Connect with us

ፕ/ር መረራ ያስነሱት አቧራ

ፕ/ር መረራ ያስነሱት አቧራና፣ ከፍተኛ አምባጓሮ የፈጠረው "የብሔራዊ ውይይት" ውሎ፣
Photo: Social Media

ፓለቲካ

ፕ/ር መረራ ያስነሱት አቧራ

ፕ/ር መረራ ያስነሱት አቧራና፣ ከፍተኛ አምባጓሮ የፈጠረው “የብሔራዊ ውይይት” ውሎ፣
(መሐመድ አሊ መሐመድ)

ነሀሴ 16 ቀን 2012 ዓ.ም በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ECA) አዳራሽ በተዘጋጀው “የብሔራዊ ውይይት” መድረክ ላይ እኛም ታድመን ነበር፡፡ በዚህ መድረክ አጨቃጫቂ ጽሁፍ ያቀረቡትን ፕ/ር መረራ ጉዲናን በሻይ ሠዓት አግኝቻቸው ባቀረቡት ጽሁፍ እጅግ መደንገጤን ገልጨላቸው ነበር፡፡ ምክንያቱም ፕ/ር መረራ፣ በተለይ ለዶክትሬት (3ኛ ዲግሪ) መመረቂያቸው ” Ethiopia: competing ethnic nationalism and the quest for democracy, 1960-2000″ በሚል ርዕስ ባዘጋጁትና በመጽሐፍ መልክም ባሳተሙት የምርምር ሥራቸውና በሌሎችም ጽሁፎቻቸው አማካይ አቋሞችን በማራመድ የሚታወቁ ናቸው፡፡ ፕ/ር መረራ ራሳቸው በዚህ መድረክ ባቀረቡት ጽሁፍ፣ “አሁን ለተፈጠሩት አለመግባባቶች መንስኤ የሆኑ ችግሮችን ነቅሶ ከማሳየት ባለፈ ሰፋ ባለ መልኩ ሚዛኑን የጠበቀ ነገር ለማዘጋጀት በቂ ጊዜ አልተሰጠኝም” በሚል የመድረኩን አዘጋጆች ይወቅሳሉ፡፡ እውነትም መድረኩ በሩጫና በችኮላ የተዘጋጀ እንደሆነ ቀድሞም ይታወቅ ነበር፡፡ ለዚህ ሌሎች ማሳያዎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡

“ህገ-መንግሥትና ህገ-መንግሥታዊነት – ለብሔራዊ መግባባት” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት የኢዜማ ሊቀ-መንበር አቶ የሺዋስ አሰፋም፣ በህገ-መንግሥትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡ ከውይይቱ ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ሲቀርቡላቸው “እኔኮ የህግና፣ የህገ-መንግሥት ባለሙያ አይደለሁም” የሚል ምላሽ ነበር የሰጡት፡፡ ይሁንና ከሙያቸው ውጭ ቢሆንም “ማሻሻያ እስከሚደረግበት ድረስ አሁን በሥራ ላይ ያለውን ህገ-መንግሥት ማክበር” እንደሚያስፈልግ በአፅንዖት የተናገሩት፣ የአቶ የሺዋስ አቀራረብ በአንፃራዊነት የተሻለ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ሦስተኛው ጽሁፍ አቅራቢ ሻ/ል አማን ዑስማን “የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት – በዘመናዊት ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ የፖለቲካ ፓርቲ አመጣጥን ታሪካዊ ዳራና የሌሎች ሀገራትን ልምድ ለመዳሰስ ሲባዝኑ ቆይተው የኢትዮጵያን ተሞክሮና ውጤት በቅጡ ሳያሳዩን የተመደበላቸው ሠዓት አለቀ ተባለ፡፡

የመድረክ አመራሩም ቢሆን ያልተቀናጀና ግራ መጋባት የሚታይበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ “የአካሄድ ጥያቄ” በማንሳት ውይይቱ ወደባሰ ጭቅጭቅ እንዳያመራ ለማድረግ ሞክሬያለሁ፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን ደጋግሜ እጄን ባወጣም ከመድረኩ ዕድል ሊሰጠኝ አልቻለም ነበር፡፡ በተለይ ዶ/ር መረራ ባቀረቡት ጽሁፍ ዙሪያ የሚደረገው ውይይት ከመቋጨቱ በፊት “ማሳሰቢያ አለኝ” ብዬ ብወተውትም መድረኩን ሲመሩት የነበሩት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ “አቶ መሐመድ አንተ ምን እንደምትናገር ስለገባኝ ዕድል አልሰጥህም” በማለት ውይይቱን በችኮላ ዘጉት፡፡ በትግል ተሳትፏቸውና በዕድሜያቸውም ጭምር የማከበራቸውን ዶ/ር አረጋዊ በርሄንም በሻይ ሠዓት “ምነው ተሾመ ቶጋን ሆኑብኝ?” በሚል ቀልድ በታጀበ አግራሞት ስጠይቃቸው “በጣም ይቅርታ አቶ መሐመድ፣ ከመድረኩ አስተባባሪዎች ከፍተኛ ጫና ስለነበረብኝ ነው” ነበር ያሉኝ፡፡ ግን ለምን? ውይይቱ ለምን እንዲህ ግልብና ጥድፊያ የበዛበት ሊሆን ቻለ? ከዚህ ማትረፍ የተፈለገውስ ምን ይሆን? የሀገራችን ዕጣ-ፋንታ ሊወስን የሚችልን መሠረታዊ ጉዳይ ለፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል ታስቦ ከሆነ መቼም ትልቅ “እብደት” ነው፡፡

የኢትዮጵያ ተራማጅ ፓርቲ (ተራማጅ) በግንቦት ወር 2012 ዓ.ም “የብሔራዊ ውይይት አስፈላጊነትና የተግባር ፍኖተ-ካርታ” በሚል ርዕስ ስፋትና ጥልቀት ያለው ሰነድ አዘጋጅቶ ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለሲቪል ማህበራት፣ ለሙያ ማህበራት፣ ለእምነት ተቋማት፣ ለሚዲያ ተቋማት፣ ለታዋቂ ሰዎችና ለአክቲቪስቶች አሰራጭቶ ነበር፡፡ ሰነዱን ከማሰራጨት በተጓዳኝ ከተቋማቱ ኃላፊዎች፣ በተለይም ከ20 ከሚበልጡ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር በግንባር በመገናኘት ሰፊ ውይይት ማድረግ ተችሎ ነበር፡፡ ከዚያም ባለፈ በEthiopian Civil Society Forum የተወሰኑ የፓርቲና የሲቪል ማህበራት መሪዎችን፣ እንዲሁም በተራማጅ ፓርቲ ጽ/ቤት የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን ያሳተፉ ውይይቶች ተካሂደው ነበር፡፡ ተራማጅ ባቀረበው ሰነድ ዙሪያ የተደረጉ ውይይቶች የጋራ መግባባት የተፈጠረባቸው፣ አበረታችና ተስፋ ሰጭ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡

ይሁን እንጅ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ሰብሳቢና ም/ሰብሳቢን ጨምሮ ሰነዱን ከተቀበሉ በኋላ በምክክር መድረኮቹ ላይ ያልተገኙ ፓርቲዎች ነበሩ፡፡ በዚህ መሐል ጠቅላይ ሚ/ሩ በጽ/ቤታቸው የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጠርተው ባወያዩበት ወቅት ብሔራዊ ውይይት ለማካሄድ ጽሁፍ አቅራቢዎችና የመድረክ መሪዎች መሰየማቸውን በዜና ሰማን፡፡ እኛ በዚህ እንዲህ ዓይነት መድረኮች ላይ ለምን እንደማንጋበዝ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ም/ሰብሳቢ የሆኑትን አቶ ግርማ በቀለን ጠይቀን ያገኘነው ምላሽ “እናንተ የሚጠሩ ፓርቲዎች ዝርዝር ውስጥ ስላልተካተታችሁ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጠይቁ” የሚል ነበር፡፡ የቦርዱን ጽ/ቤት ስንጠይቅ ደግሞ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት የተላከው ሰነድ ዝርዝር ውስጥ መካተታችንን ከሰነዱ ግልባጭ አሳዩን፡፡ የእኛን ቅሬታ መነሻ በማድረግ የቦርዱ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ በተለይ ከጋራ ም/ቤቱ ም/ሰብሳቢ ጋር ከተደዋወሉ በኋላ፣ እኛን የሚያካትት ዝርዝር የያዘው ሰነድ በጋራ ም/ቤቱ ሰብሳቢ በአቶ ሙሳ አደም እጅ እንደተገኘ ተገልፆ በዚህ የውይይት መድረክ ለመታደም በቃን፡፡ ይሁን እንጅ ቢያንስ በቀረቡት ጽሁፎች ላይ እንኳን ሀሳብና አስተያዬት ለመስጠት ዕድል አላገኘንም ነበር፡፡

በውይይቱ መጨረሻ ላይ ግን፣ አቶ ግርማ አልጨክን ብሎ ማሳሰቢያዬን እንዲያቀርብ ዕድል ሰጥቶኝ ነበር፡፡ የእኔ ማሳሰቢያ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲህ ፊት ለፊት ተገናኝተው መነጋገራቸው መልካም ጅምር እንደሆነ፣ ይሁንና ይኸኛው መድረክ ተቀራርቦ መነጋገርን እንደመለማመጃ እንጅ ብሔራዊ ውይይትን ሊተካ እንደማይችል፣ ፈርጀ-ብዙና ውስብስብ የሆኑ የሀገራችን ችግሮች በፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ሊፈቱ እንደማይችሉ፣ መሬት ላይ ያሉትን ችግሮች መፍታት ካልቻልን “ብሔራዊ ውይይት” ተደርጓል መባሉ ብቻውን ትርጉም እንደሌለው፣ ብሔራዊ ውይይት ሁሉን አቀፍና አሳታፊ መሆን እንዳለበት፣ ለብሔራዊ ውይይት ሰፊ ጊዜ ወስዶ በቂ ቅድመ-ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ ለዚህ ደግሞ ተራማጅ ፓርቲ ቀደም ብሎ ያዘጋጀውን ሰነድ ለሁሉም እንዲደርስ ያደረገ መሆኑን፣ 52 ገፅ ያለው የብሔራዊ ውይይት ሰነድ የተሟላ ፍኖተ-ካርታ የያዘ ስለሆነ ብንመራበት ውጤታማ ብሔራዊ ውይይት ማካሄድ እንደሚቻል ለማሳሰብ ሞክሬያለሁ፡፡

በመጨረሻ ማሳሰቢያዬ ሰሚ ያገኘ ይመስላል፡፡ የጋራ ም/ቤቱ ም/ሰብሳቢ አቶ ግርማ በቀጣይ ሁሉን አቀፍ የውይይት መድረክ እንደሚዘጋጅ ቃል ገብተዋል፡፡ ሰብሳቢው አቶ ሙሳም “እነ መሐመድ አዘጋጅተው ያቀረቡት ሰነድ እጅግ በጣም የሚገርምና ጥልቀት ያለው ነው” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡ አድናቆትና ምስጋናው ትርፍ ነገር ነው፡፡ ዋናው ነገር ከገባንበት ምስቅልቅል ሁኔታ ለመውጣት የሚያስችለንን እውነተኛ ብሔራዊ ውይይት ማካሄድ መቻል ነው፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ከዚህ በፊት በግንባር ላላገኘናቸው የገዥው ፓርቲ – ብልፅግና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም በተራማጅ ፓርቲ የተዘጋጀው የብሔራዊ ውይይት ፍኖተ-ካርታ እንዲደርሳቸው ማድረግ ተችሏል፡፡ ብልፅግና ፓርቲ ለብሔራዊ ውይይቱ ስኬት የአንበሳውን ድርሻ እንደሚያበረክት ተስፋ እናደርጋለን፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top