Connect with us

ለግፍም፣ ለርትዕም.. – ኳሷ በፖለቲካው ዓየር ላይ ናት!

ለግፍም፣ ለርትዕም.. - ኳሷ በፖለቲካው ዓየር ላይ ናት!
Photo: Social Media

ትንታኔ

ለግፍም፣ ለርትዕም.. – ኳሷ በፖለቲካው ዓየር ላይ ናት!

ለግፍም፣ ለርትዕም.. – ኳሷ በፖለቲካው ዓየር ላይ ናት!
(አሰፋ ኃይሉ)

‹‹የሀገርን ሀብት ለሁሉም ዜጋ በርትዕ የሚያካፍሉትም፣
በግፍ ብዙሃኑን-ድሃ ህዳጣኑን-ቱጃር የሚያደርጉትም፣
የገበያው ኃይሎች አይደሉም፣ ፖለቲከኞች ናቸው!››
– ፕ/ር ጆሴፍ ስቲግሊዝ

የአንድ ቤተሰብ ገቢ ዝቅ ሊል፣ ከፍ ሊል ይችላል፡፡ ገቢው አነሰም፣ በዛም ግን አንድ የማይናወጥ የቤተሰብ ርትዕ አለ፡፡ የትኛውም በዓለም ላይ ያለ ቤተሰብ ገቢዬ አነሰ ተብሎ አንዱን ልጅ አጥግቦ፣ ሌሎቹን ልጆቹን ፆም አያሳድርም፡፡ የቤተሰቡ አቅም ከፍ ሲልም፣ ሁለቱን ልጆቹን አልብሶ፣ አስሩን ልጆቹን ራቁት አያስቀርም፡፡ ልጅ ጎርሶ፣ እናት ጦሟን አታድርም፡፡ ቤተሰብ – ምንግዜም – ቤተሰብ ነው፡፡ በአንድ ጣራ ሥር ያለውን ተካፍሎ የሚበላ፡፡ ከችግሩም፣ ከቤዛውም አብሮ የሚካፈል፡፡

ስለ ቤተሰብ ያነሳሁት – በትንሽ የቤተሰብ ማጀት ውስጥ – ሀገርን ማየት ስለሚያስችል ነው፡፡ ሀገር ማለት ትልቅ ቤተሰብ ማለት ነው፡፡ ወይም መሆን ነበረበት፡፡ ሀገር ካዝናዋ ሲሞላ፣ የነዋሪው ህዝብ ኪስም አብሮ መሙላት አለበት፡፡ ሀገር ሀብት ስታፈራ፣ ያንን ሀብት ሁሉም ልጆቿ ተቃምሰው ማደር አለባቸው፡፡ ሀገር ማለት ትልቅ ቤተሰብ ነው፡፡ አንዱ ልጅ ተርቦ፣ አንዱ ልጅ በቁንጣን የሚሞትበት ሀገር – ሀገር አይደለም፡፡ እንጦረጦስ ነው፡፡ የአንዲት ሀገር ኢኮኖሚ – ለዜጎች ሁሉ መዳረስ አለበት፡፡ የአንድን ሀገር ኢኮኖሚ ለዜጎች ሁሉ ማዳረስም ይቻላል፡፡

ብዙዎች የሚሸሸጉበት ጥግ አጥተው፣ በፀሐይና በዝናብ አውራ መንገድ ላይ ተኝተው እያደሩ፣ ጥቂቶች ደግሞ ከሚሊዮን ወደ ቢሊዮን፣ በሀብት ላይ ሀብትን እየጨመሩ የሚሄዱበት ሀገር – የጋራ ሀገር ሊባል አይችልም፡፡ አንዱን ሚሊየነር፣ እልፉን ቤሳ ቤስቲን የሌለው ድሃ የምታደርግ ሀገር – በቤተሰብ ልትመሰል አትችልም፡፡ በዓለም እየሆነ ያለው እውነታ ግን ይህ ነው፡፡ በአሜሪካም በአፍሪካም እውነታው ይህ ነው፡፡ በኢትዮጵያም የምናየው ከዚህ ይከፋል፡፡ ሀገር ለአንዱ እናት፣ ለሌላው የእንጀራ እናት ሆናለች፡፡ ብዙዎች የሚላስ የሚቀመስ አጥተው የሥርዓቱን ውድቀት ሲመኙ፣ ሌሎች ብዙዎች ደግሞ ሞልቶላቸው ሥርዓቱን እያመሰገኑ ይኖራሉ፡፡

በአንድ ሀገር ቤት፣ በአንድ ሀገራዊ ጣራ ሥር እየኖርን፣ አንድ ሠማይ፣ አንድ ምድር እየተጋራን – ሚሊዮኖች የእለት ጉርስ ለማግኘት እንማስናለን፡፡ ሌሎች ሚሊዮኖች ደግሞ የሚሊየን ብሮች የነፃ ሥጦታ ይሰጣጣሉ፡፡ ሸራተን የዓለምን ልዑላን፣ የጊዜውን ባለሥልጣናት፣ እና ሀገር ደግ የሆነችላቸውን ቱጃሮች በምቾት ያምነሸንሻቸዋል፡፡ ያንኑ የሸራተን አጥር ተደግፈው በልመና የሚተዳደሩ በመቶዎችና በሺህዎች የሚቆጠሩ ሀገር የከፋችባቸው ምስኪን ዜጎች ደግሞ በችግር ተቆራምደው የዕለት ኑሯቸውን፣ እግዜሩ እንዳመጣላቸው፣ የሰው እርጥባን እየጠበቁ በነሲብ ይመራሉ፡፡ ህይወት አንዱ እያለቀሰ፣ ሌላው እየገለፈጠ የሚኖርባት – ገነትና ገሃነም ጎን ለጎን ተዳብለው የሚኖሩባት – የእንጀራ ልጅና የስለት ልጅ ሆነን ተጎራብተን የምንኖርባት አስገራሚ የእብድ ተዝካር ሆናብናለች፡፡

ይህን ሁሉ የዓለም ክፋት ነው – በአጭር ቃል – የዜጎች የተራራቀ የኑሮ ልዩነት – ወይም የዜጎች ገቢ አለመመጣጠን – Income Inequalities – ብለው ኢኮኖሚስቶች የሚጠሩት፡፡ አጭሩ ቃል – ማለቂያ የሌለውን ችግር አይገልጸውም፡፡ የሀገርን እንጀራ አብዛኛው ተከልክሎ – ጥቂቶች እየቆረሱ ቁንጣን እስኪይዛቸው ሲሰለቅጡት – ይሄን ‹‹የገቢ ልዩነት›› ብቻ ብሎ ማለፍ እንዴት ይቻላል? ‹‹የክፋት ጥግ›› ቢባል ራሱ ክፋቱን በትክክል አይገልጸውም፡፡

አንዱን ልጅ እያበላ፣ አንዱን ልጅ የሚያስርብ ቤተሰብ – ግፈኛ ቤተሰብ ነው፡፡ ጥቂቶችን በሀብት እያስዋኘ፣ ብዙሃኑን ዜጋ በድህነት የሚያማቅቅ ሀገር – በግፍ ግፍ የተጨማለቀ ሀገር ነው፡፡ ይህ ኢሰብዓዊ የግፍ ሥርዓት ነው በዓለም ላይ በአሜሪካ አቀንቃኝነት እየተተገበረ ያለው ነጭ ካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ሥርዓት በራሷ በአሜሪካም ሆነ፣ ያን እንደ ብልጽግና መስመር እንኮርጃለን ብለው በተነሱት በላቲን አሜሪካና በአፍሪካ ሀገሮች ኢኮኖሚ ላይ የፈጠረው ኢሰብዓዊ የኑሮ ሚዛን መዛባት ያስከተለው፡፡

ከዚህ ቀደም ‹‹The Price of Inequality›› በሚል መጽሐፉ ዓለማቀፍ አድናቆት የተቸረው የኮለምቢያ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር፣ የዓለም ባንክ የልማት ፈንድ ዳይሬክተር፣ የዓለም ኢኮኖሚስቶች ካውንስል ሊቀመንበር፣ እና የሌሎች የትዬለሌ ሙያዊ እርከኖች ታላቅ ክብርን በመቀዳጀት ከፍተኛ ልምድ ያካበተው፣ እና በኢኮኖሚክስ ሳይንስ የኖቤል ተሸላሚ የሆነው ጆሴፍ ስቲግሊዝ – ለዚህ በየሀገሩ ለተተከለው አንዱን እያስራበ ሌላውን በቁንጣን እያናጠጠ ለቀጠለው የየሀገሩ የግፍ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት እንደ ዋነኛ ምክንያት አድርጎ – ደግሞ ደጋግሞ የሚነግረን አንድ ታላቅ ነገር አለው፡፡

ጆሴፍ ስቲግሊዝ በዚህ ‹‹The Great Divide – Unequal Societies and What We Can Do About Them›› በተሰኘው ከ3 ዓመት በፊት ባሳተመው ባለ 418 ገጽ መጽሐፉ ደግሞ ደጋግሞ እንዲህ ይለናል፡- የአንድ ሀገር ዜጎች የኑሮ ልዩነት መጓን ዋነኛ ምክንያቱ ፖለቲካ ነው፡፡ የፖለቲካ ሥርዓቱ ነው በዜጎች መካከል የኢኮኖሚ ልዩነቱን የሚፈጥረው፡፡ በአንድ ሀገር ላይ ተፈጥረው – አንዱ የጎዳና ተዳዳሪ፣ አንዱ እያከከ የሚኖር ችግረኛ፣ ሌላው ደግሞ ሚሊየን ብሮችን እየመነዘረ የሚኖር ቱጃር አድርጎ ዜጎችን እንደ ሰማይና ምድር አራርቆ ያስቀመጣቸው – በየሀገሩ የሚቀነቀነው ፖለቲካ ነው፡፡ የዜጎች ድህነትና ቱጃርነት፣ ከብሔራዊው እንጀራ ላይ የአንዱ የእንጀራ ልጅነትና ረሃብ፣ የሌላው በላተኛነትና ጥጋብ የሚመነጨው – በየሀገሩ መሪዎች በሚተላለፈው የፖለቲካ ውሳኔ የተነሳ ነው ይለናል፡፡

ኦባማ ሲመረጥ አካባቢ – የአሜሪካ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ድቀት በተመታበት በዚያኑ ተመሣሣይ ወቅት – የቻይና ኢኮኖሚ – የ500 ሚሊየን ዜጎቹን የኑሮ ገቢ ከፍ በማድረግ ከድህነት ህይወት ገላግሏቸዋል፡፡ እንግዲህ – ይለናል ፕ/ር ጆሴፍ ስቲግሊዝ – እንግዲህ – ኢኮኖሚው በመንግሥት ቁጥጥር ሥር በመዋሉ፣ በዲሞክራሲ ድርቁ፣ እና በግፈኛ ሰብዓዊ አያያዙ የሚኮነነው የቻይና ኢኮኖሚ – ከሀገሪቱ ዳቦ ላይ – ለሁሉም ዜጎቹ እያቃመሰ – በርትዕ ዓይን ሚዛናዊነቱን በተግባር ለዓለም ያስመሰከረ ሥርዓት ሆኖ ታየ፡፡

በተቃራኒው ግን ቢሊየነር ቱጃሮች በነገሱባት በአሜሪካ – የኢኮኖሚ ክራይሲስ ሲከሰት – መንግሥት በመቶ ቢሊየን ዶላሮች መድቦ ከውድቀት ለማትረፍ ሲባክን የነበረው በሀብታቸው የዓለምን ጣራ የነኩ ትላልቅ የሀገሪቱን ባንኮችና የገንዘብ ተቋማት ነበር፡፡ ድሃውን ዞር ብሎ ያየው መንግሥት አልነበረም፡፡ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አሜሪካውያን የቤት መግዢያ ብድራቸውን መክፈል አቅቷቸው በከፍተኛ ችግር ላይ ሲወድቁ – ነጩ ካፒታሊስት መንግሥት – እንዳላየ አልፏቸዋል፡፡ ስቲግሊዝ አንድ የሚፀፅተውን ነገር ሲናገር – የሚከተለውን ይላል፡፡

‹‹በዎርልድ ባንክ እያለሁ – ብዙ የታዳጊ አገሮችን መንግሥታት – ኢኮኖሚያችሁን ለነጋዴ አስረክቡ፣ ከገበያችሁ እጃችሁን አውጡ፣ ሀብታሞቻችሁን አቀማጥሉ፣ ወዘተ እያልኩ የቀሰቀስኩበት ወቅት በጣም ይቆጨኛል፡፡ ውጤቱ እጅግ ‹‹ዲዛዝትረስ›› (የውድቀት-ውድቀትን ያስከተለ) ነበር፡፡ ራሴ ተሳስቼ አሳስቼያለሁ፡፡ አሁን ወቅቱ ለራሳቸው ህዝብ የተከመረ ሀብታቸውን ሊያዳርሱ ያልቻሉትን – እንደ አሜሪካ ያሉትን የዲታ ሀገራት የምንኮርጅበት ወቅት አይደለም፡፡ ወቅቱ – ያለንን የሀገር ሀብት – ለሁሉም ዜጋ እንዲዳረስ – ምን ማድረግ ይበጀናል ብለን የምንጠበብበት – እና በእጃችን ላይ ዕለት በዕለት የምንዘውራቸውን የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውሳኔዎቻችንን፣ እና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻችንን – የሀገርን ሀብት ለሀገሬው ሁሉ ለማዳረስ ባለመ መልክ የምናስተካክልበት አሳሳቢ ወቅት ነው፡፡››

በእርግጥ ሀገር ትልቅ ቤተሰብ ነው፡፡ ከሆነ ግን ከሀገሪቱ ማዕድ – ሁሉም የሀገሪቱ ልጆች – የድርሻቸውን ሊቋደሱ ይገባቸዋል፡፡ ይህ የምጣኔ ሀብት ርትዕ ብቻ ነው – ህዝባዊ ነውጦችንና አለመረጋጋቶችን የሚያስቀረው፡፡ ይህ የኢኮኖሚ ፍትሃዊነት ብቻ ነው – የዜጎች እኩልነት ማረጋገጫ መሠረቱ፡፡ ይህ እስካልሆነ ድረስ – ለሁሉም እኩል ዕድል እስካልተመቻቸ ድረስ – አንዱን ሸራተን አሳድራ፣ አንዱን ጎዳና ላይ የምታሰጣ ሀገር – ነገና ከነገ ወዲያ ውሎ አድሮ በግፍ የሚወራረድ – የግፍ ግፍ የተሸከመች ሀገር ነች፡፡ ግፉን አስፋፍቶ ለመቀጠልም፣ ግፉን አስቀርቶ ኢኮኖሚያዊ ርትዕን ለማስፈንም – ለሁሉም ነገር መጫወቻ ኳሷ – በፖለቲከኞቹ እና በባለሥልጣናቱ እጅ ላይ ነች፡፡››

“The marked differences in the extent and nature of inequality across countries demonstrate that inequality is not just determined by economic forces; it is shaped by politics and policies”
(- Joseph E. Stiglitz, The Great Divide, pp 286, 2016)

እና – የኖቤል ተሸላሚው ኢኮኖሚስት – ፕ/ር ጆሴፍ ስቲግሊዝ – የየሀገሩ ፖለቲከኞች – ኳሷን በአግባቡ እንዲጫወቱባት – አጥብቆ ይመክራል፡፡ እኛም እንላለን፡- ንጉሥ ሆይ፣ መኳንንት ሆይ፣ ሹማምንት ሆይ – ኳሷ በአየር ላይ ነችና – እባክዎ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ይለጓት?!

መልካም ንባብ፡፡

መልካም ጊዜ፡፡

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን አብዝቶ ይባርክ!

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ትንታኔ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top