Connect with us

ሲቪል ሰርቫንቱ የመንግስት የግል ንብረት አይደለም!

ሲቪል ሰርቫንቱ የመንግስት የግል ንብረት አይደለም!
Photo: Social Media

ማህበራዊ

ሲቪል ሰርቫንቱ የመንግስት የግል ንብረት አይደለም!

ሲቪል ሰርቫንቱ የመንግስት የግል ንብረት አይደለም!
(መልካም ይሆናል፣ ለድሬቲዩብ)

ቀደም ሲል መንግስት የሚነሱበትን ቅሬታዎች እና ጥያቄዎች “ተሃድሶ” እና “ጥልቅ ተሃድሶ” የሚሉ ማደንዘዣዎችን ለጊዜ መግዣነት አሟጥጦ ተጠቅሟል፡፡ የህዝብ ጥያቄዎች እና ቅሬታዎች ሞልተው ሲፈሱ ድህረ-ኢህአዴግ ወይም “ለውጥ”ን ወለደ፡፡ አቤት! በዚህ ድህረ-ኢህጨ
ኢህአዴግ የመጀመሪያው ወቅት ተስፋ የሰነቀው ሰው ብዛት!

በተለይም ሲቪል ሰርቫንቱ (የመንግስት ሰራተኛው) ዓመታትን የተሻገሩ እና ያልተመለሱ ጥያቄዎች ስለነበሩት መፍትሄ አገኛለሁ ብሎ በጉጉት ሲጠባበቅ ነበር፡፡ ነገሩ “ስልቻ ቀልቀሎ፤ ቀልቀሎ ስልቻ” ሆነና ለውጡ ስልቱን ቀይሮ በፌስቡክ ፕሮፖጋንዳ ጊዜ ለመግዛት እየተጋ ነው፡፡ የለውጡ አክሮባት “ከምኔው ከምኔው!” ያስብላል፡፡

የሰራተኛው የደመወዝና የጥቅማጥቅም ጥያቄዎች ከለውጡ በኋላም የቀጠሉ መንግስት “የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ” ብሎ ምላሽ ያልሰጣቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች ሆነው ቀጥለዋል፡፡ እንደ ሀገር ያለው የኑሮ ውድነት ከድጡ ወደ ማጡ ሆኗል፡፡ መንግስት የኑሮ ጫናው በሰራተኛው ህልውና ላይ እስኪመጣ ቆሞ ከማየት አልፎ ችግሩ ላይ ቤንዚን በማርከፈከፍ ይበልጥ እያፋፋመው ነው፡፡

በእርግጥ በኑሮ ውድነቱ የሚጎዳው የመንግስት ሰራተኛው ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ግን ቢያንስ የመንግስት ሰራተኛውን ጥያቄዎች ለመፍታት ፍንጭ ማሳየት መጀመር አለበት፡፡ ምክንያቱም መንግስት “ቀበሌ ስትመጣ በ5 ደቂቃ መታወቂያ ልሰጥህ ነው፣ የቤት ባለቤት ላደርግህ ነው፣ ዳቦ ላድልህ ነው” ብሎ ሲደሰኩር የመንግስት ሰራተኛውን ይዞ ነው፡፡

መንግስት በህዝብ ዘንድ የሚኖረው አመኔታ እና ቅቡልነት የሚወሰነው ቃሉን ሲያከብር ነው፡፡ ተጨባጭ ውጤቶች እንዲመጡ የሲቪል ሰርቪስ የሪፎርም ስራዎች በፍጥነት መከናወን ነበረባቸው፡፡ ፖለቲካውና የህዝብ አገልግሎቱ (ሲቪል ሰርቪሱ) ያለቅጥ ሆን ተብሎም ይሁን ባለማወቅ ከልክ በላይ ተቀላቅሎ ፖለቲካው የህዝብ አገልግሎቱ ውስጥ ዘልቆ ገብቷል፡፡ አሁንም የህዝብ ተቋማት ውስጥ የገዢው ፓርቲ ስብሰባዎች ይካሄዳሉ፡፡ ሁሉ ነገር የተበላሸው እዚሁ ላይ ነው፡፡

መንግስት የሪፎርም ስራውን ለመስራት አመላካች ነገሮች የሉም፡፡ ከሪፎርም ስራው ይልቅ የሰው ኃይል ላይ መሰራት ሲገባው ቢሮ የማሳመር፣ ለሹማምንቱ ከቪ8 በተጨማሪ አዳዲስ መኪኖችን መግዛትና የቤት አበል ማሻሻል ስራ ላይ ተጠመደ፡፡ የሲቪል (ፐብሊክ) ሰርቪስ ሚኒስቴር ያጠናክረዋል ተብሎ ሲጠበቅ ጭራሽ ወደ ኮሚሽን ዝቅ አደረገው፡፡ እነዚህ እንግዲህ የመንግስት ሰራተኛው “የለውጡ አቧራ” ብቻ ተቋዳሽ ሆኖ መቅረቱ ማሳያዎች ናቸው፡፡

ዛሬም ሹማምንቱ ለአለቆቻቸው እጅ መንሻ የሚያቀርቡት የሰራተኛውን ደመወዝ ሆኗል፡፡ ሰራተኛው የደመወዝ ማሻሻያ ወይም ጭማሪ ሲጠብቅ ያለፍላጎቱ ከስፖርት እስከ ፓርክ ከወር ደመወዙ ያለማንም ሃይ ባይ ይቆርጣል፡፡ ለይምሰል ሰራተኞች ለ”ሆነ ገበታ ፕሮጀክት ደመወዛቸውን ለመስጠት ተስማሙ” የሚል ዜና ቴሌቪዥኑ፣ ሬድዮው እና ፌስቡኩ እንዲያጨናንቀው ይደረጋል፡፡ እውነታው ግን ገበታው ባዶ የሆነበት ሰራተኛ ደመወዙን ለመስጠት የሚስማሙት የመንግስት ጋሻጃግሬዎች ናቸው፡፡ ለዚያውም የተቆረጠው ደመወዝ በቦንድ መልክ ለሰራተኛው ሊመለስ በማይችልበት ሁኔታ ነው ደመወዛቸውን ለመስጠት ተስማሙ ተብሎ ዜና የሚሰራበት፡፡

ከዚህ በፊት ሰራተኛው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተደጋጋሚ ከወር ደመወዙ ሲቆርጥበት ቢያንስ ቦንድ በመግዛትና ወለድ ጭምር ታስቦለት የተተገበረ ነው፡፡ ይህ በንፅፅር የተሻለ የሚባል ነበር፡፡ አሁን ግን የሰራተኛውን የኑሮ ሁኔታ ታሳቢ ያላደረገ ፣ በጥናት ላይ ያልተመሰረተ እና የሰራተኛው ፍላጎት ጭምር ያልተጠየቀበት ነው፡፡

አንድ ኪሎ ጤፍ 30 ብር ሲሸጥና አሁን 58 ብር ሲደርስ የሰራተኛው ደመወዝ ተመሳሳይ ነው፡፡ አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት 15 ብር እያለ እና 30 ብር ሲደርስ የሰራተኛው ደመወዝ ከነበረበት ፈቀቅ አላለም፡፡

መንግስት ራሱ እንኳን ለእኩል ስራ እኩል ደመወዝ (JEG) ክፍያ ብሎ ያጠናው ጥናት እንኳን ቃሉን ጠብቆ ሊተገብረው አልቻለም፡፡ ሰራተኞች የስም ለውጥ ያለው ደረጃ ብቻ ተሰጥቷቸው ደመወዝ ሳይስተካከልላቸው በዱቤ ጭምር እየሰሩ ነው፡፡ የሰራተኛውን ጥያቄ መልስ ሲባል እንደ ኤሊ የሚያዘግመው መንግስት ደመወዝ ለመቁረጥ እንደ “ዩዜንቦልት” ይወረወራል፡፡
በዚህ ሁኔታ አፍንጫው ስር ሆነው የሚያስተዳድራቸውን ሰራተኞች ቅሬታ መፍታት ያልቻለ መንግስት የዜጎችና የግሉ ዘርፍ ሰራተኞች መብት ያስከብራል ማለት ቅዠት ነው፡፡

በጣም አሳዛኙ ክስተት በየሁለት ዓመቱ በህግ የተፈቀደለት የእርከን ጭማሪ እንኳን የሚያከብርለት መንግሰት እስካሁን አልተገኘም፡፡ ሰራተኛው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለማግኘት መንግስት ላይ ጫና እንዳያሳድር የመደራጀት መብት ተነፍጎት ቅሬታውን በተናጥል ለማቅረብ እየተገደደ ነው፡፡ ሰራተኛውን የሚወክል ማህበር እንዲመሰረት መንግስት ፍላጉቱም የለውም፡፡

ሰራተኛው በአነስተኛ ደመወዙ ምክንያት መታመን እንኳን አልቻለም፡፡ “እየሰራቃችሁ ካልሆነ በዚህ ደመወዝ መኖር አትችሉም” የሚባልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ አሁን በሚከፈለው የደመወዝ መጠን “መኖር አይቻልም” ቢባል ለምን ይገርማል?!

ከዚህ የባሰው የመንግስት ሰራተኛው ትክክለኛ ግብር ከፋይ ቢሆንም አሁንም ተደራራቢ ታክስ የመክፈል ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ ታክስ ከፍሎ የቀረው የተጣራ ደመወዙ ላይ አስቤዛ ሲሸምት እንኳን ታክስ መክፈል አለበት፡፡ እንደ ነጋዴው ላወጣው ወጪ ወይም ለገዛው ዕቃ የታክስ ተመላሽ የሚያገኝበት አሰራር አይታወቅም፡፡

ይህ ብቻ አይደለም አንድ መካከለኛ ደመወዝ የሚከፈለው የመንግስት ሰራተኛ እና በትላልቅ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች በተመሳሳይ ምጣኔ ግብር ይከፍላሉ፡፡ አንድ ትክክለኛ ግብር የሚከፍል የመንግስት ሰራተኛ እና የህንፃ መሳሪያ ነጋዴ ተመሳሳይ ታክስ የሚከፍሉበት ሀገር ነው የምንኖረው፡፡

ሰራተኛው ለሀገሩ ቀናኢ አመለካከት ያለው፤ ሀገሩ እንድትለማለት እንድትለወጥለት የሚፈልግ ዜጋ ነው፡፡ ልማቱ እና እንድትኖረን የምንመኛት ሀገር መፍጠር ይቻላል፡፡ ነገር ግን ስራችን ተቋማዊ ሆኖ በዕቅድ የሚመራ፣ እርስ በርሱ የሚናበብ እና ቅደም ተከተል ያለው ሊሆን ይገባል፡፡ ለስራችን የሚያስፈልገን ሀብት ማሰባሰብ ብቻ ሳይሆን ሳይባክን ስራ ላይ መዋሉን እርግጠኞች መሆን አለብን፡፡

ግን ይህ ሲሆን አይታይም፡፡ መንግስት ከፍተኛ ሀብት የሚጠይቁ ስራዎች “በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ አመንጪነት” እየተባለ ከላይ እንደ ዝናብ ሲያዘንብብን ነው የሚታየው፡፡ የብር ኖት የፌዴራል ፖሊስ ዩኒፎርም መቀየሩን፣ የፓርክ ፍላጎቱም፣ ግድቡንም ሌላም ሌላም በአንድ ጊዜ ልስራው እያለ ነው፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ለዚያውም ከወጪ ንግድ 3 ቢሊዮን ዶላር እንኳን ለማግኘት እየተንገዳገደች በምትገኝ እና 300 ቢሊዮን ብር እንኳን የታክስ ገቢ ማመንጨት ያልቻለች ሀገር፤ በግድቡ ምክንያት ቃል የተገባላት እርዳታና ብድር እንደ መደራደሪያ ለሚቀርብላት ሀገር፡፡

85 በመቶ አርሶአደር ይዛ በምግብ ራስን መቻል እንደ ሰማይ ለራቃት እና የውጭ እርዳታ እና ብድር ቢቋረጥባት ለሰራተኛ ደመወዝ መክፈል ለማትችል ሀገር ፓርክ ነው የሚቀድመው ትራክተር? ካለፉት 50 ዓመታት ጀምሮ ስንዴ ከውጭ ለምታስገባ ለዚህች ድሃ ሀገር በቢሊዮን አውጥቶ ፓርክ ከመገንባት በምትኩ ትራክተር ቢገዛበት የተሻለ ገቢ አያስገኝላትም?!

በዚያ ላይ በመንግስት የተያዙ ይዞታዎች ወደ ግሉ ዘርፍ እንዲተላለፉ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጫና እየተደረገበት ባለበት ወቅት መንግስት በግል ዘርፍ መልማት የሚችሉት ካልሰራው እያለ የሚታገለው ለምንድነው?!

በአፍሪካ መዲና በሆነች ከተማ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ባለመዳረሱ እኮ ነው ነዋሪው ጀሪካን አንጠልጥሎ ውሃ ፍለጋ የሚንከራተተው፡፡ መንግስት ግን ፓርክ ውስጥ ወደ ሰማይ የሚተኮስ ውሃ እየሰራ ሊያስደምመን የሚሞክረው፡፡
ህዝቡ ማገዶ ትተህ ታዳሽ ኃይል ተጠቀም እየተባለ ኤሌክትሪክ በቅጡ መብራት የማያገኝ ምስኪን እኮ ነው፡፡ ፓርክ ውስጥ ግን በመብራት ለማሽቆጥቆጥ ገንዘብ ይበትናል፡፡

ስርዓት አልበኛውን አደብ ማስገዛት አይቀድምም?! እነዚህን መሰረታዊና ጊዜ የማይሰጡ የቤት ስራዎቹን ቢሰራ መልካም ነበር፡፡
ሰላም ማስፈን ላይ ትኩረቱን አድርጎ የታክስ ማበረታቻዎች እየሰጠ የግሉ ዘርፍ ወደ ስራ እንዲገባ ማበረታታት እየተቻለ፡፡
እሺ! ችግራችንን ዋጥ አድርገን ሀብት አሰባስበን እንሰራዋለን እንበል፡፡ የተሰበሰበውን ሀብት በየቦታው የሚያፈሱ ኪሶችን ለመድፈን መንግስት ለምን ቁርጠኝነት ያንሰዋል? ድግስ ከሌለ ስብሰባ የማይታይቻው ካድሬዎቹ አደብ ማስገዛት አቅቶታል፡፡

ግዙፍና የተበላሸ ግዥ በሽ ነው፡፡ በቅርቡ እንኳን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ለቤት ቆጠራ በሚል ሰበብ ያስገዛቸው 900 ሚሊዮን ብር የሚያወጣው ታብሌት ግዢ ውሃ ሲበላው ተመልከተናል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር በመፅሐፍ ህትመት ሽፋን ያባከነው ሀብት እንዲሁ ተወርቶ መቅረት ያለበት አልነበረም፡፡ በውጭ ግዥ ሰበብ የሚበዘበዘው የሀገር ሀብት የትየለሌ እየሆነ ነው፡፡ ኦዲተሩም ፀረ-ሙስናውም ዝም ብለዋል፡፡

ይህ ሁሉ ችግር ባለበት መንግስት ባንክ እንዳስቀመጠው ገንዘብ የሰራተኛ ኪስ ሲያይ ሰራተኛው ቅሬታ ቢፈጠርበት ምን ይገርማል!

ሲቪል ሰርቫንቱ የህዝብ አገልጋዮች እንጂ የመንግስት የግል ንብረቶቹ አይደሉም፡፡ የሚከፍለው ደመወዝ በመንግስት ችሮታ የሚሰጡ ሳይሆን ለሰሩት ስራ (ምንም እንኳን በቂ ባይሆን) የሚከፈል አይደለምን?!

ሰራተኛውን የገዢው ፓርቲ ደጋፊ አድርጎ የማየት አባዜም እንደቀጠለ ነው፡፡ ሰራተኛው የመንግስት ፖሊሲ የማስፈፀም ኃላፊነት ቢኖርበትም የፈለገውን የፖለቲካ ፓርቲ የመምረጥ መብት እንዳለው ባይዘነጋ፡፡ ፖለቲካው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችል ኃይል እንደሆነም እንደዚሁ፡፡

(ማስታወሻ:- በዚህ ጽሁፍ የተንፀባረቀው አቋም የፀሐፊውን እንጂ የድሬቲዩብ ኤዲቶሪያል አቋም የሚያሳይ አይደለም)

Click to comment

More in ማህበራዊ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top