Connect with us

ክቡር ጠ/ሚኒስትር አይንገሩን፤ ፈጽመው ያሳዩን?!

ክቡር ጠ/ሚኒስትር አይንገሩን፤ ፈጽመው ያሳዩን?!
Photo: Social Media

ነፃ ሃሳብ

ክቡር ጠ/ሚኒስትር አይንገሩን፤ ፈጽመው ያሳዩን?!

ክቡር ጠ/ሚኒስትር አይንገሩን፤ ፈጽመው ያሳዩን?!

(ጫሊ በላይነህ)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ ከትላንቱ የፓርላማ ንግግራቸው መካከል በሁለት ነጥቦች ላይ የሰጡት አስተያየት አስገርሞኛል፡፡ ሁለቱን ነጥቦች ልጥቀስ፡፡

የመጀመሪያው፡- “አስፈጻሚው አካል የፍርድ ቤት ትእዛዞችን ማክበር አለበት” በማለት የገለጹት ነው፡፡ “ፍርድ ቤቶች የሚሰጡትን ማንኛውም ውሳኔዎች አስፈጻሚው አካል ማክበር አለበት፡፡ እኛ ያላከበርነው እና ያልታዘዝነው ፍርድ ቤት ነጻና ገለልተኛ ሆነ ማለት ከንቱ ነው” ብለዋል፡፡

አባባሉ ለእኔ ትንሽ ፈገግ ያሰኘኝ ነው፡፡ በሕግና በስርዓት የተጣለበትን ኃላፊነት ሊወጣ መሀላ ገብቶ ወንበር ላይ የተቀመጠ ሹም “ሕግ አክብር” ማለት ለቀባሪ ማርዳት ይሆናል፡፡ ለመሆኑ ከህግ በላይ የሆነ የአስፈጻሚው አካል በዚህ መልክ የሚለመነውና የእለት ተዕለት ስራው የሚነገረው ለምንድነው? ከሕግ በላይ እንዲሆንስ ቀድሞውኑ የፈቀደለት ማንነው? በወያኔ ዘመን እንኳን በዚህ ደረጃ ያልተሞከረ ፍርድ ቤትን መናቅና ማዋረድ ከየት የመጣ ልምድ ነው? ደግሞም ለፍርድ ቤት አልታዘዝም የሚሉ አካላት በዝምታ የታለፉበት ምክንያትስ ምንድነው? የሚሉት ነጥቦች መልስ የሚሹ ናቸው፡፡ ሰዎችን ከስሶ ፍርድ ቤት የሄደ አካል ለእሱ የሚስማማው ውሳኔ ሳይተላለፍ ሲቀር የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚጥስበት አሰራር እያደገ ከመጣ እጅግ አደገኛ ነው፡፡ይህ እየሆነ ያለው በማን አይዞህ ባይነት የሚለውን ነው የሚለው በጥብቅ መፈተሽ የለውጥ ኃይሉ ለማንም ሳይሆን ለራሱ ሕልውና ሲል ፈጥኖ ሊከውነው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

ጠ/ሚኒስትሩ የአገር መሪ ናቸው፡፡ እስከታች ባሉ ጥቃቅን ጉዳዮች ሁሉ እጃቸውን እንዲያስገቡ ላይጠበቅ ይችላል፡፡ እርግጥ ነው፤ ስራውን በአግባቡና በህግና በህግ ብቻ የሚወጣ መዋቅር ቢኖር ኖሮ የጠ/ሚኒስትሩ የትላንት ማሳሰቢያም ባላስፈለገ ነበር፡፡ የጠ/ሚኒስትሩና የአስፈጻሚው ከፍተኛ አካላት ጣልቃ ገብነት የሚያስፈልገው የህግ የበላይነት ምሰሶ መነቅነቅ በመጀመሩ ነው፡፡ በአስፈጻሚ ውስጥ ያሉ ጥቂት ዋልጌዎች ፍርድ ቤትን መጫወቻና መሳለቂያ ሲያደርጉ በዝምታ ማለፍ በተቃራኒው ለህገወጥ ድርጊቱ መተባበር ይሆናል፡፡ ዘለግ አድርጎ ሲታይም ህገወጥነትን በዚህ መልክ ማበረታታት ነገ ለማረም አስቸጋሪ የሚሆን የህገወጥነት መዋቅር እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል፡፡

ክቡር ጠ/ ሚኒስትሩ እንደእነአቶ ልደቱ አያሌው አይነት የአደባባይ ፖለቲከኞች የፍርድ ቤት ትእዛዝ ለማክበር ፍላጎት በሌላቸው አካላት በሕገወጥ እስር መቆየታቸውን “አልሰማሁም፣ አላየሁም” ሊሉን አይችሉም፡፡ ደግሞ እንዲህ ዓይነት መሰል እርምጃዎች በሌሎች ታሳሪዎችም ላይ መደጋገም ፍርድ ቤቶችን ጥርስ የሌለው አንበሳ ከማድረጉም በላይ በፍትሕ ስርኣቱ ለመሳለቅ ለሚፈልጉ ኃይሎች ዱላ ያቀበለ ግዙፍ የህግ ጥሰት ነው፡፡

የሚገርመው ጠ/ሚኒስትሩ ይህንን ንግግር ባደረጉበት በትላንትናው እለት አቶ ልደቱ አያሌው የፍርድ ቤት ትእዛዝ አላከብርም ባለ አካል በህገወጥ እስር ላይ ነበሩ፡፡ እናም የእኔ ጥያቄ ጠ/ሚኒስትሩ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ መከበር አለበት እያሉ የሚናገሩት ለማን ነው የሚል ነው፡፡ ምናልባት እሳቸው ትክክለኛ ሰው ናቸው ብለን ስህተቱን ሌሎችን አካላት ላይ እንድንደፈድፍ ፈልገው ይሆን?

ክቡርነታቸው፤ ይህን ግሳጼ በቀጥታ ለሚመለከታቸው አካላት በመግለጽ አቶ ልደቱ ከህገወጥ እስር እንዲፈቱ ለማድረግ አንድ የስልክ ጥሪ ማድረግ ብቻ ይበቃቸው ነበር፡፡ ይህን ማድረግ እየቻሉ ለምን ሕገወጥነትን በዝምታ እንደሚመለከቱ ለእኔ ግልጽ አይደለም፡፡

ሁለተኛው ጉዳይ፤ የሚዲያ ነጻነትን በተመለከተ ያደረጉት ንግግር ነው፡፡ እርግጥ ነው፤ “ሰዎች መናገር ፣መጻፍ እና መተቸት እንዲችሉ መፍቀድ ይኖርብናል” ባሉት አልሰማማም፡፡ ምክንያቱም የንግግሩ ድምጸት አስፈጻሚው አካል የፕረስ ነጻነትን ፈቃጅና ከልካይ ስለሚያስመስለው ነው፡፡ የፕረስ ነጻነት ሕገመንግስታዊ መብት ነው፡፡ ጋዜጠኞች አንድ ባለስልጣን በመተቸታቸው ምክንያት ያለፍርድ ቤት መያዣ ማሰር፣ ማስፈራራት፣ ማሸማቀቅ መብት የላቸውም፡፡ ባለስልጣናት በፕረስ ስራዎች ቅሬታ ካላቸው ሕጉን ተከትለው ማስተባበያ ማሰራት፤ አለበለዚያ ክስ መመስረትና መሟገት እንጂ ጋዜጠኛን ማሰር ከፍተኛ የህግ ጥሰት ነው፡፡

ለክቡር ጠ/ሚኒስትሩ በግሌ የምመክረው፤ ይኸን ግሳጼያቸውን ለእኛ ሳይሆን ለሹማምንቶቻቸው በተዋረድ እንዲያደርጉ ነው፡፡ አልታዘዝ ባዮችን፣ አጥፊዎችን በአስተዳደራዊ መንገድ እንዲቀጡ በማድረግ ሕግና ስርዓት እንዲከበር እንዲያደርጉ ነው፡፡

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top