Connect with us

ሽልማትስ በህዝብ ልብ ውስጥ መገኘት ነው!!

ሽልማትስ በህዝብ ልብ ውስጥ መገኘት ነው!!
Photo: Facebook

ባህልና ታሪክ

ሽልማትስ በህዝብ ልብ ውስጥ መገኘት ነው!!

ሽልማትስ በህዝብ ልብ ውስጥ መገኘት ነው!!
(ጫሊ በላይነህ)

ኢንጅነር ታከለ ኡማ የአዲስአበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ነው። ህግ ለእሱ ሲባል ተሻሽሎ ወደስልጣን ከመጣ ሁለት አመት ደፍኗል። ታከለን የአዲስአበባ ከተማ ተወላጅ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ “ከተማዋ በተወላጇቿ ትመራ” የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች አሁን ድረስ ይቃወሙታል። አንዳንዶች “ለብሔሩ ሰዎች ለይቶ መሬት ሰጠ፣ ኮንደምኒየም አደለ” እያሉ ሌት ተቀን ያብጠለጥሉታል።

ቢሆንም ግን ታከለ ኡማ በአንድ የተከበረ ስራው ብቻ ደጋግሞ መሸለም አለበት እላለሁ። በተለይ በተማሪዎች ምገባ፣ የዩኒፎርም እና የትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦት ረገድ ያከናወነው ስራ፣ በአካል ጭምር እየተገኘ ለታዳጊ ህፃናት በሰጠው ፍቅርና ተስፋ ብቻ ከሽልማት በላይ የሚያስከብረው ነው። ይህን ስል ታከለ እንከን አልባ ቅዱስ ነበር እያልኩኝ አይደለም። ሌላው ቀርቶ ከአንድ አመት በፊት እነጀዋር መሐመድ ያሳመፁዋቸው ጥቂት ጎረምሶች የኮዬ ፈጪ ኮንደምኒየም ማንአባቱ ይገባበትና ብለው ሲፎክሩ ታከለና የብልፅግና ሰዎች ዝምታን ከመምረጥ ባለፈ የፈየዱት ነገር አልነበረም።

በወቅቱ የወሰን ጉዳይ የሚያይ ኮምቴ ተቋቋመ ተባለና ምን እንደሰራ እንኳን ሳይታወቅ በዝምታ ተዋጠ። እነዚያ ለአመታት ሳይተርፋቸው ቆጥበው ከዛሬ ነገ የቤት ችግሬ ይቀረፍልኛል ያሉ የአዲስአበባ ነዋሪዎች አይዟችሁ የሚላቸው እንኳን መጥፋቱ አሳዛኝ ሆኖ ቆይቷል። ይኸው የ13ኛው ዙር የ20 በ80 ኮንደምኒየም እድለኞች መቼ እንኳን ቤታቸውን እንደሚረከቡ እስካሁን ማወቅ የተሳናቸው በታከለ የአመራር ዘመን ነው።

የከተማዋ መሬት እንደጉድ በጠራራ ፀሀይ መወረሩ በራሱም ቢሮ ጭምር ተደጋግሞ የታመነ ነው። ከዚሁ ችግር ጋር ተያይዞ ጥቂት ወራሪ ግለሰቦች የጦፈ ህገወጥ የመሬት ንግድ ውስጥ ሲዋኙ የታየው በታከለ የአመራር ዘመን ነው።

በህዝብ ገንዘብ የተገነባ ኮንደምኒየም አርቲስት ነኝ፣ አክቲቪስት ነኝ… ባይ ሁሉ ሳይቀር ከቤቱ እየተጠራ የታደለው በታከለ የስልጣን ዘመን ነው።

ኢንጅነር ታከለ ሰው ነውና እንደማንኛችንም እንከን ባያጣው ላይገርም ይችላል። ግን ቢያንስ ከህዝብ ልብ የሚያርቅ ስህተት ላለመፈፀም ቀሪውን ጊዜ እንዲጠነቀቅ ጉድፉን በግልፅ መንገር ይገባል። ለኢንጅነር ታከለ ትልቁ ሽልማቱ በምክርቤቱ የተሰጠው ውዳሴ ሳይሆን በህዝብ ልብ ውስጥ የሚያገኘው የክብር ቦታ መሆኑን ባለመዘንጋት የታዩትን ክፍተቶች በቶሎ ያርመዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ለአሁኑ ሽልማት ግን ክቡር ከንቲባችንን እንኳን ደስ አለህ እላለሁ።

( ማስታወሻ ከአዘጋጁ:- ይኸ መጣጥፍ የፀሐፊውን እንጂ የድሬቲዩብን ኤዲቶሪያል አቋም አያሳይም።)

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top