Connect with us

ጉዳት ለደረሰባቸው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ማቋቋሚያ ዕቅድ ይፋ ተደረገ

ጉዳት ለደረሰባቸው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ማቋቋሚያና ለቀጣይ ዕርዳታ የሦስት ቢሊዮን ብር ዕቅድ ይፋ ተደረገ
Photo: Ethiopian Reporter

ማህበራዊ

ጉዳት ለደረሰባቸው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ማቋቋሚያ ዕቅድ ይፋ ተደረገ

ከጠቅላይ ቤተክህነትና የአገር ሽማግሌዎች ተውጣጥቶ የተቋቋመው ዓብይ ኮሚቴ በኦሮሚያ ክልል ጉዳት ለደረሰባቸው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ማቋቋሚያና ድንገተኛ ለሆኑ አደጋዎች የሚውል የሦስት ቢሊዮን ብር ገቢ ማሰባሰቢያ ዕቅድ ይፋ አደረገ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በተገኙበትና የእሳቸውን ይሁንታ ያገኘው ዕቅድ ይፋ የተደረገው ነሐሴ 28 ቀን ሲሆን፣ በማግስቱ ከነሐሴ 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥራ መገባቱን፣ የዓብይ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሕግ ባለሙያው አቶ መኮንን ሰሙ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የሦስት ቢሊዮን ብር ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ተግባራዊ የሚደረገው ወይም ለማግኘት የታቀደው፣ ከአብያተ ክርስቲያን፣ ከምዕመናን፣ ከቤተ ክርስቲያኒቷ አገልጋዮች ከዩኒቨርሲቲ ኮሌጆችና ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ወገኖች መሆኑንና በእርግጠኝነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሰቡትን እንደሚያሳኩ ሰብሳቢው ተናግረዋል፡፡

የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም መነሻው በኦሮሚያ ክልል ከሰባት በላይ ዞኖችና ከ25 በላይ ወረዳዎች ላይ እምነታቸውን መሠረት ያደረገ ጥቃት ለደረሰባቸውና ቤታቸውን፣ ንብረታቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ላጡ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ማቋቋሚያ ቢሆንም፣ ሌሎች ያልታሰቡና ድንገተኛ ችግሮች ሲያጋጥሙ መርጃ የሚሆን ዘለቄታነት ያለው መተማመኛ የዕርዳታ ገንዘብ እንዲሆን ማድረግ መሆኑንም አክለዋል፡፡

በክልሉ ላይ የደረሰውን በተለይ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችን በመለየት የደረሰባቸውን ግድያ፣ የአካል መጉደል፣ ንብረት መዝረፍና ማቃጠል፣ ከቤተ ክህነትና ከአገር ሽማግሌዎች የተውጣጣው ቡድን፣ የመገናኛ ብዙኃንና ሌሎችም ወገኖች ሆነው በ25 ወረዳዎች ተዘዋውረው በመጎብኘትና በአካል በመገኘት የማጽናናትና የማረጋጋት ሥራ መሠራቱን የገለጹት አቶ መኮንን፣ በአካባቢው ባለው ሀገረ ስብከት አካውንት ተከፍቶ 42 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ይህ የተሰበሰበ ገንዘብ በማንም እጅ ሳይገባ በቀጥታ ተጎጂዎቹ በሚከፍቱት አካውንት ከአዲስ ዓመት በፊት ገቢ እንደሚደረግላቸው አስታውቀዋል፡፡ እጃቸውን ለዘረጉ በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉ ወገኖችንም አመስግነዋል፡፡

ለተጎጂዎቹ የሚሰጠው ገንዘብ በሥፍራው ተገኝቶ የእያንዳንዱን ተጎጂ ወገን የጉዳት መጠን አጥንቶ የመጣ ቡድን ባቀረበው የጉዳት መጠን ላይ ተመሥርቶ መሆኑንም አቶ መኮንን ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ ላይ በተለይ ሃይማኖትንና ማንነትን መሠረት በማድረግ በደረሰው ግፍ የተመላበት የጭካኔ ድርጊት፣ መላው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችንና ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንን እንዳሳዘነ ጠቁመው፣ መንግሥት በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ ሕግን የማስከበርና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እየወሰደ ያለው ዕርምጃ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን በቀጥታ በድርጊቱ ተሳትፎ የነበራቸው ግለሰቦችና በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ያሉ አመራሮች በመኖራቸው፣ የክልሉ መንግሥትና የፌዴራል መንግሥት በመተባበር በቁጥጥር ሥር እንዲውሉና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ ምንም ሳያጠፉ ታስረው እየተንገላቱ ያሉ ወገኖች በመኖራቸው እነሱም እንዲፈቱ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡(ሪፖርተር)

Click to comment

More in ማህበራዊ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top