Connect with us

ከንፈር መምጠጥ ይብቃ

ከንፈር መምጠጥ ይብቃ
The remains of a car set on fire by a mob in Shashamane during the violence after the death of Haacaaluu. Photograph: AFP/Getty Images

ነፃ ሃሳብ

ከንፈር መምጠጥ ይብቃ

ከንፈር መምጠጥ ይብቃ

ይድረስ ለኢትዮጵያ ህዝቦች
እንደዋዛ እያየን
ብዙ ሕይወት ጠፋ፣
ብዙ ሀብት ወደመ፣
ብዙ ሕዝብ ተፈናቀለ።

ይህ ተደጋጋሚ ስለሆነ የማያባራ የሀዘን ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ይህ ነገር ያልታሰበ ክስተት ሳይሆን በእቅድ የሚሰራና የሚመራ መሆኑ ደግሞ ለኢትዮጶያ ህዝቦች ግልፅ እየሆነ መጥቷል፡፡ ከንፈር መምጠጥና ማዘን መፍትሔም ዋስትናም አይሆንም፡፡ ከዚህ በኋላ ከንፈር መምጠጥ ይብቃ! መባል አለበት፡፡

የኛ ታሪክ እንደዚህ አይደለም። እኛ እንኳን ለራሳችን ለአለም የሚተርፍ ማህበራዊ ትስስርና አንድነት ያለን ህዝቦች ነን፡፡ ቤት ለእንግዳ፣ ጉረስ በሞቴ፣ ከእኛ ጋር ኑር ፣ አይዞህ፣ በሚል ማህበረሰብ ውስጥ ነው ተወልደን ያደግነው፡፡ ይህን ተምሮ ያደገ ትውልድ ታዲያ እንዴት እንዲህ አይነት ግፍና ክፋት ሊፈፅም ይችላል? ሌላውስ ቢሆን ከጎን ቆሞ እንዴት እያየ ዝም ሊል ይቻለዋል? ይህ ጥያቄ መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ ከሁሉ በፊት ህይወት ይቀድማልና እስኪ ከሰው ልጅ ህይወት እንጀምር፡፡

የወገን ህይወት እንደ ቅጠል ረገፈ

እኔ እያወራሁ ያለሁት ሌላ አገር ላይ በውጭ ስለሆነ ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገር ግን እዚሁ ሀገራችን እየሆነ ስላለው ጉዳይ ነው እንጂ። የሰው ልጅ በህይወት የመኖር መብት ማንም የሚሰጠው ወይም የሚነፍገው አይደለም፡፡ የሀገራችን ህገመንግስትም የዜጎችን ተዘዋውሮ የመስራትና የመኖር መብት እንዲጠበቅ የደነገገ ነው፡፡ ለነገሩ ያህል ነው እንጂ ድሮም ህገ መንግስት ባልነበረበት ዘመን ኢትዮጵያውያን ሲዘዋወሩና ባሻቸው ቦታ ሲኖሩ ማን ጠይቋቸው ያውቃል? ማንስ ጠይቆ ማንስ ተጠይቆ ነበር? ማንም!
ኧረ ለመሆኑ የሀገራችን ዜጎች በዓለም ዙሪያ ተበትነው የሚኖሩትና የሚሰሩት ሰዎች ስለሆኑ ብቻ በሀገር ይቅርና ባዕድ ሀገር እንኳ መኖር ስለሚቻል አይደለምን? እና ታዲያ ኢትዮጵያዊያኑ ይልቁንም አቃፊ መሆኑ በሚነገርለት የሀገሩ ህዝብ ውስጥ መኖር እንደምን የማይቻል ሆነበት? በማንነቱና በእምነቱ ምክንያት እንደምን ህይወቱን ሊያጣ ፣ ሊፈናቀል፣ ሊዘረፍ፣ ሊባረር ይገባዋል? ይህም ጥያቄ በቅጡ መመለስ አለበት፡፡

የሀገር ሀብት ወደመ
ይህ ደግሞ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ነው፡፡ በድህነት አቅማችን የገነባነውን ንብረት በቅስበት አይን አመድ ሆኖ ስናይ ለመሆኑ ማነው የሚጎዳው? ህዝቡ ራሱ አይደለምን? ብለን መጠየቅ አለብን።ዜጎች ጥረው ግረው ሀብት ፈጥረው መጠቀም እንኳን በሀገር ላይ በባዕድ ሀገርም አልተከለከለም፡፡ ስንት ኢትዮጵያዊያን በውጭ እየሰሩ ከራሳቸው አልፈው ለሀገራቸው እየጠቀሙ አይደሉምን? የሀገራችን ባለሀብቶች ጥረው ግረው ኢንቨስት በማድረጋቸው ብዙ ወጣትና የሕብረተሰብ ክፍል አልቀጠሩምን? አካባቢውንስ አላለሙምን? ኢኮኖሚውን አላሳደጉምን? ምን አጥፍተው ነው ታዲያ ባለሀብቶቻችን ሀብታቸውና ድርጅታቸው የሳት እራትና ዶግአመድ የሚሆንባቸው? የስራ እድል በስፋት እንዲፈጠር የውጭ ኢንቨስትመንት እየጠራን የእኛ ኢንቨስተሮች ለምን የጥቃት ኢላማ ይሆናሉ? እንዲህ እየሆነ ከቀጠለስ የሀገራችንና የወጣቱ እጣፈንታስ ምን ሊሆን ነው? ይህም ጥያቄ መመለስኮ አለበት፡፡

እኔ ለሀገራችን ህዝቦች በተለይም ለተከበረው የኦሮሞ ህዝብ መልዕክትም ጥያቄም አለኝ፡፡ በጥቂት ክፉና ጨካኞች፣ ሴረኞች መቶ ሚሊዮን ህዝብና ሀገር እየተጎዳ ነው፡፡ ለዚህ የሆነውን ሁሉ ዘወር ብሎ ማየቱ ከበቂ በላይ ማስረጃ ነው። በንፁሀን ገደብ የሌለው ጭፍጨፋና ሞት፣ በንብረት ውድመትና መፈናቀል የሚያዝን እንጂ የሚስቅ ወገን አለ ብዬ ላስብ አልችልም፡፡ የሚደሰቱ ቢኖሩ ያደረጉት ብቻ ናቸው፡፡ግን አነሱም እንደወገን እንኳ ባያስቡ ሰው በመሆናቸው ቁጭ ብለው ሲያስቡት ህሌናቸው ምን ብሎ ይሆን? የነሱ አይምሮ ምንም ባይል የሰማይ አምላክ ግን ይፈርዳል።

የእኛ ሀገር ህዝብ የራሱ መንፈሳዊና፣ ባህላዊ ፣ህግና ስርዓት አለው፡፡ ለምሳሌ የኦሮሞ የገዳ ህግ ዓለም የሚያውቀው ነው፡፡ ሁሉም ጎሳዎች በየራሳቸው ግጭትን የሚቆጣጠሩበት የሽምግልና መንገድ አላቸው፡፡ የመንግስት ህግ እንኳን ባልፈየደበት ወቅት ህዝባችን በራሱ ህግ አካባቢውንም ሀገርንም ሰላም ያውላል፡፡ ይህ ነገር የትም አለም ላይ የለም፡፡ ክቡር የሀገሬ ህዝብ ሆይ! ክቡር የኦሮሞ ህዝብ ሆይ! የጠፋውን ሕይወትና የወደመውን ሀብት ብቻ አትይ፡፡ በእርግጥ ይህን እንደዋዛ የምታየው እንደማይሆን አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ከዚህ በላይ የወደመውና የተደረመሰው ያ የአንተ በጣም መከበር ያለበት ነባሩ እምነትህ፣ ባህላዊ ህግህና ክብርህ ነው፡፡

ከዚህ በላይ ምን መደፈር አለ? ክፉ ነገር በቤቴ፣ በሰፈሬ፣ በግዛቴ፣ በሀገሬ ሲደረግ ዝም ማለት እርምነው፣ በፈጣሪ ያስጠይቀኛል የሚለው እምነትህ ዛሬ የት አለ? ይህም በአርግጥ መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ በጣም መመለስ ያለበት፡፡ ይህን በወገኖች ላይ በተደጋጋሚ እየሆነ ያለውን ግፍ በየቀዬህ ባየህበት ጊዜ ቁጣህን አላሳየህም የሚል ቅሬታ አለኝ፡፡ የአካባቢ አስተዳደርና ለህዝብ ሰላም ሰልጥኖ የተሰማራው ፖሊስማ እዚያው ቆም አስጨፍጭፏል። የሀገር ሀብት ሲወድም ዝም ብሏል፡፡ እኔ ለመከላከያ ኃይላችን ትልቅ አክብሮት አለኝ፡፡ ግን በሰሞኑ ጥፋት ለጉዳዩ በነበረው ኃላፊነትና ቀናኢነት ልክ ለወገን በቅርብ እያለ ፈጥኖ ለሻሽመኔው ጥፋት አልደረሰም ባይ ነኝ።መከላከያ ከፈጣሪ በታች ዜጎች የሚየምኑት የሚመኩበት ብርቅዬ ተቋም ነው። ይህ ቀጣይም ችግር እንዳይሆን ትምህርት ሊሆነው የሚገባ ይመስለኛል፡፡ እኔ ግን ከሁሉም በላይ ለወገን ዋስትና የድፍን ኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም የኦሮሞ ክቡር ህዝብ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁንም ቢሆን ከፀጥታ ኃይል ይልቅ የህዝቡ ሙከራ ባይኖር ኖሮ ጥፋቱ ከዚህም የከፋ ይሆን ነበር፡፡ ግን የሚገባውን ሁሉ አላደረገም ማለት አለብኝ፡፡ ቁጣውን ያሳያል ብዬ እጠብቅ ነበርና፡፡ የአማራ ህዝብና ሌላውም ህዝብም ይህንን ይጠብቁ ነበር።ተጠብቆ ግን ያልታየ ጉዳይ ሆነ።

ይኽ የጥፋት ኃይል ወደ አዲስ አበባ ለመግባት በሞከረበት ጊዜ የአዲስ አበባ ህዝብ ሰራዊት አልጠበቀም፡፡ አይ! በቃ እንከባበር ! ተመለሱ! ልክ አይደለም! ብሎ ራሱን አስከብሯል፡፡ እናም ታላቁ የኦሮሞ ህዝብ በሚያሰፈራው ድምፁ እረፍ! ልክ አይደለም! ማለት ይችል ነበር፡፡ ለምን ይኽ አልሆነም? ይህም ለኔ መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ እናም በግልፅ ተነጋግሮ ችግሩን ፈቶ አገር ሰላም ውሎ ማደር እንድችል መሆን አለበት፡፡ የሀገር ሰላም ፣ የአካባቢ ሰላም በምንም ዋጋ አይተመንም፡፡ በዓለም ላይ በጣም አስከፊ ልምዶች አሉ፡፡ያንን መጋበዝ አለብን እንዴ? በፍፁም!

በግጭትና ሽብር ዘመን ሰርቶ መብላት፣ ተኝቶ ማደር..የለም፡፡ ሴራው በአንድ ብሔር ላይም ተወስኖ አልቀረም።ያገሪቱን ታዋቂ ሰዎችንም እያሳጣ ነው። እነዚህ ከፊት ለፊት ያሉ አጥፊዎች ብዙ አስበውበት፣ ጥቅምና ጉዳቱን መዝነውት ላይሆን ይችላል፡፡ከኋላ ሆኖ የሚያሰማራው ኃይል ግን የሚሰራው በእቅድና በስልት ነው፡፡ የሴራው ስብስብም ማን ከማን ጋር፣ ከየትና ከየት ፣ እንዴትም እንደሆነ ለህዝብ ግልፅ መሆን አለበት። በየትኛውም ሀገር መንግስት ተቃዋሚ ኃይል አለው፡፡ በነፃ ውድድር መንግስት ለመሆን በሰላም መንቀሳቀስ ዝግ አይደለም፡፡ ዝግ ቢሆንና አመፅ ቢያስፈልግ እንኳን ግጭቱ በመንግስትና በአማፂ መካከል ነበር የሚሆነው፡፡

እነዚህ ሰዎች ግን ንፁሀን ዜጎችን፣ ነፃ ባለሀብቶችንና አውራ መንገዶችን ኢላማ ማድረግ ምን ማለት እንደሆነ ህዝባችን መረዳት አለበት፡፡ እነዚህ ሰዎች ከራሳቸው ውጭ የህዝብ አጀንዳ እንደሌላቸውና በስሙ እየነገዱበት መሆኑን ህዝቡ ተረድቶ በቃ ማለት አለበት፡፡ ይህ ሴራ በተለይ አንጋፋዎቹን የኦሮሞና የአማራ ወንደማማች ህዝቦችን ወደማያባራ ግጭት ውስጥ በማስገባት ይህን ትልቅ አገር ማፍረስና የለውጡን ተስፋ ማጨለም እንደሆነ በጣም ግልፅ ነው። ይህ ደግሞ ለአማራና ለኦሮሞ ህዘቦች በጠቅላላም ለድፍን ኢትዮጵያ ህዝቦች አይጠቅምም።

እናም ነገም ደግሞ እንደዛሬው ችላ ሊባል አይገባም። እንዲህ አይነት ጥፋት መቼም ቢሆን መፈቀድ የለበትም፡፡ ለፖለቲካ ስልጣን መንቀሳቀስ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በህግና በስርአት መሆን አለበት። ከሁሉም በላይ ግን የህዝቡ የዘመናት አንድነቱና ሀገሩ መከበርና መጠበቅ አለበት፡፡ ሰው በሀገሩ ውስጥ ያለስጋት መኖር አለበት። ዋስትናውም መንግስትና ህዝብ መሆን አለበት፡፡ ከትንሽ ሀገር ትልቅ ሀገር ይበልጣል፡፡ ከጥቂት ህዝብም ብዙ ህዝብ እጅጉን ኃያል ይሆናል፡፡የአገራችን ህዝብ የሚያምርበት አንድነቱም ልዩነቱም ተሰናስኖ ህብር ሲሆን እንጂ መለያየቱና መናቆሩ አይደለም።አለም በአንድነታችን ይደመም እንጅ በግጭታችንና በንትርካችን እንዲስቅ መፍቀድ የለብንም።

መንግስት የጀመረውን የህግን የበላይነት የማስከበር ስራ ሊያጠናክረው ይገባል፡፡ ግን ትኩረቱ ቀድሞ መከላከሉ ላይም መሆን አለበት፡፡ ዜጎች መጠበቅ አለባቸው፡፡ የግል፣ የመንግስትና የህዝብ ሀብት እኩል መጠበቅ አለበት፡፡ ይህን ያላስከበረ የመንግስትና የፀጥታ ኃይል ያለማወላወል መጠየቅ አለበት። ከወንጀል ተጠያቂነት ባለፈ የወደመ የግልና የመንግስትም ይሁን የህዝብ ሀብት ተተምኖ ለባለቤቱ መመለስ አለበት፡፡ አገራችን ለዚሁ የሚሆን የህግ ማዕቀፍም ሊኖራት ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡በዚህ አይነት ጉዳት ለተጎጂ ባለሀብቶች የሀገራችን የኢንሹራንስ ስርዓት አይመለከተኝም የሚል ነው፡፡ ታዲያ ማን ነው የሚመለከተው? መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው። ይህ ነገር ከንፈር ከመምጠጥ ያለፈ ማስተካከያ ስራ ይጠይቃል። ለዛሬው በዚሁ ልጨርስ።

በማከታተል ተያያዥ የሆነ ሀሳቦች አቀርባለሁ።እስከዚያው ቸር ያቆየን!
ከንፈር መምጠጥ ይብቃ!!
መሠረት ጀማነህ
ነሃሴ 01 ቀን 2012 ዓ/ም

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top