Connect with us

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሥጋት ምንድነው?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሥጋት ምንድነው?
Photo: Social media

ትንታኔ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሥጋት ምንድነው?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሥጋት ምንድነው?

(ፍሬው አበበ)

ምርጫ ቦርድ ሰሞኑን አንድ ለውይይት የሚረዳ ጥናት ቀመስ መጣጥፍ አውጥቶ ነበር፡፡ መጣጥፉ የቦርዱን ሥጋት ፍንትው አድርጎ ያሳየ ነው፡፡ ቦርዱ ለምን ሰጋ? በመጣጥፉ ውስጥ በግልጽ የተመለከተ ነገር የለም፡፡ ነገርግን ምርጫ በሚካሄድበት በዚህ ወቅት በምርጫ ሕጉ ላይ ማሻሻያ ሊደረግ ይችላል የሚል ሥጋት ገብቶታል፡፡ ምናልባትም የሥጋቱ መነሻ የፖለቲካ ኃይሎች እያካሄዱ ያሉት ውይይት ወዴየት እያመራ እንደሆነ ተገንዝቦ ሊሆን እንደሚችል የዚህ ጹሑፍ አቅራቢ ይገምታል፡፡

ያም ሆነ ይህ የምርጫ ቦርድ በምርጫ ዓመት ሕግ ማሻሻል የሚያስከትለውን ጣጣ በዚህ መጣጥፉ ዙሪያ ገባውን በሚገባ ቃኝቷል፡፡ ልብ ያለው፤ ልብ እንዲል መክሯል፡፡ ዋና ዋና ነጥቦቹን ብቻ እንመልከተው፡፡

በምርጫ ቦርድ መጣጥፍ ውስጥ የምርጫ ሥርዓትን ብሔራዊ ምርጫ በሚደረግበት ተመሳሳይ ወቅት መቀየር ምን ተጽእኖ ሊያስከትል ይችላል? የሚለውን ሊመልስ ከመሞከሩ በፊት ምን ለውጥ ሊኖር ይችላል የሚለውን ግምታዊ እሳቤውን ያስቀምጣል፡፡

“ይህ የውይይት ሃሳብ በሚዘጋጅበት ወቅት በምርጫ ስርአቱ ላይ ሊኖሩ የሚችሉ ለውጦች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ግልጽ መረጃ የለም፡፡ ነገር ግን የተመጣጣኝ ውክልና ስርአትን በመጨመር የምርጫ ስርአቱን ወደ የቅይጥ ስርአት የመቀየር ይህም ማለት አሁን ከሚገኘው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስቱ አንቀጽ 54 ከተቀመጠው በአብላጫ ድምጽ የሚገኙ መቀመጫዎች በተጨማሪ በተመጣጣኝ ውክልና ተጨማሪ መቀመጫዎችን የመጨመር አሰራር ሊሆን ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡ 

የምርጫ ስርአት ለውጡ ይህ አይነት ከሆነ የሚመለከተው የተወካዮች ምክር ቤትን ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡ ፡ የዚህ ፅሁፍ ትኩረት ይህ አይነት ለውጦች  የምርጫ ኦፕሬሽን ላይ የሚኖራቸውን ተጽእኖ ላይ ብቻ ይሆናል፡፡ የምርጫ ስርአት መቀየር ራሱን የቻለ የፓለቲካ ሂደት በመሆኑ ይህ መነሻ ጽሁፍ በእንደዛ ያሉ ጉዳዮች ላይ አቋም ለመያዝ ሳይሆን በቴክኒካል የምርጫ ሂደት ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ ለማሳየት ብቻ የተዘጋጀ ነው፡፡”

ለውጡ ከሚያስከትላቸው ተጽዕኖዎች መካከል

–    ሕገመንግሥታዊ ማሻሻያን ሊጠይቅ ሊጠይቅ መቻሉ፣

–     የምርጫ ህግ እና አሰራሩ ላይ ማሻሻያ መጠየቁ፣

–     የምርጫ ክልሎችን የሚነካ የምርጫ ስርአት ለውጥ ከተከናወነ የመጪውን ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ተጽእኖ ሊኖረው የመቻሉን ጉዳይ በዝርዝር ዳሷል፡፡

*ለውጡ በህግ እና በተቋማዊ አሰራር ላይ የሚኖረው አንደምታ 

በቦርዱ መጣጥፍ መሰረት አንዱ የሚጠበቀው የህገመንግስታዊ ማሻሻያ ይሆናል፡፡ በ.ኢፌ.ዲ.ሪ ህገመንግስት አንቀጽ 54(2) እና 54(3) የተቀመጠውን የምርጫ ስርአት መቀየር በህገመንግስቱ አንቀጽ 104 እና አንቀጽ 105 በተቀመጠው መሰረት መከናወን ይኖርበታል፡፡ ይህ ማለት የምርጫ ስርአቱን መቀየር ከፍተኛ ጊዜ፣ ውይይት/ምክክር እና ሃብት የሚወስደውን የህገመንግስት የማሻሻል ስራን ይጠይቃል ማለት ነው፡፡ 

ከነዚህ አጠቃላይ ሂደቶች በተጨማሪ የህገመንግስቱ አንቀጽ 104 ማሻሻያ ለሚመለከታቸው አካላት ሊቀርብ እንደሚገባ ይደነግጋል፡፡ የምርጫ ስርአት ማሻሻያ ደግሞ መላ አገሪቷን የሚመለከት በመሆኑ ከተለያዩ የማህበረሰብ አካላት ጋር ውይይት መደረግ እንደሚገባ ይኸው የህገ መንግስቱ አንቀጽ ይደነግጋል፡፡ 

ስለዚህ አገራዊ ምርጫን በታለመለት በ2013 አመት ለማካሄድ ከታሰበ የምርጫ ስርአት ለውጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ መከናወን የሚገባው ሲሆን ለውጡም የምርጫ ኦፕሬሽን ላይ ከፍተኛ ለውጥ የማያስገድድ መሆን ይኖርበታል፡፡ 

የህግ ማሻሻያ – የህገ መንግስታዊ ማሻሻያው በማስከተል የምርጫ ህጉ እና አሰራሩ ማሻሻያ ሊደረግበት ይገባል፡፡  ለምሳሌ አሁን ያለው የምርጫ ስርአት እንዳለ ሆነ የተመጣጣኝ ውክልና ስርአት ከተጨመረበት በምርጫ ኦፕሬሽን ወቅት ተጨማሪ የድምጽ መስጫ ወረቀት፣ የተለየ የድምጽ ቆጠራ እና ድመራ ስርአት መዘርጋት የሚጠይቅ ይሆናል፡ ፡ ይህም ለስህተት  ለመዳረግ እንዲሁም የምርጫ ውጤት ይፋ ማድረጊያ ጊዜን የማራዘም ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል፡ ፡ 

የምርጫ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች እና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ 1162 እንዲሁም የብሔራዊ ምርጫ ቦርዱ ማቋቋሚያ አዋጅ 1133 በ2011 ዓ.ም ሲወጡ የምርጫ ኦፕሬሽን ላይ ብዙ ለውጦችን ማካተታቸው ይታወሳል፡፡ 

 ተቋማዊ ማሻሻያ – ከህጎች በተጨማሪ የሚቀየረው የምርጫ ስርአት ለውጥ የቦርዱን ውስጣዊ አደረጃጀት የመቀየር እድል ሊኖረው ይችላል፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዲስ በወጡት እና ከላይ ተጠቀሱት ህጎች መሰረት ተአማኒ እና አለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ምርጫ ለማከናወን ራሱን እያደራጀ ሲሆን የምርጫ ስርአት ለውጥ በቦርዱ የውስጥ አሰራር እና መዋቅር ለውጥ ላይ አዲስ ማስተካከያ ለማድረግ ሊያስገድደው ይችላል፡፡  

 የምርጫ ክልሎች አከላል- የምርጫ ስርአትን መቀየር ከምርጫ ክልሎች አከላል ጋር ሊኖረው የሚችለው ግንኙነት እና ተጽእኖ ግልጽ አይደለም፡፡ የምርጫ ክልሎችን የሚነካ የምርጫ ስርአት ለውጥ ከተከናወነ የመጪውን ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል፡፡

**ማጠቃለያ

በታቀደው የምርጫ ስርዓት ለውጥ ላይ ያለው የመረጃ ውስንነት ለውጡ የሚያመጣውን ቴክኒካዊ አንድምታዎች በተመለከተ ዝርዝር ትንታኔ ለመስጠት እንዳይቻል ይገድባሉ፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ የመጀመሪያው ትንታኔ እንደሚያመለክተው በምርጫ ዓመት ውስጥ የሚደረጉ የተወሰኑ ለውጦች በአጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ ተዓማኒነት እና ተቀባይነት፣ አካታችነት እና ወቅታዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋን ይጥላሉ፡፡

የምርጫ የጊዜ ሰሌዳን መወሰን የሚቻለው ለውጦቹ ተጠናቀው አዲሱ ህገ-መንግስት ማሻሻያ እና የምርጫ አዋጅ ከፀደቀ በኋላ ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዲሱ ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ ላይ  እና የተሻሻለውን የምርጫ አዋጅ ላይ በመመርኮዝ መመሪያዎችን እና የአፈፃፀም እቅዶቹን መገምገም የሚችለው ከዚያ በኋላ ብቻ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ የሚወስደው ጊዜንም ማካተት ይኖርበታል፡፡  የምርጫ ስርዓቱ መለወጥ ጉልህ የሆኑ ተጨማሪ የአሰራር ችግሮችን የማይፈጥር ቢሆን እንኳን ምርጫው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንዲካሄድ ለማስቻል እንዲሁም ምርጫ ቦርድ የምርጫ እንቅስቃሴዎችን አተገባበር ለመቀጠል እንዲችል በጊዜ ውሳኔ ላይ መድረስ አስፈላጊ ነው፡፡

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሊኖር የሚችለው የምርጫ ስርአት ለውጥ የሚጠናቀቅበት ቁርጥ ጊዜን ማወቅ ይኖርበታል፡፡ እንዲሁም በሂደቱ ላይ መሳተፍ እና የሚመጡት ለውጦች ከምርጫ ኦፕሬሽን እና የጊዜ ሰሌዳ አንጻር ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ እና ተጽእኖአቸውን ለመገምገም ስለሂደቱ በቂ እውቀት ሊኖረው ይገባል፡፡   

   

Click to comment

More in ትንታኔ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top