Connect with us

የአርቲስት አልማዝ ኃይሌ አጭር የህይወት ታሪክ

የአርቲስት አልማዝ ኃይሌ አጭር የህይወት ታሪክ
Photo: Social Media

ጥበብና ባህል

የአርቲስት አልማዝ ኃይሌ አጭር የህይወት ታሪክ

የአርቲስት አልማዝ ኃይሌ አጭር የህይወት ታሪክ

አርቲስት አልማዝ ኃይሌ(ማሚ) ከአባቷ አቶ ኃይሌ ዑርጌ እና ከእናቷ ወ/ሮ የሺ ሰይፉ መስከረም 01 ቀን 1938 ዓ.ም በቀድሞው ሀረር ክፍለሀገር ልዩ ስሙ አሰበተፈሪ ተወለደች፡፡ በተፈሪ መኮንን ት/ቤት እስከ 8ኛ ክፍል ተምራለች፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ከተቀጠረችበት ታህሳስ 08 ቀን 1958 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥር 30 ቀን 1993 ዓ.ም ድረስ ለ35 ዓመታት በሀገር ባህል ተወዛዋዥነት፣ በተዋናይነት፣ በድምጻዊነት፣ በሜክአፕና ማስክ ሰራተኝነት አገልግላለች፡፡ እንዲሁም ከመደበኛ ስራዋ ጎን ለጎን አልባሳትን በመጠገን በተለያዩ መድረኮች የገጽ ቅብ ስራዎችን በመስራት በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትና ተደናቂነትን ያተረፈች ሲሆን በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ ያበረከተችው አስተዋጽኦ በህሊናችን ውስጥ ተቀርጸው የቀሩ ናቸው፡፡

ከየካቲት 01 ቀን 1993 ዓ.ም ጀምሮ በጡረታ የተሰናበተችው አርቲስት አልማዝ ኃይሌ ለሙያዋ ምን ያህል ክብር እንደምትሰጥ ማሳያ ከሆኑት ተግባራቶቿ መካከል ሰኔ 22 ቀን 1991 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የተጻፈው የምስጋና ደብዳቤ እንዲህ ይላል፡፡

“ሚያዝያ 30 ቀን 1991 ዓ.ም “ጉማ” የተሰኘው ቴአትር ለህዝብ በሚቀርብበት ጊዜ የእናትዎን ማረፍ ሰምተው ትርኢቱ ከሚስተጓጎል ሀዘኔን በውስጤ ችዬ ቴአትሩን እሰራለሁ ብለው በመወሰን አንዳችም ነገር ሳይጓደል በብቃት እንደተወጡት፣ ከዚህም በተጨማሪ በእንክብካቤ ያሳድጉት የነበረው የልጅዎት ልጅ በህጻንነት እድሜው ከዚህ ዓለም በሞት በተለየ በሶስተኛው ቀን ግንቦት 25 ቀን 1991 ዓ.ም “ጉማ” ቴአትር ለህዝብ በሚቀርብበት ጊዜ ከመራር ሀዘንዎት ላይ ተነስተው ቴአትሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ማድረግዎን ከጉማ ቴአትር ዋና አዘጋጅ ሰኔ 14 ቀን 1991 ዓ.ም ሪፖርት ተደርጓል፡፡

በመሆኑም በሁለቱም ቀናቶች የእናትዎንና የልጅ ልጅዎን ሀዘን በመቻል ያከናወኑት ተግባር አርአያነቱ እጅግ የላቀ በመሆኑ የተሰማንን አድናቆትና ምስጋና እየገለጽን ቸሩ አምላክ ለእርስዎና ለቤተሰብዎ መጽናናትን እንዲሰጣችሁ ከልብ እንመኛለን፡፡ ” ይላል፡፡ ይህም ኪነ-ጥበባዊ የሙያ ሥነ-ምግባርን ማሚ እንዴት እንደተወጣችውና ለትውልድ ማስተማሪያነት እንደሚያገለግል ያሳያል፡፡

በበዓላት ቀናት እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ ጭምር ሳይቀር ከመስራቷም በላይ ከስራ ባልደረቦቿ ጋር በመግባባት የስራ ኃላፊነቷን በብቃት የተወጣች ባለሙያም ነበረች፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በሚያዘጋጃቸው እንደ 60ኛ ዓመት ክብረ-በዓል እና ሌሎች ዝግጅቶች ላይ በሙሉ ፍቃደኝነት በመገኘት ታላቅነቷን አሳይታለች፡፡ አርቲስቷ ከ40 ዓመት በላይ በኪነ ጥበቡ ዓለም በመቆየት በርካታ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎችን አበርክታለች። ከብሔራዊ ቴአትር ቤት ተሳትፎዋ ባሻገር በበርካታ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራሞች፣ ፊልሞች እና ማስታወቂያዎች ላይ ተሳትፎ አድርጋለች፡፡

አርቲስት አልማዝ ኃይሌ በሀገር ውስጥ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር፣ ከአቶ ሽመልስ ማዘንጊያ እጅ ሰርተፊኬት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ምስረታ መቶኛ ዓመት መታሰቢያ ላያ የአድዋ ዘመቻ መታሰቢያ ድልድይ ምረቃ ትርኢት ግብረኃይል አባል ሆና በመስራቷ የምስክር ወረቀት፣ በውጪ ሀገር ደረጃ ከፕሬዘዳንት ሴንጎር የምስክር ወረቀት እንዲሁም ከፕሬዘዳንት ቡሚዲያን እጅ የነሀስ ሜዳሊያ ተሸልማለች፡፡

አንጋፋና ታዋቂ አርቲስት አልማዝ ኃይሌ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ሶማሊኛ፣ እንግሊዝኛና አረብኛ ቋንቋን የምትችል፣ በስራዋ ጠንካራ፣ ሰውን አክባሪ፣ ቅን እና ታታሪ ባለሙያ የነበረች ሲሆን የ 4 ልጆች እናትም ነበረች፡፡

በበርካታ የቴአትርና ፊልም ስራዎች የምትታወቀው አንጋፋዋ አርቲስት አልማዝ ኃይሌ (ማሚ) ያጋጠማትን ጤና ማጣት ለመታከም በህክምና ብታሳልፍም መስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡ የቀብር ስነስርአቷም ዛሬ መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 6:00 ሰአት አብዛኛው ህይወቷን ባሳለፈችበትና ዘውትር ጸሎቷን ታደርስበት በነበረው በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ይፈጸማል!!!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በአርቲስት አልማዝ ኃይሌ ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ ለመላው የጥበብ አፍቃሪያን፣ ለወዳጅ ዘመዶቿ፣ ለቤተሰቦቿ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ይመኛል፡፡

(የኢት. ብሔራዊ ቲያትር)

Continue Reading
Click to comment

More in ጥበብና ባህል

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top