Connect with us

ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የለውጡ ስጋት ያሏቸውን ስምንት ነጥቦች አስቀመጡ

ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የለውጡ ስጋት ያሏቸውን ስምንት ነጥቦች አስቀመጡ
Photo: Social Media

ፓለቲካ

ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የለውጡ ስጋት ያሏቸውን ስምንት ነጥቦች አስቀመጡ

የኢትዮጵያ ዜጐች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ከሰሞኑ በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአለማቀፍ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ጋር ባደረጉት የቪዲዮ ውይይት ላይ በኢትዮጵያ ለውጡን እየተፈታተኑ ያሏቸውን ስምንት ስጋቶች ለይተው አስቀምጠዋል፡፡

ሀገሪቱ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአትና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ እንዳትሻገር ማነቆ ከሆኑባት መካከል ዋነኛ የሚሏቸውን ነው ፕ/ሩ የጠቆሙት፡፡ አንደኛው ስጋት የህወኃት አካሄድ ነው ያሉት ፕ/ሩ፤ የህወኃት ችግር በትግራይ ላይ ብቻ የሚቆም ሳይሆን በሀገሪቱ አጠቃላይ ችግር ሊፈጥር የሚችል ስጋት ነው ብለዋል፡፡

ሁለተኛው ስጋት ያለንበትን ሁኔታ በአግባቡ አለመረዳትና ኃላፊነት የማይሰማቸው የሚዲያ አካላት የሚፈጥሩት ጫና መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመፍጠር የምንሞክረው በማህበራዊ ሚዲያ ዘመን ነው ያሉት ፕ/ር ብርሃኑ፤ የማህበራዊ ሚዲያ እንኳን ለኛ ለጀማሪዎቹ ጠንካራ ተቋም ለገነቡትም አውሮፓውያን ፈተና ሆኗል ይላሉ – ዋናው ችግሩን መቋቋም የሚቻልበትን ስልት መንደፉ ላይ መሆኑን በመግለጽ፡፡

ሶስተኛ የለውጡ ስጋት በቀላሉ በስሜት የሚነሳሱ በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች በሀገሪቱ መኖራቸው ነው ይላሉ – የኢዜማ መሪ፡፡ እነዚህን ወጣቶች በቀላሉ ለረብሻ ማሰለፍ እንደሚቻልና በጥቂት ገንዘብ ገዝቶ ለጥፋት ማሰማራት የሚቻል መሆኑ ለለውጡ ስጋት መሆኑን በቅርቡ የተፈጠሩ ችግሮችን ዋቢ በማድረግ አስረድተዋል፡፡

አራተኛው የለውጡ ስጋት በአጠቃላይ በማህበረሰባችን ውስጥ የተፈጠረው የሞራል ዝቅጠት ነው ባይ ናቸው – ፕ/ር ብርሃኑ፡፡ ይህ የማህበረሰብ ዝቅጠት ያለው ከሃይማኖት ተቋማት እስከ ትምህርት ቤቶችና በሁሉም ማህበረሰብ ውስጥ ነው የሚሉት ፕ/ር ብርሃኑ ዋናው የሞራል ዝቅጠቱ መነሻም ገንዘብ በማንኛውም መንገድ የማግኘት ያልተገደበ ፍላጎት ነው ይላሉ፡፡ ይህ ጊዜ በእጅጉ የማህበረሰቡ ሞራል የተሸረሸረበት መሆኑንም በማመልከት ለማህበረሰቡ ሞራል ዝቅጠት ያለፈው 27 አመት ስርአትን በዋነኛነት ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡

አምስተኛው የተሠራው ፌደራሊዝም ለነውረኞች በዘር ላይ ለመደበቅ እድል የሚሰጥ መሆኑ ሀገሪቱ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመሸጋገር የምታደርገው የለውጥ ሂደት ስጋት ነው ሲሉ ፕ/ር ብርሃኑ ያስቀምጣሉ፡፡ አሁን የሚነሱ የክልልነት ጥያቄና ጥፋተኞች ብሔር ውስጥ ለመደበቅ የሚያደርጉትን ጥረትም በአስረጅነትም ይጠቅሳሉ፡፡

በስድስተኛነት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ አለመሆንና በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ሊገዳደሩ የሚችል ቁመና አለመያዛቸው መሆኑን የሚገልፁት የፓርቲው መሪ፤ ምክንያታዊ ሆነው ሰፊ ድጋፍ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ገና በሚፈለገው መጠን አለመፈጠራቸውንም እንደ ችግር ያነሳሉ፡፡

በሰባተኛነት የሚያነሱት፤ የጎረቤት ሀገሮች ያሉበት ሁኔታ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ስርአት በመፍጠር ሂደት ላይ የሚኖረውን ጫና ነው፡፡ ሀገሪቱ ያለችበት ቀጠና ዲሞክራሲያዊ ስርአት በቅጡ ያልተጀመረበትና የግጭት ቀጠና መሆኑን የጠቀሱት – ፕሮፌሰሩ፤ ይህም የኢትዮጵያን ለውጥ አስቸጋሪ ሊያደርገው እንደሚችል ስጋታቸውን ይገልፃሉ፡፡

በስምንተኛ ደረጃ የሚያስቀምጡት አጠቃላይ አለም ያለችበትን ሁኔታ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ጥያቄ ውስጥ የገባበትና ኢ-ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች እየጠነከሩ የመጡበት መሆኑና ዓለም ያልጠራ ሁኔታ ላይ መገኘቷ፣ በኢትዮጵያም ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ግቡን እንዳይመታ አደናቃፊ ሊሆን ይችላል ብለዋል – ፕ/ር ብርሃኑ በቪዲዮ ኮንፍረንስ በሰጡት ማብራሪያ፡፡

(አለማየሁ አንበሴ ~ አዲስ አድማስ)

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top