Connect with us

ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኾነው ተሾሙ

ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኾነው ተሾሙ
ሐራ ተዋህዶ

ዜና

ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኾነው ተሾሙ

ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኾነው ተሾሙ

~  የሌሎች አራት ዋና ሓላፊዎች ዝውውርም ተደረገ፣

  • ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው መሠረት በቅዱስ ፓትርያርኩ ተሹመው ተመድበዋል፤
  • የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የ5 መምሪያዎች ዋና ሓላፊዎች ዝውውር ተደረገ፤
  • ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ወደ መሪ ዕቅድ ትግበራ ጽ/ቤት ተዛውረው ይሠራሉ፤

ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኾነው እንዲሠሩ ተሾሙ፡፡

ቋሚ ሲኖዶስ፣ ረቡዕ፣ ኅዳር 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሔደው ሳምንታዊ ስብሰባ ላይ፣ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ያሬድ በዕጩነት ቀርበው ከተመረጡ በኋላ፣ በቅዱስ ፓትርያርኩ በተፈረመ ደብዳቤ በምክትል ሥራ አስኪያጅነት ተሹመዋል፡፡

የሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን ሹመት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ በጥቅምቱ የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባው፣ “የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ነን” በማለታቸው ሥልጣነ ክህነታቸው ታግዶ ከነበሩት ጋራ በተደረገው ውይይት መግባባት ላይ በመደረሱ፣ ክህነታቸው የተያዘባቸው ካህናት ሥልጣነ ክህነታቸው ተለቆላቸው በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ የሥራ መደብ ተሰጥቷቸው እንዲያገለግሉ የወሰነውን መሠረት የተሰጠ መኾኑ ታውቋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አህጉረ ስብከት፣ በአስተዳደር ችግር እና በቋንቋ አገልግሎት ያጋጠመውን የሐዋርያዊ ተልእኮ አፈጻጸም መዳከም፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሥር በሚቋቋም ጠንካራ አካል በኩል በአንድነት ለመፍታት ተስማምተው ወደ አሐቲ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር የተመለሱት ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን፣ ቀደም ሲል በዚኹ የሓላፊነት ደረጃ በመሥራታቸው ለሹመቱ እንግዳ አይደሉም፡፡

ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ እና የምዕራብ ጎንደር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ወቅት፣ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ፣ ለአራት ዓመት ከኹለት ወራት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ በመኾን ሠርተዋል፡፡

ከዚያም ጋራ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ሓላፊ፣ በቤቶች እና ሕንፃዎች አስተዳደር እና ልማት ድርጅት፣ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዋና ዲን፣ የሕግ አገልግሎት መምሪያ ዋና አማካሪ እንዲሁም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኾነው ሠርተዋል፡፡ በትምህርት ዝግጅታቸውም፣ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ እና በንግድ አስተዳደር ኹለተኛ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያንን የሥራ አስፈጻሚነት እና የአስተዳደር ተግባራት በከፍተኛ ደረጃ ለማከናወን ሥልጣን ለተሰጠው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በምክትል ሥራ አስኪያጅነት የሚሾም ሓላፊ፥ ሥልጣነ ክህነት ያለው ኾኖ፣ በነገረ እግዚአብሔር ወይም በአንድ የጉባኤ ትምህርት የተመረቀ፣ በቂ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ያለውና በአስተዳደር ችሎታው ብቁ መኾን እንዳለበት፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጽ 44 ንኡስ አንቀጽ (4) ተደንግጓል፤ ለምርጫውም፣ ተወዳዳሪ ዕጩዎች መቅረብ እንዳለባቸው በድንጋጌው ተመላክቷል፤ የአገልግሎት ዘመኑም፣ የጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የሥራ ዘመን ማለትም ለሦስት ዓመታት እንደኾነ አስፍሯል፡፡

በሌላ በኩል፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኾነው የቆዩት ርእሰ ደብር መሐሪ ኃይሉ፣ ወደ ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ተዛውረው በዋና ሥራ አስኪያጅነት እንዲሠሩ ተመድበዋል፡፡ የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኾነው ሲሠሩ የቆዩት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ ወደ መሪ ዕቅድ ትግበራ ጽ/ቤት ዋና ሓላፊነት ተዛውረው እንዲሠሩ ተመድበዋል፡፡

የመሪ ዕቅድ ጽ/ቤትን ለማደራጀት እና የትግበራ ፕሮጀክቱን ለማስጀመር፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ የ2.5 ሚሊዮን ብር በጀት አጽድቋል፡፡ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ለ39ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ባቀረቡት ሪፖርት፣ ጽ/ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ በቋሚ ሲኖዶስ እንዲጸድቅለት መደረጉንና ሥራውን የሚመራ እና የሚያስተባብር ምክትል መምሪያ ሓላፊ እንዲመደብለት ተደርጎ ሥራውን ማከናወን መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡ 

ትላንት በዋና ሓላፊነት ከተመደቡት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ቀደም ሲል የትግበራ ጽ/ቤቱ ምክትል ሓላፊ ኾነው የተመደቡት፣ የቀድሞው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር ይቅር ባይ እንዳለ ናቸው፡፡ 

ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም. ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ጽ/ቤቱ፣ ከመሪ ዕቅድ ክለሳው እስከ ትግበራው ሥራውን የሚያከናውኑ ባለሞያዎችን በአግባቡ ቀጥሮ ማሠራት ይጠበቅበታል፡፡

በተጨማሪ የዝውውር ዜና፣ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ሓላፊ ኾነው ሲሠሩ የቆዩት መጋቤ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ፣ ወደ ሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ተዛውረው በዋና ሓላፊነት እንዲሠሩ ተመድበዋል፡፡

የማደራጃ መምሪያው ዋና ሓላፊ ኾነው ሲሠሩ የቆዩት መጋቤ ሐዲስ ሐዋዘ ብርሃን ጫኔ ደግሞ፣ ወደ ስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ተዛውረው በዋና ሓላፊነት እንዲሠሩ መመደባቸው ተገልጿል፡፡

የዋና ሓላፊዎቹ መዛወር ዓላማ፣ “ሥራንና ሠራተኛን ለማገናኘት ሲባል” እንደኾነ፣ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ተፈርሞ በየስማቸው ከደረሳቸው ደብዳቤ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ድንጋጌ አንቀጽ 42 ንኡስ አንቀጽ 6 መሠረት፣ የመምሪያዎች እና የድርጅቶች ሓላፊዎች የሥራ ዝውውር እና ዕድገት፣ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አቅራቢነት ተጠንቶ ቅዱስ ፓትርያርኩ ሲስማማበት ተፈጻሚ እንዲኾን ይደረጋል፡፡(ሐራ ተዋህዶ)

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top