Connect with us

የኤልጂ የሠራተኞች ማህበር ለኮርያውያን ዘማች አባቶች ድጋፍ አደረገ

የኤልጂ የሠራተኞች ማህበር ለኮርያውያን ዘማች አባቶች ድጋፍ አደረገ
በድሬቲዩብ ሪፖርተር

ባህልና ታሪክ

የኤልጂ የሠራተኞች ማህበር ለኮርያውያን ዘማች አባቶች ድጋፍ አደረገ

የኤልጂ የሠራተኞች ማህበር ለኮርያውያን ዘማች አባቶች ድጋፍ አደረገ

 (በድሬቲዩብ ሪፖርተር)

ኤልጂ ኤሌክትሮኒክስ (LG Electronics)  የሠራተኞች ማህበር ለኮርያ ዘማቾች ማህበር አባላት ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ የኢኮኖሚና የጤና ችግሮች ለመደጎም የሚረዳ  የገንዘብና የመድሀኒት ዕርዳታ ሰጠ፡፡

በኮርያ ዘማቾች መታሰቢያ ፓርክ በዛሬው ዕለት በተከናወነው ሥነሥርዓት ላይ በመገኘት ከኤልጂ ሠራተኞች የተላከውን ስጦታ ለ134 የኮርያ ዘማች አባላት የሰጡት ሚስተር ፓርክ ዮንግኪዩ፤ የወርልድ ቱጌዘር ኢትዮጽያ ዳይሬክተር እና ሚስተር ሲዩንግ ሀዋን ያንግ የኤልጂ ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ  ናቸው፡፡

ስጦታው ለ134 አባላት ለእያንዳንዳቸው የ6 ሺ ብር ገንዘብ እና በሽታን ለመቋቋም የሚረዱ ቫይታሚን መድሃኒቶችን ያካተተ ነው፡፡

ሚስተር ፓርክ እና ሚስተር ሲዩንግ ሀዋን የኮርያ ዘማች አባቶች ያደረጉት ተጋድሎና ጀግንነት የማይረሳ መሆኑን ተናግረው አቅም በፈቀደ መጠን በቀጣይም የተለያዩ ድጋፎች ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡

የኮርያ ዘማቾች ማህበር ፕሬዚደንት ኮሎኔል መለስ ተሰማ ኤልጂ ኤሌክትሮኒክስ የሠራተኞች ማህበር ስላደረገላቸው ድጋፍ በማህበሩና በአባላቱ ስም ከፍተኛ ምስጋና ከማቅረባቸውም በላይ ኮርያውያን እስከዛሬም ለዘማቾች እያደረጉ ላሉት ያልተቋረጠ ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

ኮሎኔል መለስ ተሰማ ለድሬቲዩብ በሰጡት አጭር ቃለምልልስ የኮርያ ዘመቻ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተደረገ ጥሪ መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት የክብር ዘበኛ አራት ሻለቃ እና አንድ ሻምበል በጠቅላላው 6 ሺ 37 ሰራዊት የዘመተው የዛሬ 70 ዓመት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ጦርነቱም በጠቅላላ አምስት ዓመታት ጊዜ የወሰደ መሆኑንና ዋናው ጦርነት የተካሄደው ለሶስት ዓመት እንደነበር አስታውሰው ኢትዮጵያዊያን በወቅቱ ከኮርያዊያን ጎን በመሰለፍ በፍጹም ጀግንነት ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በጦርነቱ 122 ኢትዮጽያዊያን ወታደሮች መሞታቸውን፣ 536 መቁሰላቸውን ያስታወሱት ኮሎኔል መለስ አንድም ጠፍቶ የቀረ ወይንም የተማረከ ወታደር ግን አልነበረም ብለዋል፡፡

ሚስተር ፓርክ ከኢትዮጵያ አንድ  ዘማች አንድ ገራሚ ታሪክ መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡ በጦርነቱ ወቅት አንድ የኮርያ ወታደር ቆስሎ የተመለከተው ኢትዮጵያዊ ወታደር በጦርነት መካከል የቆሰለውን ወታደር ተሸክሞ ለማዳን በሚሮጥበት ወቅት የተቀበረ ፈንጂ በመርገጡ ሁለቱም በአደጋው ሕይወታቸው ማለፉን እና በዚያች ቦታ የኢትዮጵያዊው እና የኮርያዊው ወታደር ደም መወሃዱን እንደነገሩዋቸው አንስተዋል፡፡

ይኸም የሚያሳየው ኮርያዊያን እና ኢትዮጵያውያን በደም የተሳሰሩ ወንድማማች ሕዝቦች መሆናቸውን ነው ብለዋል፡፡

ኮሎኔል መለስ፤ የኮርያ ዘማቾች በዘመነ ደርግ አስታዋሽ አጥተው ከቆዩ በኃላ በዘመነ ኢህአዴግ ማህበር በመመስረት ከኮርያ መንግስት ጋር ባደረጉት መልካም ግንኙነት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ድጋፎችን በተከታተይ ከማግኘታቸውም በተጨማሪ ለዘማች ልጆች የስኮላርሺፕ ተጠቃሚ መደረጋቸውን በማንሳት የኮርያ መንግስትና ሕዝብ እያደረገ ላለው ሁለንተናዊ ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top