Connect with us

በኔትወርክ የተሳሰሩ የማፍያ ቡድኖችን ማን ይታደገን?

በኔትወርክ የተሳሰሩ የማፍያ ቡድኖችን ማን ይታደገን?
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

በኔትወርክ የተሳሰሩ የማፍያ ቡድኖችን ማን ይታደገን?

በኔትወርክ የተሳሰሩ የማፍያ ቡድኖችን ማን ይታደገን?

(ከተቆርቋሪ የጤና ሙያተኞች)

 ክብርት ከንቲባ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተሾሙ ገና የወራት እድሜ ያስቆጠሩ ቢሆንም ከተሾሙበት ዕለት ጀምሮ እያበረከቱት ላለው ሕዝባዊ አስተዋጽኦ ያለንን አክብሮት መግለጽን እናስቀድማለን። እኛ በጤናው ዘርፍ የተሰማራን ተቆርቋሪ ሙያተኞች፣ እንደ ከተማይቱ ነዋሪና የጤና ባለሙያ፣ ለሀገራችን ዕድገትና ብልጽግና የበኩላችንን አስተዋጽኦ እያበረከትን እንገኛለን፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እስከ ታች ባሉ መዋቅሮች ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተሰሩ የመዋቅር ማሻሻያ ባለፉት ዓመታት ህብረተሰቡን ተደራጅተው ሲዘርፉና ሲያዘርፉ የነበሩ አካላት ከሞላ ጎደል  የወሳኝነት ሚናቸውን ተነጥቀው  ያፈገፈጉ መሆኑ  ይታወቃል፡፡

ሆኖም አለማቀፋዊ ወረርሽኝ የሆነው ኮቪድ-19 በሀገራችን በመከሰቱ ምክንያት የለውጡ መንግስትና ህዝብ በአመዛኙ ትኩረቱን በሽታውን መከላከልና አክሞ ማዳን ላይ በማድረጉ፣ ይህ ክፍተት መንግስት ጉያ ስር ላሉ ሌቦች አመቺ መደላድልን ፈጥሯል፡፡

ላለፉት በርካታ ዓመታት ተደራጅተው ሲበዘብዙ የነበሩ ስነምግባር የጎደላቸው አንዳንድ የቀድሞ አመራሮች፣ በዚህ ወቅት አጋጣሚውን እንደማይገኝ እድል በመጠቀም እንደገና የከተማችንን መንግስታዊ ተቋማት በመቆጣጠር ሂደት ላይ መሆናቸውን እየታዘብን እንገኛለን፡፡

በዚህ አካሄድ ከቀጠሉ ከዚህ ቀደም በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ  ያደራጇቸውን ሴሎችና  ለውጡ የመጣባቸው ግን ከስልጣናቸው ያልተነኩ የእነርሱ የጥቅም ተጋሪዎች የሆኑትን  በመጠቀም ያጡትን የሴክተሮች የከፍተኛ የአመራርነት ሚናን መልሶ በመቆጣጠር፣ ለውጡንና ለውጡን ተከትሎ የመጡትን አበረታች ጅምሮች ወደ መቀልበስ ተግባር እየተገባ መሆኑን በማየታችን፣ ይህንን ግልጽ ደብዳቤ ለመጻፍ ተገደናል፡፡ 

ክብርት ከንቲባ፤ እርስዎም ባቀረብነው አቤቱታ ላይ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ እንደሚያደርጉ እናምናለን፡፡

ክብርት ከንቲባ፣ ህዝባችን የለውጡን ፋይዳና ቀጣይነት ከሚለካባቸው መንገዶች አንዱና ዋነኛው፣ ባለፈው ስርዓት ውስጥ አምርሮ ሲታገላቸውና ሲያነውራቸው የነበሩ በህብረተሰቡ፤ በሴክተር መስርያ ቤቶችና በመሳሰሉት ውስጥ የሚታወቁ ሙሰኞችና የተደራጁ የማፍያ ቡድኖች ላይ በመጣው ለውጥና በተወሰደው እርምጃ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡

 ሆኖም ግን እነዚህ ህብረተሰቡ ያነወራቸውና ያስወገዳቸው ሙሰኞች በአንዳንድ የአዲስ አበባ የመንግስት ሴክተር መስርያቤቶች ወደነበሩበት የአመራርና የውሳኔ ሰጭነት ሚና እየተመለሱ መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

ይህን እውነታ በግልጽ ለማስረዳት ከዚህ በፊት  የአዲስ አበባን ጤና ቢሮ ተቆጣጥሮ ሲዘርፍ የነበረ የማፍያ ቡድን ያደረሳቸውን ጉዳትና በአሁን ወቅት ወደ ቀድሞ የስልጣን እርከንና የዝርፊያ ሚናቸው ኔትወርካቸውን በመጠቀም እንዴት እየተመለሱ እንዳሉ በማሳያነት እንደሚከተለው በማስረጃ በማስደገፍ እናቀርባለን፡፡

ከሁሉ አስቀድሞ ከዚህ ቀደም ከማፍያው ቡድን ጋር በነበረ አሰቃቂ ግብግብ፣ ከግል ጥቅምና ስልጣን በፊት የህብረተሰብን ጥቅም በማስቀደም፣ በተለያዩ እርከኖች ላይ ሆናችሁ የታገላችሁ ወገኖች፣ ለከፈላችሁት መስዋዕትነት በጤና ባለሙያዎች ስም እናመሰግናለን፡፡

በተጨማሪም  ለሃቅ፣ ፍትህና ርዕትህ ስትታገሉ  ለነበራችሁና በዚሁ ኔትዎርክ ቡድን  በራሳችሁና ቤተሰባችሁ ላይ  የተለያዩ ጥቃቶችና አደጋዎች ማለትም ከስራ መባረር፣ ከኃላፊነት መነሳት፣  የቤተሰብ መበተን፣ ለከፋ የጤና መታወክ መዳረግ፣ ለስም መጥፋትና ለመሳሰሉት ለተዳረጋችሁ ሁሉ፣ ያልተዘመረላችሁ ጀግኖች መሆናችሁን እንገልጻለን፡፡ ነገር ግን ሲደረግ የነበረው ትግል ከለውጡ ጋር ከሞላ ጎደል ውጤት አሳይቶ የነበረ ቢመስልም፣ በአሁኑ ወቅት የማፍያው ቡድን ወደ ቀድሞ ቦታው እየተመለሰ በመሆኑ ይህንን ለመጻፍ ተገደናል፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት ምን ዓይነት ሙስናና ብልሹ አሰራር ሰፍኖ ስለመቆየቱ ለጉዳዩ አዲስ ለሆኑ ወገኖችና ለክቡር ከንቲባ ጠቅላላ ግንዛቤ እንዲረዳ ያህል፣ በተለያዩ ጊዜያት በመገናኛ ብዙኃን የተዘገቡትን እንደ አብነት ከዚህ በታች ሊንካቸውን አስቀምጠናል፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአይናችን ፕሮግራም፣ ርዕስ፡- ፈውስ የሚያሻው ፈዋሽ፤  ነሐሴ 11/2010 (https://youtu.be/u_exk0y5ATw)

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አሳሽ ፕሮግራም፣ ርዕስ፡- ተጠቃሚው ማነው? (https://youtu.be/6RxwfR9gB2w)

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (https://youtu.be/HDiE0fYMYvo)

በተለያዩ ወቅቶች ከወጡ ጋዜጦች ውስጥ አዲስ አድማስ፣ ሪፖርተር (WWW.ethiopianreporter.com/article/18510) 5 April 2000፤ ወዘተ

በተለያዩ ወቅቶች በሴክተሩ ሰራተኞች ለፌዴራል የስነምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን የቀረቡ  ሰነዶች፣

በተለያዩ ወቅቶች የተገኙ የኦዲት ግኝቶች፣

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኤፍኤም ራዲዮ፣ ስለ ከነማ መደብር የተላለፈ፣ ሐምሌ/ነሐሴ 2008

የተቋሙ ሰራተኞች ምልከታ፣

በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የታዩ ብልሽቶች

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴክተር መስሪያ ቤቶች ከዚህ በፊት አንዳንድ መሪዎች የሚሾሙት ባላቸው እውቀትና ችሎታ ሳይሆን ለአገዛዙ ባላቸው ታማኝነትና በ;እከክልኝ ልከክህ# ትስስር መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ አሰራር መሰረት በጤና ቢሮ አመራርነት ተሹመው፣ በአሰቃቂ መረብ ቢሮውን በመተብተብ ተቋሙን  ሲዘርፋና ሲያዘርፉ  የኖሩ፣  በአሁን ሰዓት ለውጡ የድጋሚ እድል ከሰጣቸው አመራሮች ጋር በመቀናጀት፣ በቅርቡ በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ውስጥ ከሚገኙ ኃላፊዎች አንዱ ሆነው ተሹመዋል፡፡

በህዝብና በጤና ባለሙያዎች ቆራጥ ትግል፣ በጎደፈ ስነምግባራቸው ምክንያት ከስልጣናቸው እንዲሻሩ የተደረጉ አመራሮች፣ ከዛሬ ነገ ለፈጸሟቸው ጥፋቶች ለፍትህ እንደሚቀርቡ ሲጠበቁ፣ ጭርሱኑ ;ጥፋታችን ተረስቶልናል# በሚል እሳቤ፣ አድብቶ ሲጠባበቅ የቆየውን ኔትዎርካቸውን ተጠቅመው መሾማቸው፣ የለውጡ አንድ ተግዳሮት አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡

ክብርት ከንቲባ፤ ሹመቱን አስቂኝና አስገራሚ የሚያደርገው በኢትዮጵያ ካሉ የመንግስት ሴክተር መስሪያቤቶች ብቁና የተደራጀ የተማረ ማህበረሰብ ገንብቶታል በሚባለውና የተማሩ ኃይሎችን ለሀገራችን በማመንጨት በሚታወቀው ትምህርት ቢሮ ውስጥ እንደዚህ አይነት ግለሰቦች በፎርጅድ የትምህርት ማስረጃ (የአንድ አመት የስልጠና ሰርተፍኬት ብቻ ያላቸውና ምንም አይነት ተጨማሪ የትምህርት ዝግጅት የሌላቸው፤ ማስተርስ አለኝ የሚሉት ውሸትና ይህም ከዚህ በፊት የተረጋገጠ መሆኑ ይሰመርበት)  የአመራርነትን ቦታ እንዲይዙ መደረጉ ነው፡፡

የመደመር አስተሳሰብ በተለይ ለትምህርት ካለው ከፍተኛ ትኩረት አንጻር ስናየው፤ ይህ ድርጊታቸው የሚያሳየው  ለውጡን ሆን ተብሎ የማቀጨጭና የማዳከም ብሎም ለውጡን እስከ ታችኛው መዋቅር እንዳይደርስ በህቡዕ ተደራጅተው እየሰሩ መሆኑንና አዲሱን ሲስተምን በመቀልበስ እንደተለመደው በቁጥጥራቸው ስር ወደ ማድረግ እየተሸጋገሩ መሆኑን  ነው፡፡ ሹመቱ ለሀገራችን፣ ለከተማችን ህዝብ፣ ለትውልድና ለዚህ አንጋፋና በምሁራን ለተሞላ ትምህርት ቢሮና ሰራተኞች የሚያስተላልፈው መልዕክት አዎንታዊ አይደለም፡፡ በፍጥነት ተጣርቶ እርምት እንዲወሰድና ለውጡን የመታደግ ስራ እንዲሰራ ስንል እንጠይቃለን።

ቡድኑ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮችን ስም ለህገወጥ ተግባሩ ማስፈጸሚያነት መጠቀሙ፣ ከለውጡ በፊት፤ “ከከንቲባው ጋር ጓደኛ ነኝ፤ ምክትል ከንቲባው አማካሪዬ ነው” በሚል ሰውን በማስፈራራትና በማሸማቀቅ፣ በኔትወርክ የተሳሰረ ዝርፊያ ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ መኖራቸው እሙን ነዉ፡፡

አሁንም ከለውጡ በኋላ፤ በተለይ  የእርስዎ ጽ/ቤት ሃላፊ አድርገው የሾሙትን ግለሰብ ስም በመጥቀስና የተሾሙት ግለሰብ ከለውጡ በፊት የጻፉትን የሥነ ግጥም መጽሐፍ ለጤናው ሴክተር ሰራተኞች በግድ እንዲገዙ በማድረግ፣ የዋሉላቸውን ውለታ በማስታወስ፣ ባለፉት ጊዜያት አምርረው ሲታገሉዋቸው የነበሩ ግለሰቦችን በለመዱት መንገድ እያስፈራሩ ነው፡፡ እኚሁ ግለሰብ የተዋለላቸዉን ውለታ በመቁጠርም ዳግም በጤናዉ ሴክተር ላይ እንደሚያሾሟቸው በጤናው ሴክተር ባደራጁት ኔትወርክ በስፋት እየተነገረ ሲሆን የተለያዩ ዛቻዎችና ማሸማቀቂያዎችም እየደረሱ ይገኛሉ፡፡

ከማፊያ ቡድኑ በህብረተሰቡ ላይ ያነጣጠሩ ምዝበራዎች ጥቂቶቹ

በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ የከነማ መድሀኒት መደብሮች ለህብረተሰቡ ጥራት ያላቸዉ መድሃኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ተልዕኮ ያላቸው መሆኑ የሚታወቅ ነው።

የቡድኑ አባላት የቦርድ ሰብሳቢና አባል በሆኑበት በነዚያ የከነማ ፋርማሲ የዝርፊያ ዓመታት የደረሱ ጉዳቶች በተደጋጋሚ ኮሚቴ ተዋቅሮ የተጠና ነበር፡፡ የጥናቶቹ ግኝቶች እንደሚያሳዩት፤ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውና ምንጫቸው ያልታወቁ  መድሃኒቶች በሽያጭ ላይ ይገኙ እንደነበር ነው። 

የቡድኑ አባላት ስልጣናቸውን በመጠቀም አብዛኛው መድሀኒት መጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸዉንና ሊያልፍባቸው ሲል ያለ ጨረታ ከግል የመድሀኒት መደብሮች እንዲገዙ በማድረግ፣ የከነማ መድሀኒት መደብሮች ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድሀኒቶች ማራገፊያ ተቋም አድርገዋቸው ነበር፡፡ በአጠቃላይ ለከተማው ህዝብ የተበላሹ መድሀኒቶች  እንዲሸጡ በማድረግ፣ ይቅር የማይባል ከፍተኛ ወንጀልም ፈጽመዋል፡፡

ይህ ድርጊት ከሕግ ብቻ ሳይሆን ከሞራልም አንጻር የቡድኑን ማንነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶችና የተደረሱባቸውን ግኝቶች በተመለከተ ከጤና ቢሮና ከጸረ ሙስና ተቋም ማስረጃዎችን ማግኘት ይቻላል።  

በተጨማሪም ለአዲስ አበባ ኦዲተር ቢሮ፣ በከነማ ሰራተኞች የገቡ ማስረጃዎችም ይገኛሉ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኤፍኤም ራዲዮ፣ ስለ ከነማ መድሀኒት መደብር፣ በነሐሴ ወር 2008 በጋዜጠኛ አሻግሪ የተላለፈ የሰራተኞች ምስክርነትም ከማህደር በማስወጣት ማዳመጥ ይቻላል፡፡

ቡድኑ የከተማውን ጤና ቢሮ በተቆጣጠረበት ወቅት አባላቱን በተለያዩ የመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ የአመራርነትን ሚና በመስጠት ከላይ በከነማ መድሂኒት መደብሮች ላይ ሲፈጽም የነበረውን ዝርፊያ ወደ ሆስፒታሎቹ በማዞር አስፋፍቶት ነበር፡፡ የተበላሹ መድሀኒቶችን ወደ ሆስፒታሎች ማስገባት ብቻም ሳይሆን መድሀኒቶቹን ከሚገባቸው ዋጋ በላይ በመክፈልና በሆስፒታሎቹ መድሀኒት መደብሮች፣ መድሀኒቶቹ ከግል የመድሀኒት መሸጫዎች አንጻር ሲለካ እንኳ በ4 እና 5 እጥፍ የተወደደና ልዩነት እንዲኖረው በማድረግ ዝርፍያ ሲፈጽሙ ኖረዋል፡፡ በዚህም ድርጊታቸው የተንገፈገፉ የየሆስፒታሎቹ ሰራተኞች፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ;አይናችን# እና ;አሳሽ# በተሰኙ ፕሮግራሞች፣ ሀቁን የማጋለጥ ስራ መሥራታቸው ይታወሳል::

(ይህን ማስረጃ በቀጣዩ ሊንክ ማየት ይቻላል https://youtu.be/HDiE0fYMYvo, https://youtu.be/6RxwfR9gB2w እና https://youtu.be/u_exk0y5ATw)

በወቅቱ በቢሮው ስር ከስድስት ቢሊየን ብር በላይ በጀት የተያዘላቸው የሆስፒታልና የጤና ጣቢያ ግንባታዎች ተግባር መኖሩ ይታወሳል። በሀገራችን ደረጃ ግንባታን በተመለከተ የታዩ ሌብነቶች በቡድኑ ተፈጽመዋል፡፡ በተጨማሪም በወቅቱ የጤና ተቋማትን ለማጠናከር በብዙ ሚሊየን ብሮች የህክምና  መሳሪያዎች ግዥ ከተፈጸመ በኋላ፣ ለታቀደላቸው ተቋማት ሳይደርሱ የውሀ ሽታ ሆነው ቀርተዋል፡፡

ክብርት ከንቲባ፤ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ውስጥ ዓመታዊ ወጪው ከ100 ሚሊየን ብሮች በላይ  የሆነ በውጪ መንግስት የሚደገፍ ፕሮጀክት አለ፡፡ የከተማውን የጤና ሙያተኛ ማሰልጠንና አቅም መገንባት የፕሮጀክቱ ዋነኛ አላማው ሲሆን ገንዘቡም ለዚሁ ዓላማ ማስፈጸሚያነት እንዲውል ታስቦ የተመደበ ነው፡፡ 

ነገር ግን ይሄው ቡድን ይህንን ገንዘብ ከቡድኑ ጋር ግንኙነት ላለው የግል ማህበር እንዲዘዋወር በማድረግና የቢሮው ስልጠናዎችና ስብሰባዎች በእነሱ ጓደኞች ህንጻ ላይ እንዲካሄድ በማመቻቸት አለአግባብ  ከፍተኛ ሚሊየን ብሮች እንዲባክኑ ተደርገዋል፡፡ ይህ ተግባር በቅርቡ በአዲሱ አመራር ተደርሶበት እንዲቋረጥ የተደረገ ቢሆንም፣ ከህግ አንጻር ግን የተወሰደ እርምጃ አለመኖሩ ለተደራጁት ሌቦች የልብ ልብ ሰጥቷል፡፡

ለከተማችን አዲስ አበባ በውጪ መንግስታትና በተለያዩ ተራድኦ ድርጅቶች አማካይነት በነጻ ሲለገሱ የነበሩ ኮንደሞችን ልክ በኤች አይቪ ጽ/ቤት እንደተገዙ በማስመሰል ከመንግስት ካዝና ብር ወጪ በማድረግና ኮንደሙም ገቢ ሲደረግ  ተገዝቶ እንደመጣ  ገቢ እና ወጪ ደረሰኞችን በማዘጋጀት ብዙ ሚሊዮን ብሮች ሲዘርፉ ቆይተዋል። በተጨማሪም ከአንዳንድ በኤችአይቪ ላይ ከሚሰሩ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ ገንዘብ ተመዝብሯል (ይህም ለጸረ ሙስና ኮሚሽን በገባው ሰነድ ላይ በግልጽ ይታያል)።

ከላይ የተገለጹት ዝርፊያዎች ከብዙ በጥቂቱ እንደ ማሣያ የቀረቡ መሆኑ ይታወቅ፡፡

ከገንዘብ ባሻገር የቢሮውን የሲቪል ሰርቪስ አደረጃጀት ተገቢው የሙያ ክህሎት በሌላቸው የቡድኑ አባላት ሲሞሉት በመክረማቸው ሳቢያ ቢሮው ዋናውን ተልእኮ ለማሳካት ከፍተኛ የሆነ የአቅም ማነስ ተስተውሎበታል፡፡ (ይህንን በተገቢው ለመረዳት ሊንኩን ይጠቀሙ www.ethiopianreporter.com/article/18510)

በጤና ሚኒስቴር ውስጥ ቡድኑ

የዘረጋው መረብ 

ሀገራችን ኢትዮጵያ በሰለጠኑበት የጤና ሙያ ህብረተሰባቸውን በማገልገል እስከ ህይወት ፍፃሜ ድረስ ተጋድሎ የፈጸሙ ቀናና ታማኝ የጤና ሙያተኞች ያፈራች ሀገር ናት።  ይህም በክፍለ ዘመን ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ  በግልጽ እየታየ ይገኛል። በዚህ አጋጣሚ በሀገራችን ይህንን ወረርሽኝ በመከላከል ተግባር ህይወታቸውን ለከፈሉ (እንደ ሲኒየር ፋርማሲስት አልማዝ ምትኩና ነርስ አንበሳ አውድም ዮሀንስ ላሉ) ባለሙያዎች ነብስ ይማርልን እያልን፣ ያለንን ከፍተኛ አክብሮት ልንገልጽ  እንወዳለን፡፡

ኮቪድን ለመከላከል የጤና ባለሙያዎች እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ የጠየቀ ተጋድሎ ሲያደርጉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በዘርፉ በአመራርነት ተቀምጠው የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ መኖራቸው አሳዛኝ ነው፡፡ በፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ውስጥ የኮቪድ ወረርሽኝን የህክምና አገልግሎት እንዲያስተባብሩ ኃላፊነት ከተሰጣቸው ዳሬክቶሬቶች መካከል አንዳንዶቹ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ችላ ብለው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ አፍሪካ በተባለ የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመደበኛ መርሀ ግብር ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡ 

ትምህርት መማር በጎና የሚበረታታ ሆኖ ሳለ፣ በዚህ ፈታኝ ወቅት ሁሉም  ሙያተኛ የኮቪድን በሽታ ለመቆጣጠር እርብርብ ሲያደርግ፣ እነዚህ ግለሰቦች ግን በቴሊቪዥንና በስብሰባ ፊታቸውን አሳይተው፣ የመንግስትን የስራ ሰዓት የሚያሳልፉት በስራ ገበታቸው ላይ ሳይሆን ከትምህርታቸው ጋር የተያያዙ ስራዎችን  በማከናወን መሆኑ ያስገርማል፡፡

በተጨማሪም በሲቪል ሰርቪሱ ህግ መሰረት፣ ማንኛውም ሰራተኛ በስራ ሰዓት በስራው ገበታ ላይ መገኘት ግዴታው ነው፡፡ እነዚህ ቡድኖች ግን የሚማሩት የመንግስትና የህዝብ የስራ ሰዓትን በመጠቀም ሲሆን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም በቀን መርሀ ግብር በመንግስትና በህዝብ የስራ ሰዓት የመማር

ፍቃድ ያልሰጣቸው መሆኑ ይታወቃል። ይህም በሲቪል ሰርቪሱ ህግ መሰረት ወንጀልና የሚያስቀጣ ተግባር ነው፡፡

በፌደራል ጤና ጥበቃ ውስጥ ያለው የቡድኑ ቅርንጫፍ መነሻው ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሲሆን አሁን ያለበትን ቦታ የተቆጣጠረው ህጋዊ አሰራሮችን በመሻርና የኔትወርኩን ጉልበት በመጠቀም ነው፡፡ ይህ ቡድን በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ውስጥ እያለ በከተማይቱ ውስጥ የሚገኙትን የመንግስት ሆስፒታሎች፣ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥን መምራትና መቆጣጠር ኃላፊነቱ የነበረ ቢሆንም፣ በወቅቱ በሆስፒታሎቹ ውስጥ ሲፈጸሙ የነበሩ አይን ያወጡ ዝርፊያዎች በማስተባበርና ሽፋን በመስጠት፣ የድርሻቸውን የሚቀራመቱ ግለሰቦች ስብስብ ነው፡፡

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት አስፈላጊ የሆነውን የህክምና አገልግሎት የሚመሩ ግለሰብ በዚህ ደረጃ ህብረተሰብን በመናቅ የግል ጥቅማቸውን በማስቀደም፣ የመንግስትን የስራ ሰዓቶች በመሽራረፍ፣ ህዝባችን ላይ ላደረሱትና እያደረሱት ላሉት አደጋ ሊጠየቁ ይገባል፡፡ በተለይም በሙያቸው እስከ ህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ተጋድሎ ለፈጸሙትና ለመፈጸም ለተዘጋጁት ውድና ብርቅዬ የጤና ሙያተኞች ሞራልና ስነልቦና ሲባል በእነዚህ ቀልደኞች ላይ ተገቢውን አስተዳደራዊ የእርምት እርምጃ መውሰዱ ለነገ የሚባል አይሆንም፡፡

ክቡርነትዎ የምንጠይቅዎት፤

በከተማችንና በሴክተራችን እውነተኛ ለውጥ ማምጣት የምንችለው ስር ነቀል ለውጥ ሲደረግ ብቻ ነው፡፡ የቢሮውን ዋና እና ምክትል ኃላፊን ብቻ መቀየር የተሟላ ለውጥ እንደማያመጣ በቅርቡ በተደረገው ሽግሽግ ማስተዋል ችለናል፡፡

የአሁኑ የቢሮው ኃላፊዎች ወደ ቢሮው ሲመጡ፣ አዲስ ከመሆናቸው አንጻር የሚጠይቁትም የሚያማክሩትም እነዚህን በሙስናና በብልሹ አሰራር የተጨማለቁና በኔትወርክ የተሳሰሩ የቡድኑ አባላትን ነው፡፡ ይህ ቡድን ደግሞ ምንም ዓይነት አጋጣሚዎችን የግል ጥቅሙን ለማጋበስ ከመጠቀም የዘለለ ፍላጎት ያለው አይደለም።

 የቢሮውም የአደረጃጀት ለውጥ ሲደረግ፣ በቢሮው ያለው የተደራጀ ኃይል እነሱ ስለነበሩ በሚፈልገው መልኩ ተጠቅመውበታል። ይህ ሀይል አጋጣሚዎችን ከራሱ ጥቅም አንጻር ብቻ የሚያይና የመጣበትም መንገድ ከትምህርት ዝግጅትና ክህሎት አንጻር ሳይሆን ለቡድኑ ዝርፊያ ባለው ታማኝነት በመሆኑ፣ የህዝብን የጤና ጉዳይ የማስፈጸም አቅምና ዝግጁነቱ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ይሄንን ቡድን በደንብ ለሚያውቅ፣ አዲስ የመጡ አመራሮች ግንብ ሲገፉ ማየቱ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ 

እኛ የምንጠይቀው፤ ቢሮው አዲስ ጠንካራ መካከለኛ አመራሮችንና በቂ የትምህርት ዝግጅት ያላቸውን ሙያተኞች ከሆስፒታል፣ ጤና ጣቢያና ክፍለ ከተማ በማምጣት እንደ አዲስ እንዲደራጅ ነው፡፡ 

ስር ያለው ጠንካራ ሪፎርም በሴክተራችንና በከተማችን ካልተተገበረ፣ የከተማውን መልካም አስተዳደር በተለይ በጤና ሴክተሩ ላይ የማሳካቱ ጉዳይ አጠያያቂ ይሆናል፡፡ ለውጡ እንደመጣ ሸሽተው የነበሩት ቡድኖች፣ ሁኔታውን ካጤኑ በኋላ፣ አደረጃጀት ወደ መቆጣጠር መሸጋገራቸው የሚያሳየን ሀቅ ይህንኑ ነው፡፡

የትምህርት ቢሮው ጽ/ቤት የትምህርት ዝግጁቱና ብቃቱ በሌላቸው ሰዎች መመራት ስለማይገባው በአስቸኳይ ማስተካከያ ማድረግ፣ ትውልድን ከማዳን አኳያ፣ በይደር የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም ብለን እናምናለን፡፡

በቅርቡ የፌዴራል የጸረ ሙስናና የፌደራል ፖሊስ መስሪያ ቤቶች እንደገለጹት፤ በተለያዩ የመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተፈጸሙ ሌብነቶችን በመለየትና በማጣራት ለፍርድ የሚቀርቡ ይሆናል፡፡ እኛ እንደ ተቆርቋሪ የጤና ሙያተኞች፣ ይህንን ጹሁፍ ያዘጋጀነው ከላይ በተጠቀሱ መረጃና ማስረጃዎች ላይ በመንተራስ፣ ተቋማቱ ተገቢውን እርምት ወስደው፣ ስራቸውን በትክክለኛ መንገድ ይፈጽማሉ በሚል ሙሉ እምነት ነው፡፡(ምንጭ :- አዲስ አድማስ)

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top