Connect with us

የሹመኞች መልቀቅ!

የሹመኞች መልቀቅ!
Photo: Ethiopian Reporter

ትንታኔ

የሹመኞች መልቀቅ!

በከፍተኛ የመንግስት መዋቅር ውስጥ የፓርቲ አባል ያልሆኑ ሹመኞች ከኃላፊነታቸው መልቀቅ እየጨመረ መምጣቱን ሪፖርተር አስነብቧል፡፡ በቅርቡ የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር የነበሩት አቶ አበበ አበባየሁ ለቀዋል፡፡ የእሳቸውን መልቀቅ ተከትሎ እምብዛም የአመራር ልምድና ክህሎት የሌላቸው በመሆኑ በተደጋጋሚ ሲተቹ የቆዩት የ26 ዓመቷ ወ/ት ሌሊሴ ነሚ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስኪያጅነት ተነስተው ኮምሽኑን እንዲመሩ ተሹመዋል፡፡

አሁን ደግሞ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽንን ከጥንስሱ ጀምረው በመሥራች ኃላፊነት የመሩትና በሕክምና ሙያ የሠለጠኑት ኤፍሬም ተክሌ (ዶ/ር) መልቀቂያ አስገብተዋል፡፡ በተጨማሪም የስትራቴጂ ጉዳዮች ኢንስቲዩት ኃላፊ የሆኑትና በአንድ ወቅት ጋዜጠኛ የነበሩት አቶ ሃሌሉያ ሉሌ የመልቀቂያ ድብዳቤ ካስገቡት እንደሚገኙበት ተዘግቧል፡፡

ለሰዎቹ ለመልቀቅ ምክንያት የሆናቸው አመቺ የስራ ስነምህዳር አለመኖር ሳይሆን እንደማይቀር ሪፖርተር ጠቆም አድርጓል፡፡

***

ሥልጣን የሚለቁ የፓርቲ አባል ያልሆኑ ተሿሚዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

– የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽነር ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን ይፋ አድርገዋል

– የስትራቴጂ ጉዳዮች ኢኒስቲትዩት ኃላፊም መልቀቂያ ማስገባታቸው ይነገራል

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር የመንግሥት ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ በርካታ የፓርቲ አባል ያልሆኑ ኃላፊዎች ቢሾሙም፣ በየጊዜው ከኃላፈነታቸው በመልቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር የነበሩት አቶ አበበ አበባየሁ፣ ከኃላፊነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው እንደለቀቁ አስታውቀው ነበር፡፡ ይሁንና ከሰሞኑ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽንን ከጥንስሱ ጀምረው በመሥራች ኃላፊነት የመሩትና በሕክምና ሙያ የሠለጠኑት ኤፍሬም ተክሌ (ዶ/ር) ኃላፊነታቸውን ከለቀቁ ጎራ ተቀላቅለዋል፡፡

ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ ኮሚሽኑን ሲመሩ የቆዩት ኤፍሬም (ዶ/ር)፣ በግል ጉዳይ ምክንያት ለመልቀቅ መገደዳቸውን ይፋ ያደረጉት ሐሙስ ሐምሌ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ደብዳቤ ነበር፡፡ ‹‹ውድ የሥራ አጋሮቼና ወዳጆቼ የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነርነቴን በመተው መልቀቂያ የማስገባቴን ዜና የማካፍላችሁ በተደባለቀ ስሜት ነው፡፡ የምለቀውም ሙሉ በሙሉ በግሌ ምክንያት ነው፤›› በማለት ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡

በሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኃላፊነታቸው ወቅትና ከዚያም በፊት በነበረው የመንግሥት አገልግሎት በጠቅላላው ከአሥር ዓመታት ያላነሰ ጊዜ ማሳለፋቸውን ያስታወሱት ኤፍሬም (ዶ/ር)፣ በዚህ ወቅት ቤተሰባቸው ላይ ጫና ማሳደሩን፣ በሥራ ምክንያት ለረዥም ጊዜ ከቤተሰብ ጋር የሚያሳልፉበት ወቅት እምብዛም መሆኑን ጠቃቅሰዋል፡፡ ከእሳቸው በፊት የኃላፊነት ቦታቸውን የለቀቁትም ተመሳሳይ ምክንያቶችን አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር የነበሩት አቶ አበበም ተመሳሳይ ይዘት ያለው ሐሳብ ማካፈላቸው ይታወሳል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅርብ በሆነ ኃላፊነት ቦታ ይሠሩ የነበሩት አቶ አበበ፣ ወደ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንዲመጡ የተደረገው የቀድሞው ባልደረባቸው የነበሩት በላቸው መኩሪያ (ዶ/ር) በተመሳሳይ ከኃላፊነት መልቀቃቸውን ማስታወቀቸው ተከትሎ ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ማስገባታቸው ከሚነገርላቸው መካከል፣ የስትራቴጂ ጉዳዮች ኢንስቲዩት ኃላፊ አቶ ሃሌሉያ ሉሌ እንደሚገኙበት የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ እንደ ምንጮች ማብራሪያ ከሆነ አቶ ሃሌሉያ መልቀቂያ ካስገቡ ሁለት ወራት አስቆጥረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጥያቄያቸው እንደ ሌሎቹ ወዲያውኑ ተቀባይነት እንዳላገኘ ይነገራል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሥራ የማያመቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ እንደመጡ፣ አንዳንዶችም መስቀል አደባባይ አካባቢ የሚገኘው ጽሕፈት ቤታቸው ብዙ ዕድሳት ተካሂዶበት ለሥራ በሚያመች መንገድ ታድሶ በተዘጋጀበት ወቅት ከመስቀል አደባባይ እስከ ማዘጋጃ ቤት ለሚዘረጋው ፕሮጀክት በጽሕፈት ቤትነት የተወሰደበትን አጋጣሚ በማጣቀስ፣ ለመልቀቃቸው አንዱ ምክንያት ያደርጉታል፡፡

እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን በማንሳት ለአቶ ሃሌሉያም ሆነ ለኤፍሬም (ዶ/ር) ጥያቄ ለማቅረብና ምላሾቻቸውን ለማካተት የተረደገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ሁለቱም ኃላፊዎች በስልክም በአጭር ጽሑፍ መልዕክትም ተጠይቀው ምላሽ አልሰጡም፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየተመናመነ የመጡትና የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ያልሆኑ የመንግሥት ሹማምንት የስንብት ጉዳይ ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ኃላፊዎች የፓርቲ አባል ባለመሆናቸው ምክንያት፣ የፓርቲ አባል በሆኑት ዘንድ የሚነሳባቸው ጥያቄ አለ፡፡ ቢሮክራሲውን ለታማኝ የፖለቲካ ሹማምንት ከማስጠበቅ ባሻገር ከጥቅማ ጥቅምና ከክፍያ ጋር በተያያዘ በፓርቲ አባላት ዘንድ ቅሬታና ስሞታ እንደሚቀርብ የሚገልጹ ወገኖች፣ እየለቀቁ ለሚገኙ ሹመኞች መነሳት አንዱ መንስዔ እንደሆነ ያቀርባሉ፡፡ በሌላ በኩል ከፓርቲና ከፖለቲካ ውጪ የተሾሙ ኃላፊዎች የመንግሥትን መዋቅር ለማጎልበትና ቢሮክራሲውን ለማጠናከር ሲባል በተመድና በሌሎችም ተቋማት የሚፈከላቸው ደመወዝና ሌሎችም ጥቅማ ጥቅሞች ለረዥም ጊዜ በቦታቸው የማያቆያቸው እንደሆነ፣ ለአጭር ጊዜ በተመደቡበት ቦታ ሠርተው የሚፈልገለውን ውጤት አስገኝተው እንዲሄዱ ስለሚፈለግ መልቀቃቸው ብዙ እንደማያስገርም የሚያነሱም አልታጡም፡፡

በዚህም ተባለ በዚያ እየለቀቁ ያሉት ኃላፊዎች ለመንግሥት የቢሮክራሲ መዋቅር አመኔታን ለማትረፍና ግልጽነትን ለማስፈን ብዙ አስተዋጽኦ ሊያደርጉበት የሚችሉበት ዕድል እንደነበር፣ መንግሥት የሥራ ኃላፊነቶችን የሚሰጠው ለፖለቲካ ታማኞች ብቻ ሳይሆን በዕውቀት፣ በክህሎትና በትምህርታቸው ብሎም በሚመደቡበት ቦታ ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚችሉ ለሚታመንባቸው በተለይም ደግሞ ወጣቶች ለሆኑት መሆኑ ትልቅ ትርጉም እንደነበረው የሚጠቁሙ አስተያየት ሰጪዎች፣ ይህ አሠራር እየደበዘዘ እንዳይመጣ ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ቢሮክራሲው በፖለቲከኞችና በፓርቲ አባልነታቸው ብቻ በሚሾሙ ኃላፊዎች ከተሞላ ነባሩ አዙሪት ተመልሶ ሊመጣ እንደሚችል ያሳስባሉ፡፡ (ሪፖርተር – ብርሃኑ ፈቃደ)

Click to comment

More in ትንታኔ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top