Connect with us

“በማንኛውም ዜጋ ላይ የሚፈፀም ኢፍትሃዊነት በሁላችንም ላይ እንደተፈፀመ ይቆጠራል”

"በማንኛውም ዜጋ ላይ የሚፈፀም ኢፍትሃዊነት በሁላችንም ላይ እንደተፈፀመ ይቆጠራል"
Photo: Social Media

ህግና ስርዓት

“በማንኛውም ዜጋ ላይ የሚፈፀም ኢፍትሃዊነት በሁላችንም ላይ እንደተፈፀመ ይቆጠራል”

“በማንኛውም ዜጋ ላይ የሚፈፀም ኢፍትሃዊነት በሁላችንም ላይ እንደተፈፀመ ይቆጠራል”
(አንዱዓለም አራጌ ~የኢዜማ ከፍተኛ አመራር)

ከዚህ ቀደም በጣም በአመዛኙ የፓርቲዬን አቋም ካልሆነ በስተቀር እምብዛም የግል አቋሜን አንፀባርቄ አላውቅም።

ብዙውን ጊዜ ተቋሞቻችን ህፀፃቸውን እያረሙ ሁላችንም የምንደገፍባቸው ተቋማት እንዲሆኑ እድልም ሆነ ጊዜ መስጠት ተገቢ መሆኑን አምናለሁ። ይሁንእንጂ ፣ ትናንት የኢትዮጵያ ህዝብ በነፍስና በስጋው ተወራርዶ መራር ህዝባዊ ትግል ያደረገው ዝቅ ብለን የምንመለከተውን አይነት ግፍ ለማስተናገድ አለመሆኑ እሙን ነው።

በ1993 ዓ.ም በጊወርጊስ የጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤት በተለያዩ ሁለት ችሎቶች፣ በተመሳሳይ እለት፣ በተመሳሳይ ሰዓት የተፈፀሙ ሁለት ውሳኔወችን ለማስታወስ እወዳለሁ።

አንደኛው ችሎት በሀቪየስ ኮርፐስ ክስ አማካኝነት፣ እነአቶ ታምራት ታረቀኝን ካሰረበት አምጥቶ ለፍርድ ቤቱ ያቀርብ ዘንድ ፓሊስን ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ቢያዝም ትዛዙ ባለመፈፀሙ በወቅቱ የፍትህ ሚንስትር የነበሩት አቶ ወረደ ወልድ ወልዴ ታስረው እንዲቀርቡ ባዘዘው መሰረት ታስረው ቀረቡ። ፍርድ ቤቱም የአንድ ወር እስራት ፈረደባቸው።

በሌላ የዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ ችሎት አቶ ስዬ አብርሃ ቀርበው የወይዘሪቷ ችሎት አርነት ሰደዳቸው። ይሁን እንጂ ለቤታቸው ሊበቁ የተገባቸው አቶ ስዬ አብርሃ በአፈሙዝ አስገዳጅነት ወህኒ እንዲወርዱ ተገደዱ። ሚኒስትር ወረደ ወልድ ወልዴ ደግሞ ሳይገባቸው ለሞቀ ቤታቸው በቁ።

ይህን የሃያ ዓመት ታሪክ ያለምክንያት አላነሳሁትም። ከእልህ አስጨራሽ ህዝባዊ ትግል በኋላ የለውጥ ሽራፊ ለማየት ብንጓጓም ከሃያ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ ለከት ያጣ ግፍ እያስተናገድን ነው። በ”ለውጡ” የመጀመሪያ ወራት ህዝቡ የተራበ አንጀቱን አስሮ ይስቅ የነበረው፣ ድጋፉንም የቸረው ከእንግዲህ በፍትህ ፣ በእውነትና በእኩልነት የምጠግብበት ዘመን ጠባ ብሎ በማመኑ ይመስለኛል። ከፈጣሪ በታች ተስፋችን በእጃችን መሆኑ የቀትር ያህል ግልፅ ቢሆንም፣ ከሃያ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ የፍትህን መጨንገፍን ሳይ ጥልቅ ሀዘን አልተሰማኝም ብል ግን እውነቱን አልናገርም ።

በቅርቡ የኢዜማ ስራ አስፈፃሚ አባል ወይዘሮ ሂሩት ክፍሌ ፍርድ ቤት የዋስትና መብቷን ቢያከብርላትም ፓሊስ ላለመልቀቅ ያሳየውን ዳተኝነት እናስታውሳለን። በተመሳሳይ የአስራት ቴሌብዥን ጋዜጠኞችንም እንዲሁ በመከራ መልቀቁ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።

ዛሬ ብዕሬን እንዳነሳ ያደረገኝ ጉዳይ የአቶ ልደቱ አያሌው ጉዳይ ነው። ስለአቶ ልደቱ ከእኔ በላይ ብዙ ነገሮችን አጣቅሶ ማቅረብ የሚችል ሌላ ማን እንዳለ በእውነት አላውቅም ። በፓርቲዬም ላይ ቢሆን በተደጋጋሚ ምን ያደርጉ እንደነበር ፈፅሞ ዘንግቸው አይደለም። አቋማቸው ከአቋሜ ስለገጠመም አይደለም። ይልቅስ አቶ ልደቱ እራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት በዚህ ሁኔታ አንዳች አሉታዊ ጉዳይ አንስቼ እሞግታቸው ዘንድ ፈፅሞ ህሊናዬ አይፈቅድልኝም።

በተወሰነ መልኩ የቀደመውን ለአንባቤ ያስታወስኩትም ቢሆን፣ የቆምኩበትን የሀሳብ ማዕዘን ለማሳየት ይረዳኝ ዘንድ ግድ ሆኖብኝ እንጂ ምቾት ተሰምቶኝ አይደለም። ይልቅስ ከላይ ከፍ ብዬ ከጠቀስኳቸው ወገኖቻችንም በከፋ ሁኔታ የ”ፓሊስ” ጢባጢቢ መጫወቻ ሆነው ሳይ እርሳቸውን የወጋ ጦር እኔንም እንደወጋኝ ተሰምቶኛል። በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ከእስር እንዲለቀቁ ቢያዙም በፓሊስ እንቢተኝነት ግን በእስር ላይ ይገኛሉ። ውርደቱ፣ መረገጡ፣ንቀቱና ኢፍትሃዊነቱ፣ የኢፍትሃዊነትን ስቃይ ለምናውቅ ዜጎች ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ነው።

በማንኛውም ዜጋ ላይ የሚፈፀም ኢፍትህአዊነት በሁላችንም ላይ እንደተፈፀመ የሚጠራጠር ካለ እርሱ ፍፁም ማስተዋል የጎደለው ነው።

በኢትዮጵያችን እየታየ ያለው ለከት ያጣ ግፍ ቅስም የሚሰብርና በምንም አይነት መንገድ ልንታገሰው የማይገባ ኢፍትሃዊ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ያዋረደ ወደር አልባ የነውረኝነት ተግባርም ነው።

በፈጣሪ እንደምትታመኑ ደጋግማችሁ የነገራችሁን ወገኖች በሚፈፀመው ግፍ ፈጣሪ የሚደሰትበት ይመስላችኋል? የሚሰራውን ኢፍትሃዊነት በአስቸኳይ እስካላስቆማችሁ የፈጣሪም ሆነ የህዝብም ቁጣ እሩቅ እንደማይሆን ለመናገር ነቢይነትን አይጠይቅም።

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top