Connect with us

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ መጣስ በ 2 ዓመት እስራት ያስቀጣል

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ መጣስ እስከ 2 ዓመት በሚደርስ እስራት ያስቀጣል
Photo: Social media

ዜና

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ መጣስ በ 2 ዓመት እስራት ያስቀጣል

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጣር የወጣውን መመሪያ ቁጥር 30/2013 መጣስ እስከ ሁለት ዓመት በሚደርስ እስራት ያስቀጣል

የኮቪድ 19 የሚመለከተው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኃላም በአሁኑ ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጣር የወጣ መመሪያ ቁጥር 30/2013 በተለያዩ አካላት ላይ ማለትም በግለሰቦች፣ በመንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና በድርጅቶች ላይ ክልከላዎችን እና ግዴታዎችን ጥሏል፡፡

በመመሪያው የተቀመጡ ክልከላዎች እና ግዴታዎች ተላላፊ በሽታን ለመከላከል እና ለመግታት የተደነገጉ የጥንቃቄ እርምጃዎች አካል ሲሆኑ ክልከላዎቹን መተላለፍ እና ግዴታዎቹን አለመወጣት አግባብ ባለው የወንጀል ህግ እንደሚያስቀጣ በመመሪያው ተደንግጎ ይገኛል፡፡

ከኮቪድ -19 ወረርሽኝ የመተላለፍ ባህርይ አንፃር በመመሪያው ከተቀመጡ ክልከላዎች ለአብነት ያክል ለሰላምታና ሌላ ለማንኛውም አላማ በእጅ መጨባበጥ፣ ሆነ ብሎ የእርስ በእርስ አካላዊ ንክኪ ማድረግ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አለማድረግ፣ በክፍት ገበያዎች፣ በትራንስፖርት መሳፈሪያ ቦታዎች፣ ህዝባዊ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቦታዎችና ሌሎች ህዝብ በሚበዛባቸው መሰል አካባቢዎች ከሁለት የአዋቂ እርምጃ በታች ርቀት መቆምም ሆነ መቀመጥ፣ አገልግሎት ሰጪ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት ሰራተኞች ከሁለት የአዋቂ እርምጃ በታች ተጠጋግተው እና የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ፣ ተገልጋዮች በሚቀመጡበት ጊዜም ይሁን በማንኛዉም አኳኋን አገልግሎት ሲያገኙ ከሁለት የአዋቂ እርምጃ በታች ተጠጋግተው እና የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ወይም በአንድ ጠረጴዛ ከሶስት ተገልጋዮች በላይ እንዲቀመጡ ማድረግ ከክልከላዎቹ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ግዴታዎችን በተመለከተ ደግሞ የመንግስታዊ እና የግል ተቋማት አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ተቋሙ ለሚመጡ ተገልጋዮች ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን የማቅረብ፣ ለሰራተኞቻቸው የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚረዱ የጥንቃቄ ቁሳቁሶችን የማቅረብ፣ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረጋቸውን እና ሌሎች አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን መተግበራቸውን የማረጋገጥ፣ ለምሳሌ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በህግ በሚወሰነው የመጫን አቅም ልክ ሰዎችን የመጫን፣ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ያላደረጉ ሰዎችን አገልግሎት አለመስጠት፣ መስኮቶችን በመክፈት በተሽከርካሪው ውስጥ በቂ የአየር ዝውርውር እንዲኖር የማድረግ እና በዘርፉ በመመሪያ የሚወጡ ሌሎች መወሰድ የሚገባቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች በመተግበር አገልግሎት የመስጠት ግዴታዎች ይገኙበታል፡፡

እነዚህ ከላይ ለአብነት ያክል የተጠቀሱትን እና ሌሎች በመመሪያው የተካተቱ ክልከላዎችን እና ግዴታዎችን የተላለፈ ማንኛውም ሰው አግባብነት ባለው የወንጀል ህግ አንቀጽ መሰረት የሚቀጣ መሆኑን መመሪያው አንቀፅ 30 ላይ ያስቀመጠ ሲሆን ለጉዳዩ አግባብነት ያለው የወንጀል ህግ  በ1996 ዓ.ም የወጣው የኢ.ፌ.ድ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 522 ነው፡፡ ይህም ጤናን ለመጠበቅና ለመንከባብ በህግ የተደነገጉትን የጥንቃቄ እርምጃዎችን መጣስ የሚያስከትለውን የእስራት እና የገንዘብ መቀጮ ይመለከታል፡፡

በዚህም መሰረት በወንጀል ህጉ አንቀፅ 522 ንዑስ አንቀፅ 1 ስር እንደተደነገገው ማንም ሰው ማለትም የተፈጥሮ ሰው ወይም በህግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ተላላፊ በሽታን ለመከላከል፣ ለመግታት ወይም ለማቆም በህግ የተደነገጉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን አስቦ የጣሰ እንደሆነ ከሁለት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል፡፡ እንዲሁም ወንጀሉ የተፈፀመው በቸልተኝነት እንደሆነ ቅጣቱ ከስድስት ወር የማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከሦስት ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮ መሆኑን አንቀፅ 522/2 ይደነግጋል፡፡

ከወንጀል ድንጋጌዎቹ ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮችን መገንዘብ እንችላለን፡፡ አንደኛ ክልከላዎችን መተላለፍ ወይም ግዴታዎችን አለመወጣት የወንጀል ተጠያቂነት ለማስከተል ሆን ተብሎ (intentionally) ወይም በቸልተኝነት (negligently) ሊፈፀም እንደሚችል እና ድርጊቶቹ በተፈጥሮ ሰዎች ወይም በህግ ሰውነት በተሰጣቸው ማለትም በተቋማት እና በድርጅቶች ሊፈፀም የሚችሉ መሆኑን ነው፡፡ በዚሁ መሰረት ጥሰቱን የፈፀመውን አካል እና የሀሳብ ክፍሉን (ሆን ብሎ ወይም በቸልተኝነት) መሆኑን መሰረት በማድረግ የወንጀል ቅጣቱ የእስራት ወይም የገንዘብ መቀጮ ይሆናል ማለት ነው፡፡

በአጠቃላይ ህብረተሰቡ ወረርሽኑን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር መደረግ ያለባቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎችን ያለመታከት በመተግበር ራሱን ብሎም ሌሎችን ከወረርሽኙ እና ከሚያስከትለው ጉዳት እንዲሁም በመመሪያው የተቀመጡ ክልከላዎች እና ግዴታዎችን መጣስ ከሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ (ምንጭ፡- የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ)

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top