Connect with us

ለዩኒቨርስቲ ግጭቶች ከወዲሁ ዘላቂ መፍትሔ እንዲበጅ ተጠየቀ

ለዩኒቨርስቲ ግጭቶች ከወዲሁ ዘላቂ መፍትሔ እንዲበጅ ተጠየቀ
Students and police outside the gates of Ambo University in Ethiopia’s Oromia region. Photograph: Tom Gardner

ህግና ስርዓት

ለዩኒቨርስቲ ግጭቶች ከወዲሁ ዘላቂ መፍትሔ እንዲበጅ ተጠየቀ

ለዩኒቨርስቲ ግጭቶች ከወዲሁ ዘላቂ መፍትሔ እንዲበጅ ተጠየቀ

~ ዘንድሮ በ6 ወራት ብቻ 12 ተማሪዎች በዩኒቨርስቲ ግጭት ተገድለዋል

በዩኒቨርስቲዎች ለሚፈጠሩ ግጭቶች ከወዲሁ ዘላቂ መፍትሔዎች እንዲበጁ ያሳሰበው የመብቶችና ዲሞክራሲ እድገት ማዕከል፤ ባለፈው አመት በዩኒቨርሲቲ ለተከሰቱ ግጭቶች ማህበራዊ ሚዲያው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን በጥናት ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡

በዘንድሮ ዓመት 6 ወራት ብቻ በ28 ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ግጭቶች መከሰታቸውን ያመለከተው የተቋሙ ጥናት፤ በዚህም 12 ተማሪዎች ለሞት፣ 58 ተማሪዎች ደግሞ ለከባድና ቀላል ጉዳት መዳረጋቸውን ጠቁሟል፡፡ በወልዲያ ዩኒቨርስቲ 2፣ በደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ 1፣ በወሎ ዩኒቨርስቲ 3፣ በድሬደዋ ዩኒቨርስቲ 2፣ በጐንደር ዩኒቨርስቲ 1፣ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ 1፣ በቡቤ ሆራ ዩኒቨርስቲ 1 እንዲሁም በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ 1 ተማሪ በድምሩ 12 ተማሪዎች በግጭቶች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ በጥናቱ መሰረት፡፡

በዩኒቨርስቲዎቹ የተፈጠሩት ግጭቶች መነሻቸው የግለሰብ ፀቦች ቢሆኑም፣ ጉዳዩ የብሔር መልክ እንዲይዝ በመደረጉ የከፋ ጉዳት መድረሱንም ጥናቱ ያመለክታል፡፡ እነዚህ ግጭቶች ላይ የየዩኒቨርስቲዎቹ አስተዳደሮችና የሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም መደበኛ መገናኛ ብዙኃን ፈጣንና ጥራት ያለው መረጃ ባለማቅረባቸውም በማህበራዊ ሚዲያ የሚራገቡ ሃሰተኛ መረጃዎች ግጭቶችን የማቀጣጠል ሚና እንደነበራቸው በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡

“የዩኒቨርስቲ ውስጥ ግጭቶች መንስኤ እና ጉዳት (2012” በሚል ርዕስ በ54 ገፆች ይፋ የሆነው ይህ የጥናት ውጤት የግጭቶቹ ዋነኛ አቀጣጣይ ማህበራዊ ሚዲያ ቢሆንም የግጭቶቹ ምንጮች ግን ከትምህርት ስርአቱ ከአስተዳደር ሁኔታዎችና ከአገሪቱ የፖለቲካ እውነታ ጋር የተያያዘ መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎች ተገኝተዋል ብሏል፡፡

በ2012 የትምህርት ዘመን ጥቅምት 30 ቀን 2012 በወልዲያ ዩኒቨርስቲ በተከሰተ ግጭት የሁለት ተማሪዎች ህይወት ማለፉን፣ ይህን ተከትሎም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ 16 ዩኒቨርስቲዎች የብሔር መልክ ያላቸው ግጭቶች መከሰታቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በዚህም የትምህርት መስተጓጐልና የተማሪዎች ደህንነት በከፍተኛ ደረጃ አደጋ ላይ የወደቀበት ሁኔታ መፈጠሩን አስታውሷል፡፡

በዓመቱ የመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ብቻ 28 ዩኒቨርስቲዎች በመጠን የተለያዩ ግጭቶች ማስተናገዳቸው ጤናማ የትምህርት ስርአት አለመኖሩን ያመላክታል ያለው ጥናቱ፤ ለግጭቶቹ የተለያዩ የእርምት እርምጃዎች ቢወሰዱም ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆኑ አልቻሉም ብሏል፡፡

በየዩኒቨርስቲዎቹ የተፈጠሩ ግጭቶችን ተከትሎም፣ በጠቅላላው 15 ተማሪዎችና 2 የአስተዳደር ሠራተኞች በግድያ ተጠርጥረው መታሠራቸውን ወይም መከሰሳቸውን፣ 3 ምክትል የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶች፣ 4 መምህራንና 25 የአስተዳደር ሠራተኞች ከሥራ መታገዳቸውን እንዲሁም ከ239 በላይ ተማሪዎች በጊዜያዊነት ወይም ሙሉ ለሙሉ ከትምህርት መታገዳቸውን ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም 45 የከፍተኛ ተቋማት ግቢዎች የሰዓት አላፊ የጣሉ ሲሆን በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የደህንነት ካሜራዎችም ተገጥመዋል ተብሏል፡፡

እነዚህ እርምጃዎች መወሰዳቸው አበረታች መሆኑንና በቀጣይም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አስተማማኝ የግጭት መከላከያና ግጭቶችን ቶሎ መቆጣጠር የሚያስችል ስርአት መዘርጋት፣ መገናኛ ብዙኃን በቂ መረጃ አግኝተው ትክክለኛውን መረጃ እንዲያቀርቡ ማድረግ እንዲሁም በዋናነት በተማሪዎች ላይ የአመለካከት ለውጥ የሚመጣበትን ስራ መስራት ተገቢ ነው ይላል፤ጥናቱ ባቀረበው ምክረ ሃሳብ፡፡

በቀጣይ አመት ምርጫ ሊኖር ስለሚችልና የበለጠ ሁኔታውን ሊያጋግል ስለሚችልም ከወዲሁ ተማሪዎች ስልጡን መንገድን በመከተል ከግጭት እንዲርቁ መምከር፣ በተማሪዎች መካከል የሰለጠነ የውይይት ባህልን በማዳበር ስለ ብዝሃነት ያለውን አረዳድ ማስተካከል ይገባል ተብሏል፡፡ የዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ሠራተኞችን የብዝሃነት ስብጥር ማስተካከልም እንደ መፍትሄ ሃሳብ ቀርቧል፡፡

(አዲስ አድማስ ~ አለማየሁ አንበሴ)

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top