Connect with us

ሥጋት ያጠላበት የትምህርት ዘመን

ሥጋት ያጠላበት የትምህርት ዘመን
Photo: አዲስ አድማስ

ነፃ ሃሳብ

ሥጋት ያጠላበት የትምህርት ዘመን

ሥጋት ያጠላበት የትምህርት ዘመን

  • አብዛኞቹ ት/ቤቶች የትምህርት ቢሮ ያወጣውን መመሪያ አያሟሉም
  • ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ስጋት አለባቸው።
  • ለተማሪዎች 50 ሚ. ማስክ ይመረታል ቢባልም እስከ አሁን የተመረተው ከ6 ሚ. አይበልጥም።
  • ከዚህ ጊዜ በላይ ተማሪዎቻችንን በቤት ውስጥ ማስቀመጥ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል – ጠ/ሚኒስትሩ
  • በዘንድሮ የተማሪዎች ምገባ መርሀግብር፤ 400ሺ ተማሪዎች ተካተዋል።
  • በሁሉም የመንግስት ት/ቤቶች የተማሪዎች ክሊኒክ ይቋቋማል ተብሏል።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር የተዘጉ ት/ቤቶችን ለማስከፈት እየተደረገ ያለው ዝግጅት  አጥጋቢ አለመሆኑን የሚጠቁሙት አስተያየት ሰጪዎች፤ በቂ ዝግጅት ባልተደረገበት ሁኔታ ት/ቤቶቹን መክፈት የበሽታውን ስርጭት ይበልጥ እንደሚያባብሰው ገልፀዋል።

አብዛኛዎቹ የመንግስት ት/ቤቶች የአዲስ አበባ ት/ቢሮ ያወጣውን ባለ 54 ነጥብ መስፈርት እንደማያሟሉም የተገለፀ ሲሆን። ት/ቢሮው በበኩሉ፤ ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እያጠናቀቅን ነው ብሏል።

ትምህርት ሚኒስቴር በአገሪቱ የሚገኙ ትምህርት ቤቶቸን በ 3 ደረጃዎች ለመክፈት ባስተላለፈው መመሪያ መሰረት፤ በተለያዩ የአገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች ያሉ ት/ቤቶች ጥቅምት 9 ቀን/2013 የተከፈቱ ሲሆን በክልል ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በመጪው ሰኞ ጥቅምት 16 ቀን/2013 ይከፈታሉ፡፡ የ8 12 ክፍል ተማሪዎች በአገር አቀፍ ደረጃ በመጪው ሰኞ ትምህርታቸውን እንደሚጀምሩ ተገልጿል ።

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ይከፈታሉ ተብሏል ።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላት ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፤ በከተማዋ የሚገኙ ት/ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ለመቀበል ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኙኛ አብዛኛዎቹ ት/ቤቶች በተጠቀሰው ጊዜ ዝግጅቶቻቸውን አጠናቀው ተማሪዎቻቸውን ለመቀበል እንደሚችሉ ተናግረዋል።

የትምህርት ቢሮው ትምህርት ቤቶቹን በቅርበት እየተከታተለ እንደሆነና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎች ለየትምህርት ቤቶች የማከፋፈል ስራ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በከተማዋ በሚገኙ ት/ቤቶች የተማሪዎች ክሊኒክ እንደሚቋቋምና በክፍሎቹን የፀረ ተዋስያን ኬሚካል  ርጭት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ት/ቢሮው ትምህርት ቤቶች ስራ ለማስጀመር ያስችላል በሚል ያወጣውን ባለ 54 ነጥብ መስፈርቶች የአብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች የማያሟሉ መሆኑንና በተለይም ተማሪዎቹን ርቀታቸውን ጠብቀው ለማስተማር የወጣውን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ የማይቻል እንደሆነ የግል ት/ቤት  ባለንብረቶችና ኃላፊዎች ይናገራሉ ።

ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ  አንድ የግል ት/ቤት ርዕሰ መምህር እንደገለጹት በከተማዋ የሚገኙ አብዛኞቹ የግል ትምህርት ቤቶች በአነስተኛ  ሥፍራ ላይ የተሰሩ የትምህርት ቢሮው ያወጣውን “እያንዳንዱን የመማሪያ ክፍል 40 ካሬ ሜትር መሆን ይኖርበታል” የሚለውን መመሪያ ያልተገበሩ በመሆኑ ተማሪዎችን በተባለው መሰረት ርቀታቸውን አስጠብቆ ለማስተማር እንደማይቻል ተናግረዋል።

ትምህርት ቤቱ ያቋቋመው የኮቪድ፣ ኮሚቴ ት/ቤታቸውን በአንደኛ ዙር ግምገማ አይቶ እንደነበር የተናገሩት ርዕሰ መምህሩ የፀረ ተዋሲያን ኬሚካል ርጭት ለመጀመሪያ ዙር ማከናወናቸውን በዚህ ስራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች በአሁኑ ወቅት በገበያው ተፈላጊ በመሆናቸው አንደ ልብ አገልግሎቱን ለማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል ብለዋል።

 የሳውዝ ዌስት ፕሪፓራቶሪ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ፈለቀ ፤እንደተናገሩት፤ት/ቤታቸው ት/ቢሮው ያወጣውን መስፈርቶች በሟሟላት ትምህርት ለመጀመር የሚያስችለውን ዝግጅት እያከናወነ እንደሆነ ጠቁመው፤የመማሪያ ክፍሎችን የማጽዳቱና የጸረ ተህዋሲያን ኬሚካል ርጭት የመጀመሪያ ዙር ማከናወናቸውን ገልጸዋል። በአንድ ክፍል ውስጥ ከ18-20 ተማሪዎች ተቀብለው ለማስተማር በቂ ክፍሎች እንዳሏቸውም ተናግረዋል።

 የአቡነ ጎርጎሪየስ ት/ቤት ወይራ ቅርንጫፍ ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ አሜጋ በበኩላቸው ለአዲሱ ትምህርት ዘመን ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሆኑና ክፍሎቹን ከተህዋሲያን የማጽዳቱን ሰራ ለመተግብር ከአንድ ተቋም ጋር ውል መፈራረማቸውን ነግረውናል።ለተማሪዎቹም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በወላጆች የሚዘጋጅ እንደሆነም ጠቁመውናል።

በግል ትምህርት ቤቶች የሥራ ኃላፊዎችና ባለንብረቶች  እየተነገረ ያለውን ጉዳይ አብዛኛዎቹን ት/ቤቶች እንደማይወክልና በተባለው ደረጃ ዝግጅት እያደረጉ እንዳልሆነ የሚናገሩት  አንድ  የግል ት/ቤት  መምህር “ይህ የሕይወት ጉዳይ ነው” ትምህርት ቤቶች   በሚሉት ደረጃ እየተዘጋጁ እንዳልሆነ ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ።

ባለፈው ዓመት በኮቪድ ሳቢያ ሙሉ ክፍያ ከተማሪዎቻቸው እንዳይጠይቁ መመሪያ የወጣባቸው ት/ቤቶች በከፍተኛ ኪሳራ ላይ እንደወደቁ እየተናገሩ ባለበት በዚህ ወቅት፤ ሌላ ተጨማሪ ወጪዎችን የሚያስወጣ ተግበር ያከናውናሉ የሚል እምነት የለኝም። በአብዛኛው ትቤቶች  ውስጥም የሚታየው ይሄው ነው ብለዋል።

ት/ቢሮ ይህን ችግር ለመቅረፍ ያወጣው መመሪያና መስፈርት በአግባቡ እየተተገበረ መሆኑን ለማረጋገጥ ጥብቅ ክትትል ሊያደርግ ይገባዋል ሲሉም መምህሩ ተናግረዋል።

የትምህርት ቤቶቹ ዝግጅት ሁኔታ ምን እንደሚመስል በቃኘናቸው ሁለት የመንግስት ት/ቤቶች ውስጥ ያየነው ሁኔታ ት/ቤቶቹ   ከኮሮና ወረርሽኝ በኋላ ተማሪዎቻቸውን ለመቀበል የሚያስችል የተለየ ዝግጅት እያደረጉ አለመሆናቸውንነው የሚጠቁም ነው።

በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኝው የሰላም በር አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፤ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል የግንባታ ስራ መጀመሩን ብንመለከት ግንባታው በጊዜ ገደቡ ተጠናቆ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጁ ይሆናል የሚል እምነት የለንም በተመሳሳይ ሁኔታ ካዛንቺስ አካባቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ አንድነት አፀደ ህፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ተገኝተን ባደረግነው  ቅኝት፤ት/ቤቱ ምንም ዝግጅት አለማድረጉንና 1200 ተማሪዎቸን ለመቀበል ቀደም ሲል ካሉት የመማሪያ ክፍሎች ውጪ ሌላ ግንባታ አለመከናወኑን ለማወቅ ችለናል ።

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ባንታየሁ ግርማ   እንደነገሩን ት/ቤቱ ከፍተኛ የመጸዳጃ ቤት ችግር እንዳለበትና ለትምህርት ቤቱ አጠቃላይ ተማሪዎች ያለው የመጸዳጃ ቤት አንድ ጉድጎድ ብቻ መሆኑን ገልጸውልናል ይህ ሁኔታም ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረባቸውና መንግስት ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አሳስበዋል ት/ቤቱን የጸረ ተህዋሲያን ኬሚካል ርጭት ስራ እንደተከናወነለት ጠቁመው ድጋሚ የሚደረግበትን ጊዜም እንደማያውቁ ነግረውናል።

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የአዲስ አበባ ት/ቢሮ ሰራተኛ እንደሚሉት ትምህርት ቢሮ ያወጣውን መስፈርት የሚያሟሉ ት/ቤቶች በጣም ጥቂት መሆናቸው  አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች

ብዙዎቹን ነገሮችን ወደፊት እናሟላለን በሚል ሁኔታ ትምህርት  ለመጀመር የሚችሉበትን መንገድ እየፈለጉ እንደሆነ ነግረውናል። ይህ ባለበት ሁኔታ ልጆቻችንን ወደትምህርት ቤት መላክ ለአደጋ መጋበዝ ነው የሚሉ ወላጆች ጉዳዩ በሚገባ ትኩረት እስኪያገኝ ድረስና በየትምህርት ቤቶቹ ያለው ዝግጅት በቂ መሆኑ እስካልተረጋገጠ ድረስ ልጆቻችንን ወደትምህርት ቤት አንልቅም የሚሉ ወላጆች መንግስት በጉዳዩ ላይ ትኩረት ይሰጥበት ይላሉ፡፡

የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያ  ዶክተር አብርሀም ተስፋዬ ይህን የወላጆች ስጋት  በእጅጉ አይጋሩትም  ልጆቹ በዚሁ ወረርሽን ሳቢያ ከትምህርታቸው ተፈናቅለው እቤት በመዋላቸው ሳቢያ ከፍተኛ የስነ ልቦና ጫና ተፈጥሮባቸዋል የሚሉት ባለሙያ ራሳቸውን ከበሽታው ለመከላከል የተለያዩ  ጥንቃቄዎችን  በማድረግ  ልጆቹን ወደ ትምህርት ገበታቸው መላክ ይገባል ብለዋል ልጆች ከትምህርት ገበታቸውና ከጓደኞቻቸው ተለይተው ረዘም ላለ ጊዜ መቆየታቸው በራሱ የሚያመጣው ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና እንዳለ የሚገልጹት ዶ/ር አብርሃም ይህ ሁኔታ እየቀጠለ ከሄደ ደግሞ ልጆቹን ለከፋ የጤና ችግር ሊያጋልጣቸው ይችላል ስለዚም  ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በደንብ ተወያይተው እና ጥንቃቄን ተግባራዊ እንዲያደርጉ መክረው ልጆቻቸውን  ወደ ትምህርት ቤት መላክ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎች ሁለት ሁለት ለሁሉም ተማሪዎች  በነፍስ ወከፍ ለማከፋፈል አቅድ ነድፎ፣ 50 ሚሊዮን የአፍና የአፍንጫ  መሸፈኛ ጭንብሎች እንዲመረቱ ለአዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ስራው ቢሰጥም  እስከ አሁን ድረስ የተመረተው ከ6 ሚሊዮን የማይበልጥ እንደሆነና በተሠጠው የጊዜ ገድብም ምርቱን አጠናቆ ለማስረከብ እንደማይችል ውስጥ አዋቂ ምንጮች ጠቁመውናል።

ይህ የሆነበት ምክንያት ፓርኩ ለሰራተኞች የሚከፍለው ደሞዝ አነስተኛ በመሆኑና ከፍተኛ የሠራተኛ መልቀቅ ስለሚያጋጥም እንደሆነም ምንጮች ጠቁመውናል። ስለ ጉዳዩ ለማወቅ የኢንዱስትሪያል ፓርኩን ስራ አስኪያጅ አቶ ፍጹም ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ሳይሳካልን ቀርቷል።             

በተያያዘ ዜናም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከኮሮና ወረርሽኝ በኃላ ለተከፈተው የትምህርት ዘመን እንኳን በሰላም አደረሳችሁ ሲሉ ለመላው የኢትዮጵያ ተማሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

“ከዚህ ጊዜ በላይ ተማሪዎቻችንን በቤት ውስጥ ማቆየት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። በተማሪዎቻችን ላይ ሥነልቡናዊ ጫና ያሳድራል፤ አንዳንድ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመተው በሌሎች አልባሌ መስኮች እንዲሠማሩ ያደርጋቸዋል፤ መጥፎ ሱስ ውስጥ ያስገባቸዋል። በአንድም በሌላም መንገድ ያለ እድሜ ጋብቻን ያበረታታል፤ በወላጆች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና ያሳድራል፤ የቤት ውስጥ ጥቃት ቁጥሩ እንዲያሻቅብ ያደርጋል።

ስለዚህም የተሻለው መፍትሔ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ትምህርትን መጀመር ሆኖ አግኝተነዋል። ኮሮናንና መሰል ሀገራዊ ችግሮችን የሚያጠፋ ትውልድ ማግኘት የሚቻለውም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ጭምር መማርና መመራመር የሚችል ትውልድ በመፍጠር ነው።” ብለዋል ጠ/ሚኒስትሩ፡፡

“አስፈላጊ የሆኑ የንጽሕና ቁሳቁሶችን፣ የመታጠቢያና የመጸዳጃ ቦታዎችን፣ ርቀትን ለመጠበቅ የሚያስችሉ የመማሪያ ክፍሎችን፣ በተቻላቸው መጠን ትምህርት ቤቶች እንዲያሟሉ እየተደረጉ ነው። የትምህርትና የጤና ቢሮዎች፣ ፖሊሶችና ወላጆች እነዚህን ነገሮች እንዲከታተሉ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። በየትምህርት ቤቶች አስፈላጊ ነገሮች እንዲሟሉ ወላጆች፣ የበጎ አድራጎት ተቋማትና ባለሀብቶች ማኅበራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ አቀርባለሁ።” ብለዋል በመግለጫቸው፡፡(መታሰቢያ ካሳዬ – አዲስ አድማስ)

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top