Connect with us

በቤኒሻንጉል ጥቃት የፈጸሙ ታጣቂዎችና ተባባሪዎችን ለመያዝ ልዩ ኦፕሬሽን ተጀመረ

በቤኒሻንጉል ጥቃት የፈጸሙ ታጣቂዎችና ተባባሪዎችን ለመያዝ ልዩ ኦፕሬሽን ተጀመረ

ህግና ስርዓት

በቤኒሻንጉል ጥቃት የፈጸሙ ታጣቂዎችና ተባባሪዎችን ለመያዝ ልዩ ኦፕሬሽን ተጀመረ

ኦፕሬሽኑ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ በኋላ በተሰነዘረ ጥቃት 15 ሰዎች መገደላቸው ተሰማ

ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በነዋሪዎች ላይ ግድያና ዕገታ የፈጸሙ ታጣቂዎችንና ተባባሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል፣ በፌዴራል መንግሥት የታገዘ ልዩ ኦፕሬሽን ተጀመረ።

ልዩ ኦፕሬሽኑ እንዲቋቋምና ሥምሪት እንዲጀመር ትዕዛዝ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መሆናቸው ተገልጿል፡፡ የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የክልሉ የፀጥታ ኃይል በጥምረት የተሰማሩበት እንደሆነም ታውቋል፡፡

ልዩ ኦፕሬሽኑን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በዋናነት እንደሚከታተለውም የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

እስካሁን በተደረገው ኦፕሬሽን በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን፣ የክልሉ መንግሥት የፀጥታና የአስተዳደር መዋቅር የተወሰኑ አካላትም በግጭቱ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታውቋል።

በተለይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች በተሰነዘሩበት መተከል ዞን ያለውን ሁኔታ ለመግታት, በክልሉ መንግሥት የሚመራ የፀጥታ ኮማንድ ፖስት የተዋቀረ ሲሆን፣ ዞኑም ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት በኮማንድ ፖስቱ ሥር እንደሚቆይ ታውቋል።

በመተከል ዞን የሚገኙ ተደጋጋሚ ግጭቶች የተከሰቱባቸው ወረዳዎች ጉባ፣ ቡለን፣ ዳንጉርና ወምበራ የሚኖረው የፀጥታ ኮማንድ ፖስት, በአጠቃላይ የመከላከያ ሠራዊት የሚሰማራበትና የሚመራው እንደሚሆንም የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኮማንድ ፖስቱ ፀንቶ በሚቆይባቸው ወራት ውስጥ በመተከል ዞን የጦር መሣሪያዎችንና ማናቸውንም ስለታማ ነገሮችን ይዞ መንቀሳቀስ መከልከሉም ተገልጿል።

በየኬላዎችም ጠንካራ ፍተሻዎች እንደሚከናወኑ፣ እንዳስፈላጊነቱም የሰዓት ዕላፊ ሊጣል እንደሚችል መረጃው ያመለክታል።

ይህ ቢሆንም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዓርብ መስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በድጋሚ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ የ15 ሰዎች ሕይወት ማለፉን አስታውቋል።

ጥቃቱ የተሰነዘረው ልዩ ኦፕሬሽኑ ተግባራዊ መደረግ በጀመረ በማግሥቱ መሆኑም ታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ ክስተቱ በአካባቢው ያለው ችግር በእጅጉ አሳሳቢ እንደሆነ ያሳያል ብሏል።

መስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም ከንጋቱ 11 ሰዓት ገደማ በመተከል ዞን፣ ዳንጉር ወረዳ፣ ማንቡክ ከተማ በንገዝ ወንዝ አካባቢ በሚገኝ መንደር በታጠቁ ሰዎች በተከፈተ ተኩስ የ15 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ኮሚሽኑ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡

በዕለቱ እስከ ቀኑ 8፡00 ሰዓት ድረስ በተሰበሰበ መረጃ 15 ያልታጠቁ ሲቪል ሰዎች ሕይወት ማለፉንና ከሟቾች መካከልም 11 ወንዶችና አራት ሴቶች መሆናቸውን በአካባቢው ካሉ የመንግሥት ምንጮች ኮሚሽኑ ማረጋጡን ገልጿል፡፡ የሟቾች ዕድሜ እስካሁን ያልተለየ ሲሆን፣ በተጨማሪም አንድ ሰው ለሕይወት የማያሠጋ ጉዳት እንደ ደረሰበት ተመሳሳይ ምንጮች ለኮሚሽኑ መግለጻቸውን አመልክቷል፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊት አሁንም የተጎዱ ሰዎችን ለማፈላለግ አሰሳ እያካሄደ እንደሆነና ምናልባት የተጎዱ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ሥጋት መኖሩንም ጠቁሟል።

እስካሁን ያሉ መረጃዎች ጥቃቱ የተፈጸመው በሕገወጥ ታጣቂዎች እንደሆነ የሚያመለክቱ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ በደረሰው መረጃ መሠረት ታጣቂዎቹ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር የተኩስ ልውውጥ ካካሄዱ በኋላ ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ላይ የመከላከያ ሠራዊት አካባቢውን እንደ ተቆጣጠረ መረጃ ማግኘቱንም አስታውቋል።(ዮሐንስ አንበርብር ~ ሪፖርተር)

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top