Connect with us

የጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የ 2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን መልዕክት!

የጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የ 2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን መልዕክት!
Photo: Social media

ዜና

የጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የ 2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን መልዕክት!

የጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የ 2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን መልዕክት!

“ከኮሮና ራሳችሁን ከመጠበቅ ፈጽሞ ችላ እንዳትሉ!”

ከኮሮና ወረርሽኝ በኋላ ለተከፈተው የትምህርት ዘመን እንኳን በሰላም አደረሳችሁ!

ከአፀደ ህጻናት እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፤ ከግል እስከ መንግስት ትምህርት ቤቶች፤ በመላ ሃገሪቱ የምትገኙ ተማሪዎች በሙሉ

ዓለም አቀፋዊው ወረርሽኝ ኮቪድ19 በሃገራችን መከሰቱን ተከትሎ በቀዳሚነት የወሰነው ውሳኔ የእናንተን የነገ ሃገር ተረካቢዎቻችን ህይወት መታደግ ነበር፤ ትምህርት ቤቶችን በፍጥነት በመዝጋትና ሌሎች የመከላከያ እርምጃዎችን በመውሰድ ወረርሽኙ ሊያስከትል የሚችለውን ስጋትና አደጋ በእጅጉ መቀነስ ችለናል፡፡

በዚያን ወቅት የመከላከል፣ የመመርመርና የማከም አቅማችን እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነበር፤ ባህሪውን በየጊዜው ስለሚለዋውጠው ወረርሽኝ የነበረን እውቀት በጣም ውስን ነበር፡፡ ቫይረሱ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅዕኖ እንዴት መቋቋም እንደምንችል በቂ ልምድ አልነበረንም፡፡ በዚህ ምክንያት በልጆቻችን ላይ አንዳች ቸልታ ማሳየት ተገቢ እንዳልሆነ መግባባት ላይ ደርሰን ነበር፤ ለዚህ ነበር ትምህርት ቤቶችን የዘጋነው፡፡

አሁን በሃገራችን የመጀመሪያው በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው ከተገኘ ሰባት ወራት አልፎታል፤ የህክምና ባለሙያዎቻችን፤ የጤና ተቋሞቻችን ስለጉዳዩ የተሻለ ሙያዊ ብቃት አዳብረዋል፡፡

የመመርመር አቅማችን አድጓል ፤ ማህበረሰቡም ስለበሽታውና ስለመከላከያው በቂ ግንዛቤ አግኝቷል፡፡ የመከላከያ ቁሳቁሶች በቀላሉ በየአካባቢያችን ይገኛሉ፤ አንዳንድ የመከላከያ ቁሳቁሶችን በቤት ውስጥ መስራት ተችሏል፡፡

እነዚህን ነገሮች ከግምት ውስጥ ስናስገባ ከዚህ ጊዜ በላይ ትምህርት ቤቶቻችንን ዘግተን ማቆየት ተገቢ ነው ብለን አላመንም፤ ዓለም አቀፍ የጤና ተቋማት እና የጤና ባለሙያዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተፅዕኖ ለተወሰኑ አመታት ሊቀጥል እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

ክትባትና መድሃኒት የማግኘት ምርምሩም እንደቀጠለ ነው፤ በዚህ ይጠናቀቃል ብሎ ለመተንበይ ግን አስቸጋሪ ነው፡፡ ዓለም ከኮሮና ቫይረስ ራሷን እየተከላከለች እንቅስቃሴዋን መቀጠል የግድ ሆኖባታል፤ እኛም በአንድ በኩል እየተጠነቀቅን በሌላ በኩል ደግሞ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎቻችን ማከናወን እንዳለብን እናምናለን፡፡

ከዚህ ጊዜ በላይ ተማሪዎቻችንን ቤት ውስጥ ማቆየት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፤ በተማሪዎቻችን ላይ ስነ ልቦናዊ ጫና ያሳድራል፤ አንዳንድ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመተው በሌሎች አልባሌ መስኮች እንዲሰማሩ ያደርጋቸዋል፤ መጥፎ ሱስ ውስጥ ያስገባቸዋል፤ በአንድም በሌላ መንገድ ያለ እድሜ ጋብቻን ያበረታታል፤ በወላጆች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና ያሳድራል፤ የቤት ውስጥ ጥቃት ቁጥሩ እንዲያሻቅብ ያደርጋል፡፡

ስለዚህም የተሻለው መፍትሄ አስፈላጊውን ጥንቃዌ በማድረግ ትምህርትን መጀመር ሆኖ አግኝተነዋል፤ ኮሮናን እና መሰል ሃገራዊ ችግሮችን የሚያጠፋ ትውልድ ማግኘት የሚቻለውም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ጭምር መማር እና መመራመር የሚችል ትውልድ በመፍጠር ነው፡፡ 

አስፈላጊ የሆኑ የንጽህና ቁሳቁሶችን፣ የመታጠቢያና የመጸዳጃ ቦታዎችን ርቀትን ለመጠበቅ የሚያስችሉ መማሪያ ክፍሎችን በተቻላቸው መጠን ትምህርት ቤቶች እንዲያሟሉ እየተደረገ ነው፡፡

የትምህርትና የጤና ቢሮዎች፣ ፖሊሶች እና ወላጆች እነዚህን ነገሮች እንዲከታተሉ ሃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡ በየትምህርት ቤቶች አስፈላጊ ነገሮች እንዲሟሉ ወላጆች የበጎ አድራጎት ተቋማትና ባለሃብቶች ማህበራዊ ሃላፊነታችሁን እንድትወጡም በዚህ አጋጣሚ ጥሪ አቀርባለሁ፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተማሪዎቻችንን እንዳያጠቃብን መጀመሪያ ወላጆች ቀጥሎም መምህራን ከባድ ኃላፊነት አለባችሁ፡፡ ልጆች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርጉ፣ እጆቻቸውን በተደጋጋሚ እንዲታጠቡ፣ አቅም በፈቀደ መጠን የእጅ ማጽጃ ይዘው እንዲሄዱ፣ ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲንቀሳቀሱ ወላጆች እለት ተዕለት መከታተል አለባቸው፡፡ ማስማርና መምከር ይጠበቅባቸዋል፡፡

በትምህርት ቤት ውጥ ለተማሪዎች ከመምህራን የቀረበምም የለም፡፡ መምህራን ሁለተኛ ወላጅ ናቸው፡፡ ተማሪዎች በትምህርት ቤት በሚኖራቸው ቆይታ ተማሪዎችን ከኮሮና ቫይረስ ለመጠበቅ የሚያስችል መሆኑን መከታተል ይገባቸዋል፡፡ 

በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ኮሮናን ለመከላከል የሚያስችሉ መገልገያዎች እንዲያሟሉ የትምህት ቤቶች ባለቤቶች አመራሮችና መምህራን ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የምናሳየው ቸልታ ትውልድን የሚያሳጣን በመሆኑ መንግስት በዝምታ የሚያልፈው ነገር አይደለም፡፡

ይህ የኮሮና ወቅት በታሪክ ምንጊዜም ስናስታውሰው የምንኖረው ነው፡፡ 

ይህን ወቅት የድል ወቅት በማድረግ የተሻለ ትውስታ እንዲኖረን እናድርግ፡፡ ያልተስተካከሉ ነገሮችን በማስተካከል የጎደሉ ነገሮችን በማሟላት ያልተመቹ ነገሮችን በማመቻቸት ይህን ዓመት የውጤት ዓመት እናድርገው፡፡ አካባቢያችንን በማጽዳት ችግኞችን በመትከል ለኮሮና መከላከያ የሚሆኑ አዳዲስ ነገሮችን በመፍጠር የኮሮና ወቅት የስኬት ወቅት ሆኖ እንዲያልፍ እናድርገው፡፡

ያለፈውን ዓመት ትምህርት ለመከለስ ዘግይቶ የተጀመረውን የዚህን ዓመት ትምህርት ለማካካስ ሲባል በተማሪዎች፣ በመምህራን እና በወላጆች ጫና መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ሆኖም ግን አንድ ነገር እንድታስታውሱ አደራ ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ 

ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ውጤታማ ሆነው ለክብር የደረሱት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አልፈው ነው፡፡ ብዙዎቹ ሳይንቲስቶች፣ ምሁራንና ሊቃውንት ለማዕረግ የበቁት በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ተምረው ነው፡፡ ለዚህም እናንተ የመጀመሪያዎቹም የመጨረሻዎቹም አይደላችሁም፡፡ ጀግና የሚፈጠረው በችግር ጊዜ በመሆኑ የኮሮና ወቅት የብዙ ጀግና ተማሪዎች መፍጠሪያ ጊዜ እንደሚሆን አምናለሁ፡፡

ውድ ተማሪዎች ሀገራችን ኢትዮጵያ ትፈልጋችኋለች ፤ ወላጆቻችሁ ይፈልጓችኋል፤ የሚያውቋችሁ የሚቀርቧችሁ ሁሉ ይፈልጓችኋል፡፡ ኮሮናን በተመለከተ የሚፈጠር ቀላል መዘናጋት ከባድ ዋጋ ስለሚያስከፍለን ጥንቃቄ አይለያችሁ፡፡ ጉዳዩ የህይወት ጉዳይ ነው፡፡ ጉዳዩ የትውልድ ቀጣይነት ጉዳይ ነው፡፡

ከኮሮና ራሳችሁን ከመጠበቅ ፈጽሞ ችላ እንዳትሉ፡፡ ይህ ጊዜ አልፎ እንዴት እንዳለፈ የምንተርክበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ ጥንቃቄ ሳይለያችሁ ትምህርታችሁን በርትታችሁ ተማሩ፡፡

ከተማሪዎች ባለፈ ወላጆች፣ መምህራን፣ የትምህርት ቤቶች አስተዳደር ሰዎች፣ የጤና ባለሙያዎችና የጸጥታ አካላት ኮሮናን በትምህርት የሚያሸንፍ ትውልድ እንዲፈጠር ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ ከፍ ያለ አደራ ተሰጥቷችኋል፡፡ አደራውን በብቃት እንደምትጠብቁም ሙሉ በሙሉ በእናንተ እተማመናለሁ፡፡

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top