Connect with us

ታላቁን ሰው ስናከብር

ታላቁን ሰው ስናከብር፤
Photo: Social media

ጥበብና ባህል

ታላቁን ሰው ስናከብር

ታላቁን ሰው ስናከብር፤
ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል፤ የግብርና ሊቁ፣ ጸሐፊ ትዕዛዙና የዘውድ አማካሪው፡፡
****
ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

አንድ ሰው ናቸው፡፡ ግን ብዙ ሰው ያልኾነውን ኾነው ተግባራቸው ይቆጠራል፡፡ የጥቅምት ገብርኤል ዕለት አዲስ አበባ ውስጥ የተወለዱ የሸገር ልጅ ናቸው፡፡ የዛሬ መቶ አስራ አምስት አመት፤

አባታቸው ክቡር ጸሓፌ ትእዛዝ ወልደ መስቀል ታሪኩ ናቸው፡፡ የቡልጋ ሊቅ ወልደ መስቀል የራስ ዳርጌ ባለሟልና ጸሐፊ ነበሩ፡፡ በኋላም በዳግማዊ ምኒልክ ጸሐፊ ትዕዛዝነትን ለመሾም በቅተዋል፡፡

ቄስ ተምረው ሲጨርሱ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ገብተው ፈረንሳይኛ ቋንቋ ተማሩ፡፡ ከቄስ ትምህርት በኋላም ይኼው የፈረንሳይ ትምህርት ተከትሏቸዋል፡፡ በ1916 ወደ ፈረንሳይ ሀገር ሄደው ናሲዮናል ሱፔርዮር ዲ አግሮኖሚ ኮሎኒያል ናዥን ሱር ማርኒ ፓሪስ በተባለው ትምህርት ቤት በመግባት የእርሻ ትምህርት ተማሩ ይለናል የመርስዔ ሀዘን ወልደ ቂርቆስ መረጃ፡፡

ሰውዬው ለኃላፊነት የተመረጡ ናቸው፡፡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰርተዋል፡፡ በአምቦ የዘመናዊ እርሻ ልማት ፋና ወጊ ሆነው በተማሩት አግልግለዋል፡፡ ባላምባራስ የተባሉት በ1926 ዓ.ም. ሲሆን ያኔ ወሎ የጽሕፈት ቤት ሹም ኾነው ተመድበዋል፡፡

በህይወት ዘመናቸው በርካታ ቦታዎች ተሸመው አግልግለዋል፡፡ መሥሪያ ቤቶችን በሥራ አስኪያጅነት መርተዋል፡፡ ዋና ዲሬክተርም ነበሩ፡፡ ምክትል ሚኒስትርና ሚኒስትር በመሆንም ሀገራቸውንም አገልግለዋል፡፡ በመጨረሻም አብዮቱ እስኪፈናዳ ዘውዱን በማማከር አገልግለዋል፡፡

የየካቲት 12 የግራዚያኒ ቁጣ አዚናራ ያስጋዛቸው ሰው ናቸው፡፡ በአዚናራ እስር ቤት ሳሉ እጹብ ድንቅን ጽፈዋል፡፡ ደራሲ ናቸው፡፡ ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል ስማቸው ጎልቶ የሚነሳው በባለ ብዙ ገጹ ዝክረ ነገር ነው፡፡

የቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴን ሽልማት የወሰዱ ደራሲ ናቸው፡፡ “ያባቶች ቅርስ”፣ “ያገር ባህል”፣ “ባለን እንወቅበት”፣ “ቼ በለው”ን የመሳሰሉ ስራዎችን ጽፈዋል፡፡

ጥቅምት 22 ቀን 1943 ዓ.ም. ንጉሠ ነገሥቱ ሃያኛውን የዘውድ በዓላቸውን ሲያከብሩ ማኅተመ ሥላሴ በጻፉት ማስታወሻ ስለገለጹት እጹብ ድንቅ ለንጉሡ ያቀረቡበትን ማስታወሻ መሰናበቻ እናድርገው፡፡
“ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፤
ግርማዊ ሆይ፤

በጠላት ወረራ ዘመን አዚናራ በምትባል ደሴት በእስር በነበርንበት ጊዜ በ1930 ዓ.ም. ላይ ያዘጋጀሁትን ይኽንን ዕጹብ ድንቅ ብዬ የሰየምኩትን ታናሽ መጽሐፍ ለቸርነቱ ወሰን የሌለው አምላክ የተቀደሰ ፍቃዱ ሆኖ ዛሬ የግርማዊነትዎን ፳ኛው ዓመት የዘውድ በዓል በሚከበርበት ቀን እድል አግኝቼ ለማቅረብ በመቻሌ እግዚአብሔርን እያመሰገንኩ ሞገስ ያገኝልኝ ዘንድ ከዙፋንዎ ሥር ቆሜ

በታላቅ ፍርሀት አበረክታለሁ፡፡
ጥቅምት ፳፪ ቀን ፩፱፻፵፫ ዓ.ም.
ባርያዎ

ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል፡፡”

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ጥበብና ባህል

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top