Connect with us

ከዚህ በኋላ ገዳዮች ሞት ምን ያህል አስከፊ እና መራር እንደሆነ የሚቀምሱበት …

"ከዚህ በኋላ መሞት ብቻ ሳይሆን ገዳዮች ሞት ምን ያህል አስከፊ እና መራር እንደሆነም የሚቀምሱበት ጊዜም ይሆናል"
Photo: Social Media

ህግና ስርዓት

ከዚህ በኋላ ገዳዮች ሞት ምን ያህል አስከፊ እና መራር እንደሆነ የሚቀምሱበት …

“ከዚህ በኋላ መሞት ብቻ ሳይሆን ገዳዮች ሞት ምን ያህል አስከፊ እና መራር እንደሆነም የሚቀምሱበት ጊዜም ይሆናል”

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የመስቀል በዓልን አስመልክቶ መልእክት አስተላልፈዋል ሙሉ መልእክቱን እነሆ:-

መልካም የመስቀል ደመራ በዓል ለሁላችን ይሁንልን!

‹‹… የመጣንበት የእሳት መንገድ በደመራ ችቦ ብርሃን እንዲያበቃ ህዝባችን ለጥምር ተልዕኮ መዘጋጀት ይጠበቅበታል …›› !!

የተከበራችሁ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትኖሩ የክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን !!

በቅድሚያ እንኳን ለ2013 ዓ.ም የደመራ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቴን ለመግለጥ እወዳለሁ !!
የደመራ በዓል በአማራ ክልልና በመላው የሀገራችን ክፍል እንደ ጥምር በዓል የሚታይ ነው ፡፡ የኃይማኖታዊና ባህላዊ የአደባባይ ስርዓተ-ዐምልኮ የሚፈጸምበት፤ የሀገራችን ዘርፈ ብዙ ትውፊቶች እና ሚስጥራት የተገለጡበት ዓለማቀፋዊ ዕውቅና የተቸረው ዘመን ተሸጋሪ ክብረ-በዓል ነው ፡፡

‹‹የመስቀል ደመራ በዓል›› ከዓለም የቱሪዝም ቀን ጋር የሚከበር መሆኑም የበዓሉን እሴቶች በቱሪዝም ዘርፍ ኃብት በማመንጨት እንደርስበታለን ላልነው ‹‹የብልጽግና ጉዞ›› ስንቅ የሚሆን ጸጋንም የተላበሰ ነው ፡፡

ይህን መሰል ኃብት ጨምሮ ሌሎችንም ዘመናትን የተሻገሩ ጸጋዎቻችንን ለማጥፋት ሀገራዊ ‹‹ዋልታዎችን›› ለማፍረስ ታሳቢ አድርገው የሚሰሩ እኩያን የህዝቦችን ደስታ በመንጠቅ ሐሴትን ለማግኘት ይጥራሉ። በእጅ አዙር የገዟቸውን ኃሳይ መሲዎችም በቻሉትና በተመቻቸው ቦታ ሁሉ ይጋልቧቸዋል:: መላው ሰላም ወዳድ ህዝባችን ግን የትኛውም ተራራማ መከራ ቢቆለልበት እንደመስቀሉ በተዓምራት ችግሮቹን ሁሉ ፈንቅሎ እንደሚሻገር ከልቡ ያምናል።

የዘንድሮውን ‹‹የመስቀል ደመራ በዓልን›› ስናከበር በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በተሟላ ገጽታው እንዳልሆነ ይታወቃል ፡፡ ስለሆነም የዘመኑን የጥበብ ምጥቀት ተጠቅመን መገናኛ ብዙኃን የሚያስተላልፉትን የቀጥታ ስርጭት መታደም ግድ ይላል፡፡

ደመራ ከ300 ዓመታት በላይ በቆሻሻ ክምር ተቀብሮ የነበረውን መስቀል በእምነት ጽናት የቆመችው ‹‹ንግስት ኢሌኒ›› አስቆፍራ በማግኘት ደስታዋን ሙሉ አድርጋለች፡፡ የእኛ ‹‹የብልጽግና ጉዞም›› ታላቁን ህዝባችንን በተዛባ የታሪክ አስተምህሮ አቆሽሸው፤ በብልጽግና ጉዞ ያገኘነው ደስታ ሙሉ እንዳይሆን ህዝቦችን አስተሳስሮ ያኖረውን የእምነት፣ የባህልና የስርዓት መሰረትን ለማምከን ቀንከሌት የሚጥሩትን አካላት መሰሪ ሚስጥራቸውን በአደባባይ ያጋለጠ ነው ፡፡

ለዚህም የዘንድሮው ሀገር አቀፍ የቱሪዝም ቀን የለውጡ ፍሬ በሆነችው በ10ኛዋ የሲዳማ ክልል በተከበረበት ፤ ስንጥር በመፈለግ የኃይማኖትና ብሔር ግጭቶችን የሚመኙ አካላት መቆሚያ እንዲያጡ በተሰራበት ፣ የኮቪድ 19 በሽታ ተግዳሮቶችን ለመመከት የሚያስችሉ አቅሞች በገነባንበት፣ የዓባይ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውኃ ሙሌትን ጨምሮ ሌሎች መጀመር ብቻ ሳይሆን አቀላጥፎ ማጠናቀቅን እንደምንችል ያሳየንባቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በተግባር ተምሳሌትነትን ባገኘንበት ማግስት የሚከበረው የዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል ካለፉት ክብረ-በዓላት ሁሉ ልዩ ነው ፡፡

ክቡራንና ክቡራት !!
በዓሉ የጽናትና የቃል- ኪዳን መሰረት ነው ፡፡ ይህን መሰረት የሚያናጉ አካላት አስካሁን የፈጸሟቸው እኩይና ነውረኛ ተግባራት አልበቃቸው ብሏል ፡፡
የስልጣን ጥመኞች ‹‹ህዝባችንን በተራበ ቀበሮ ከተከበበ ጎሽ ጋር›› በሚመሳሰል ሁኔታ በየአቅጣጫው ከበው ለዳግም ጥፋት ለመዳረግ ከመስከረም ወር በኋላ መንግስት የለም የሚል መርዘኛ ትርክት ውስጥ ገብተዋል ፡፡ ይህን የመንታ ምላስ ትርክት ቀርቶ ‹‹ምስጋና ለለውጡ ይሁንና ›› ሌላውንም እሾኃማ መንገድ አልፈነዋል፡፡

ለውጡ እሾህ አልባ ጽጌረዳ ብቻ ይዞልን አልመጣም ፡፡ በጽጌረዳዋ እንደ አደይ አበባ የፈካ የመኖሩን ያህል ፤ ለውጡ በነበሩ እሴቶች ላይ መጨመርን ታሳቢ ያደረገ ‹‹ሪፎርም›› እንደመሆኑ መጠን ፤ ለውጡ ይዞት በመጣው የጽጌረዳ እሾህ ተወግተው የተለዩን እንዲበዙም አድርጓል ፡፡

‹‹የመሰቀል ደመራ›› በዓልን ተከትለው የሚመጡ ህዝባዊ በዓላትም መሰረታቸውን ሳይለቁ በደስታ እንዲከበሩ ‹‹ ደመራን ስናከብር !! የመጣንበት የእሳት መንገድ በደመራ ችቦ ብርሃን እንዲያበቃ ህዝባችን ለጥምር ተልዕኮ መዘጋጀት እንደሚጠበቅበት የምናስገነዝብበት ጭምር ነው›› !!

ከዚህ በኋላ መሞት ብቻ ሳይሆን ገዳዮች ሞት ምን ያህል አስከፊ እና መራር እንደሆነም የሚቀምሱበት ጊዜም ይሆናል::

በድጋሜ መልካም የመስቀል ደመራ በዓል እንዲሆንልን እየተመኘሁ በለውጡ የጽጌረዳ እሾህ ተወግታችሁ መርዙ ህይወታችሁን ለነጠቃችሁ ሰማዕታት ወገኖቻችን ነፍሳችሁን በአጸደ-ገነት እንዲያኖርልን እየፀለይኩ፤ ለመላው ህዝባችንም መጽናናትን እመኛለሁ !!

ተመስገን ጥሩነህ
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር
መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም
ባህር ዳር

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top