ለህዳሴ ግድብ በነሐሴ ወር ከ152 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ
. ኢዜማ ለግድቡ የ500 ሺ ብር ስጦታ ማበርከቱ ዛሬ ይፋ ይደረጋል
አዲስ አበባ፡- ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝቡ በነሐሴ ወር ብቻ ከ152 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት አስታወቀ።የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ለግድቡ ግንባታ 500 ሺህ ብር ስጦታ ማድረጉንም ገለጸ።
የፅህፈት ቤቱ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ለግድቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሏል።በተለይ ከመጀመሪያው ውሃ ሙሌት በኋላ በየወሩ የሚደረገው ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።
በነሐሴ ወር ብቻ ከ152 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ ፣የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሶስተኛው ዙር ለስድስት ወር ከተሰበሰበው የ8100 ኤ ደግሞ ነሐሴን ጨምሮ ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ ነው።ወደ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ህዝብ ደግሞ ሰብስክራይብ አድርጓል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ውስጥ ሐምሌ ወር ላይ የተዋጣው 119 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር እንደነበረ ጠቁመው ፣ ነሐሴ ላይ ከ152 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉ በግድቡ ዙሪያ የተፈጠረ መነቃቃት መኖሩን አመላካች ነው ብለዋል።አጠቃላይ ያለው የሕዝብ ድጋፍም በገንዘብ ሲታይ በቦንድም በስጦታም እየጨመረ መምጣቱን አመልክተዋል።
ከውሃ ሙሌቱ በኋላ ህጻናቱ ወላጆቻቸውን ብሎም ጎረቤቶቻቸውንም ጭምር ቦንድ እያስገዙና እያስተባበሩ እንደሚገኙ ገልጸው ፣ ከእነዚህ ህጻናት ወደ 180 ሺህ ብር ያህል የቦንድ ግዥ መካሄዱን አስታውቀዋል።
ጽህፈት ቤቱ በ2012 ዓ.ም ወደ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ 745 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ገልጸው ፣ በዚህ ዓመት ደግሞ የውሃ ሙሌቱ የፈጠረውን መነቃቃት ከግምት ውስጥ በማስገባት ከሁለት ቢሊዮን እስከ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን አመልክተዋል። ለዚህም በምክንያነት የተቀመጠው ዘንድሮ መላውን ህዝብ የሚያነቃቁ የመጀመሪያ የኃይል ማመንጨት ሙከራን ጭምር በርካታ ስራዎች ስለሚሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይ 8100 አጠናክረን እንቀጥላለን ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ይህም የሆነበት ምክንያት ከንኪኪ ነጻ የሆነ የድጋፍ መስጫ መንገድ ስለሆነ ነው ብለዋል።ከዛ ውጭ ደግሞ እንደሁኔታው እየታየ የተለያዩ መድረኮች የሚዘጋጁ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ኢዜማ 500 ሺህ ብር ለግድቡ ግንባታ ስጦታ ማድረጉን በዛሬው እለት ይፋ እንደሚደረግ ጠቁመው፤ በተጨማሪም በውጭ አገር የሚኖሩ አንድ አባት በአውሮፓ በተለያዩ አገር የሚኖሩ ልጆቻቸው ልከውላቸው የገዙትን የ500ሺ ብር ቦንድ ገቢ ማድረጋቸውን አሳውቀዋል።
በመላ አገሪቱና ከአገር ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ድጋፍ እያረጉ እንደሚገኙም አመልክተዋል።
አቶ ኃይሉ እንዳሉት፤ በአሁኑ ሰዓት የውሃ ሙሌቱ የነበረውን ጥርጣሬ አስወግዶ በህዝብ ዘንድ መተማመንን ፈጥሯል።ከአሁን በኋላ ግድቡን መሙላትና መጠቀም እንደሚቻልም ተረጋግጧል።በመሆኑም በዚህ ዓመት ብዙ ድጋፍ ከህዝቡ ይጠበቃል።
ለግድቡ እስካሁን 121 ቢሊዮን ብር መውጣቱ ይታወሳል።ድግቡ ከሚያስፈልገው 160 ቢሊዮን ብር አንጻር ወደ 40 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልጋል።
ከዚህ ውስጥ ከ15 እስከ በመቶው ከህዝብ የሚጠበቅ ነው።ድጋፉ በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ ሊሰበሰብ እንደሚገባ አመልክተውዋል።ከዚህ የተነሳም 2013 ዓ.ም ከመቼውም ጊዜ በላይ መስራትና ገንዘብ መሰበሰብን እንደሚጠይቅ አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 12/2013