከሁለት ዓመት በፊት ቢሾፍቱ አቅራቢያ በተከሰከሰውና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት በሆነው 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች አስከሬን ከተሰበሰበ በኋላ የተነሳ ነበር፡፡

ሸገር ያነጋገራቸው የጋዜጠኝነት መምህርም “እንደዚህ ያሉ የለየላቸው የሐሰት መረጃዎችን በማሰራጨት የተጠመደ ቡድን፣ በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ስለተፈፀመው ጥቃት እና እርሱን ተከትሎ እየተካሄደ ስላለው ወታደራዊ ዘመቻ እውነተኛ መረጃ ይቀርብባቸዋል ብሎ የሚሰጋባቸውን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለመሸበብ መሞከሩ ሊያስገርም አይገባም” ብለዋል፡፡

(ሸገር ~ዘከሪያ መሐመድ)

 

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top