Connect with us

ፓለቲከኛው ልደቱ አያሌው ምን ያህል ቅጣት ሊጠብቃቸው ይችላል?

ፓለቲከኛው ልደቱ አያሌው ምን ያህል ቅጣት ሊጠብቃቸው ይችላል?
Photo: Social media

ዜና

ፓለቲከኛው ልደቱ አያሌው ምን ያህል ቅጣት ሊጠብቃቸው ይችላል?

ፓለቲከኛው ልደቱ አያሌው ምን ያህል ቅጣት ሊጠብቃቸው ይችላል?

ያልተፈቀደ የጦር መሳሪያ በመያዝ ወንጀል የተከሰሱት አቶ ልደቱ አያሌው ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ምን ቅጣት ሊጠብቃቸው ይችላል? ተከታዩ ሰንበትበት ያለ የቢቢሲ ዘገባ የሚነግረን ይኖራል።
***

መንግሥት የዜጎችን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ እንዲሁም የሕዝብን መብትና ደህንነት ለማስከበር የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ታህሳስ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ጸድቋል።

“ተቆጣጣሪ ተቋም” ተብሎ የሚጠራው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወይም ውክልና የተሰጠው የክልል ፖሊስ ኮሚሽን በሥሩ ብሔራዊ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር የሥራ ክፍል አደራጅቶ አዋጁን ያስፈጽማል።
ለመሆኑ ይህ ሕግ ምን ይላል? ማን፣ ምን፣ እንዴት መታጠቅ ይችላል?

የጦር መሳሪያ ፍቃድ እና ሁኔታ?
ለግለሰብ የሚፈቀደው አንድ አነስተኛ ወይም አንድ ቀላል የጦር መሳሪያ ብቻ ነው። ለድርጅትም ቢሆን የሚፈቀደው የጦር መሳሪያ አይነት አነስተኛ ወይም ቀላል የጦር መሳሪያ ሲሆን፤ ዝርዝሩ እና የጥይት ብዛት በተቆጣጣሪው ተቋም በሚወጣ መመሪያ ይወሰናል።

የጦር መሳሪያ ፍቃድ የተጠየቀበት የጦር መሳሪያ ከዚህ ቀደም በሌላ ሰው ስም ፈቃድ ያልወጣበት እና የጦር መሳሪያው ወንጀል ያልተሰራበት መሆን አለበት።

ፍቃድ የሚሰጥባቸው መስፈርቶች
• በተቆጣጣሪ ተቋሙ የሚወጣውን ዕድሜ የሚያሟላ፣ ቋሚ አድራሻ እና መተዳደሪያ ገቢ ያለው
• ኢትዮጵያዊ የሆነ ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ፍቃድ ያለው
• ከጦር መሳሪያ አያያዝ ጋር ያሉ ሕጎችን ግዴታዎች መወጣት የሚችል
• ለጦር መሳሪያ ፍቃድና እድሳት አስፈላጊውን ክፍያ የሚከፍል
• ከሚኖርበት አካባቢ አስተዳደር መልካም ሥነ ምግባር ያለው ለመሆኑ የትብብር ደብዳቤ ማቅረብ የሚችል፤ የሚሉ መስፈርቶች ይገኙበታል።

የተከለከሉ ተግባራት
በዚህ አዋጅ መሰረት ከተፈቀደለት ሰው ውጪ ማንኛውም ሰው፤ የፀና ፍቃድ ሳይኖረው የጦር መሳሪያ እና መለዋወጫዎች ወይም አብረው ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ መሳሪያዎችን፣ ወደ ሀገር ማስገባት እና ማስወጣት፣ መያዝ፣ ማከማቸት፣ መገልገል፣ መደለል፣ መሸጥ፣ መግዛት፣ ማስተላለፍ፣ ማዘዋወር . . . ከተከለከሉ ተግባራት መካከል ይገኙበታል።

የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት የማይቻልባቸው ሥፍራዎች
• ሰላማዊ ሰልፍ ወይም አድማ በሚደረግባቸው ሥፍራዎች
• በምርጫ ሥፍራዎች
• ሆቴል፣ ሲኒማ ቤቶች፣ ሙዚየሞች እና ተመሳሳይ በሆኑ የሕዝብ መዝናኛ ሥፍራዎች
• በትምህርት እና ሃይማኖት ተቋማት ግቢ ውስጥ
• ሆስፒታል፣ መሥሪያ ቤቶች . . . የህዝብ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ሥፍራዎች ተጠቃሽ ናቸው።
መሳሪያ ታጥቀው ከላይ ወደ ተጠቀሱት ሥፍራዎች መግባት ካሰቡ በቅድሚያ የጦር መሳሪያውን ለተቋማቱ የጥበቃ ሰራተኞች ማስረከብ ይኖርብዎታል።

የጦር መሳሪያ ፍቃድ የማይሰጣቸው ተቋማት
• የፖለቲካ ፓርቲ፣
• የሃይማኖትና የእምነት ተቋም፣
• የበጎ አድራጎት ድርጅትና ማህበር፣ እና
• የትምህርት ተቋም ናቸው

ከላይ የተጠቀሱት ተቋማት ለጥበቃ ከሚያስፈልጋቸው የጦር መሳሪያ ውጪ ማንኛውም ዓይነት የጦር መሳሪያ ፍቃድ አይሰጣቸውም።

በልማድ ለታጠቁ የህብረተሰብ ክፍሎች የጦር መሳሪያ ፍቃድ ስለመስጠት
በተለምዶ የጦር መሳሪያ የሚያዝባቸው አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑ እና የጦር መሳሪያ የያዙ ሰዎች፤ የያዙት የጦር መሳሪያ በዚህ አዋጅ ያልተከለከለ አይነት እስከሆነ ድረስ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተቆጣጣሪው ተቋም በአካባቢያቸው ተገኝቶ በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በአካል ቀርበው ፈቃድ ሲጠይቁ ለአንድ ሰው አንድ የጦር መሳሪያ ፈቃድ በዚህ አዋጅ መሰረት ይሰጣል።
በተገለፀው ጊዜ ገደብ ውስጥ ፈቃድ ያልወጣበት የጦር መሳሪያ ለተቆጣጣሪው ተቋም ገቢ መደረግ አለበት፣ በቁጥጥር በተገኘም ጊዜ ይወረሳል።

የጦር መሳሪያ ፍቃድ ስለሚታደስበት ሥርዓት
የጦር መሳሪያ ፍቃድ የተሰጠው ማንኛውም ሰው የፍቃዱ አገልግሎት ጊዜ ከማብቃቱ ከ60 ቀናት በፊት የእድሳት ጥያቄውን ለተቆጣጣሪው ተቋም ማቅረብ አለበት። ተቆጣጣሪው ተቋም ጥያቄው እንደቀረበለት በፍጥነት የፍቃድ መስጫ መስፈርቶቹ መሟላታቸውን ሲያረጋግጥ ፍቃዱን ያድሳል።

የጦር መሳሪያ ፍቃድ ስለመሰረዝና መውረስ
• መሳሪያው ወንጀል የተፈፀመበት መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ወይም ባለፍቃዱ ይህን አዋጅ ተላልፎ ሲገኝ
• ባለፍቃዱ ሲሞት፣ ያለበት አድራሻ ሳይታወቅ ሲቀር ወይም በፍርድ ወይም በሕግ ችሎታውን ሲያጣ፣
• የጦር መሳሪያው በተለያዩ ምክንያቶች ከባለቤቱ ቁጥጥር ውጪ መሆኑ ሲታወቅ የሚሉት ይገኙበታል
የጦር መሳሪያ አጠቃቀም ግዴታዎች

• በአዋጁ መሠረት ፍቃድ የተሰጠው ማንኛውም ሰው፣
• የጦር መሳሪያውን ሲይዝ የፍቃድ ወረቀቱን አብሮ የመያዝ፣
• ፍቃድ ካገኘበት የጥይት መጠን በላይ በአንድ ጊዜ አለመያዝ፣
• የሚቻል እስከሆነ ድረስ የጦር መሳሪያው በግልፅ ሊታይ በማይችል ሁኔታ መያዝ፣
• የጦር መሳሪያው ሲበላሽ፣ ሲጠፋ፤ ሲሰረቅ፣ ሲቀማ ወይም በማንኛውም ምክንያት ከቁጥጥሩ ውጪ ሲሆን ለተቆጣጣሪው ተቋም ወዲያውኑ ማሳወቅ፣
• የጦር መሳሪያ በማናቸውም መልኩ ለሌላ አሳልፎ ያለመስጠት፣ ያለማዋስ

የተቆጣጣሪ ተቋም ሥልጣንና ተግባር
በአዋጁ መሠረት ተቆጣጣሪ ተቋሙ ከተሰጡት ሥልጣን እና ተግባራት መካከል፦
• ፍቃድ ይሰጣል
• ለሕዝብ ሰላምና ደህንነት አስጊ ሆኖ የተገኘን ማንኛውንም ፍቃድ ያለውንም ሆነ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ የታጠቀን ሰው ያስፈታል፤ ይወርሳል።

• መንግሥታዊ ወይም መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም አማካኝነት በዚህ አዋጅ መሰረት የጦር መሳሪያዎችን ከውጪ ሀገር ማስገባት፣ ማከማቸት፣ ማዘዋወር፣ መሸጥ . . . ተግባራትን እንዲያከናውኑ ፍቃድ ይሰጣል።

የወንጀል ተጠያቂነት
የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 481 የተጠበቀ ሆኖ፤ ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ የተመለከተውን ክልከላ እና ግዴታ የተላለፈ ከአንድ አመት እስከ ሦስት ዓመታት በሚደርስ ቀላል እስራት እና ከአምስት ሺህ እስከ አስር ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል።

የተፈጸመው ወንጀል ብዛት ባለው የጦር መሳሪያ ሲሆን ቅጣቱ ከአምስት አመት እስከ አስራ አምስት አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከሀምሳ ሺህ እስከ መቶ ሺህ ብር በሚደርስ ገንዘብ ይቀጣል።

በሕጋዊ መንገድ ያገኘውን የጦር መሳሪያ የሸጠ በማስያዣነት የተጠቀመ፣ ያከራየ ወይም በውሰት ለሦስተኛ ወገን ያስተላለፈ ማንኛውም ሰው ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ይቀጣል።(BBC)

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top