Connect with us

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ዞኖች የተነሡት ክልል የመሆን ጥያቄዎች

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ዞኖች የተነሡት ክልል የመሆን ጥያቄዎች ወጥነት ባለው መልክ መመለስ ይገባቸዋል!

ፓለቲካ

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ዞኖች የተነሡት ክልል የመሆን ጥያቄዎች

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ዞኖች የተነሡት ክልል የመሆን ጥያቄዎች ወጥነት ባለው መልክ መመለስ ይገባቸዋል!

ከኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔርሰቦችና ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደርና ክልላዊ መንግሥት የማቋቋም መብት እንዳላቸው በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 47(2) ላይ ተደንግጓል፡፡ ይህንን ሕገ መንግሥታዊ መብት ለማስከበር ከአሥር በላይ የሆኑ የደቡብ ብሔራዊ ክልል ዞኖች፣ በየዞናቸው ም/ቤት በማስወሰን ለክልሉ ም/ቤት ጥያቄዎቻቸውን ማቅረባቸውና ውሣኔ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን ከተለያዩ ምንጮች ስንሰማ ቆይተናል፡፡

እስካሁን ጥያቄያቸውን ካቀረቡት ዞኖች መካከል በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ-ውሣኔ ተካሂዶ በክልልነት የመደራጀት መብቱ የተከበረለት የሲዳማ ዞን ብቻ ሲሆን߹ የሌሎች ዞኖችን ጥያቄዎች በተመለከተ፣ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን በቡድን/በክላስተር/ በማሰባሰብ ከአንድ በላይ በሚሆኑ ክልሎች ለማደራጀት በመንግሥት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ እየሆነ ባለበት ሁኔታ፣ በመንግሥት እየተደረገ ያለው በክላስተር የማደራጀት እንቅስቃሴ “ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የለውም” በማለት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች በየዞኑ እየታዩ መሆናቸው፣ ፈጣን ምላሽ አልተሰጠንም ከሚል ተስፋ መቁጥ ተነስቶ ሕዝቡ ወደ ግጭት እንዳይገባ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ይሰጋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከኢሶዴፓ የኋላ ታሪክ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ ደቡብ ኢትዮጵያን በፌዴራል መንግሥቱ አባል ክልልነት የማካለሉ ተግባር በ1984 ዓ/ም በሽግግር መንግሥቱ ሲወሰን፣ የዛሬው ኢሶዴፓ የበላይ አመራር ጭምር የሚያውቀው ጉዳይ ነበር፡፡ በጊዜው “የደቡቡ” የማካለል ተግዳድሮት ተብሎ የተወሰደው፣ “በውስን መልክዓ-ምድራዊ አካባቢ” ከ50 በላይ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖራቸው ነበር፡፡

በወቅቱ በሀገሪቱ የነበረው ሁኔታ ጉዳዩን ለሕዝበ-ውሣኔ ለማቅረብ እንደማያመች ግንዛቤ ስለተወሰደ፣ የሽግግሩ ፓርላማ ኢትዮጵያን በአሥራ አራት (14) ክልሎች ያደራጀውን በአዋጅ 7/1984 ማፅደቁን የምናስታውሰው ነው፡፡ በዚሁ መሠረት በሽግግሩ ፓርላማ የተቋቋመው የአከላለል ኮሚቴ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን በአምስት (5) ክልሎች እንዲደራጁ ያቀረበው ሀሳብ የአዋጁ አካል በመሆን በሽግግሩ ፓርላማ መፅደቁንም እናስታውሳለን፡፡

ይህም ውሣኔ በጊዜው ሕዝቡን በመወከል የተገኙትን የሁሉንም የደቡቡን የፖለቲካ ድርጅቶች ተወካዮች ይሁንታ አግኝቶ እንደ ነበር የምናስታውሰው ሲሆን፣ ከወከልናቸውም የደቡቡ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተቃውሞ አልገጠመንም፡፡ ስለሆነም፣ በኢሶዴፓ እምነት በአሁኑ ወቅት ለተከሰተው የደቡቡ ዞኖች በክልልነት የመደራጀት ጥያቄዎች መንስኤው ኢሕአዴግ በአዋጅ 7/1984 መሠረት የተደራጁትን አምስቱን የደቡብ ክልሎች ያለ ሕዝቡ ፈቃድ ለመጨፍለቅ የወሰደው ሕገወጥ እርምጃ ነው።

ይህንን የኢሕአዴግ ሕገወጥ እርምጃ የሽግግሩ ፓርላማ አባል የነበርን፤ የዛሬው ኢሶዴፓ አባላትና መሪዎች ተቃውመን ባካሄድነው ትግል ምክንያት፣ ከሽግግሩ መንግሥት እስከ መባረር አድርሶናል። ኢሶዴፓም መላውን የደቡብ ሕዝብ በማደራጀት የተወሰደውን ሕገወጥ እርምጃ እስከዛሬ ድረስ ሲያወግዝና ሲያታገል ቆይቷል፡፡ በአሁን ወቅት ይህ የሕዝቡ ትግል ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ በክልሉ ውስጥ ያሉት የአብዛኛዎቹ ዞኖች ሕዝቦች ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅድላቸው መሠረት፣ የየራሳቸውን ክልል ለመመሥረት ጥያቄዎችን ወደ ማቅረብ ተሸጋግረዋል፡፡

ይህ እስከዛሬ የቀጠለው የደቡብ ሕዝቦች ሕገ መንግሥታዊ መብት ጥያቄ እስካሁን ምላሽ ያገኘው በሲዳማ ዞን ብቻ ቢሆንም፣ እርምጃው በኢሶዴፓ ዕይታ መንግሥት ሕገ መንግሥቱን በማክበር ረገድ የወሰደ መልካም ጅማሮ ነው፡፡ ስለሆነም በመሪህ ደረጃ መንግሥት የክልልነት፣ የዞንነትና የልዩ ወረዳነት መብት ጥያቄዎችን በደብብ እና ሌሎችም የሀገሪቱ ክልሎች ጭምር ላቀረቡት ሁሉ፣ ጥያቄዎቹ የጥቂት ጥቅመኛ ቡድኖች ሳይሆኑ የምልዓተ-ሕዝቡ መሆናቸውን እያረጋገጠ፣ የራስ አስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ሊያስከብርላቸው ይገባል፡፡ ይህንን እርምጃ ለመውሰድ መንግሥት ፈቃደኛነቱን በማሳየት፣ ከዚህ ቀደም ኢሕአዴግ የፈፀመው ስህተት እንዳይደገም ጥንቃቄ መድረግ ይኖርበታል።

ይህ በእንደዚህ እንዳለ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ከየዞኖቹ ለተነሱት ጥያቄዎች የተለያዩ አማራጮችን በመፈተሽ መፍትሔ ለመስጠት ጥረት እያደረገ መሆኑን ኢሶዴፓ የሚገነዘበው ቢሆንም፣ በአማራጭነት እየቀረበ ያለው በክላስተር የማደራጀቱ እቅድ ግን የየዞኑን ምልዓተ-ሕዝብ ይሁንታ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ማለትም፣ የየዞኖቹም ሆኑ የየወረዳዎቹ ነዋሪዎች አንዱ ከሌላው ጋር በክላስተር የሚሰባሰቡበት ሁኔታ በዴሞክራሲያዊ አግባብ በሚገለፅ ነፃ ፈቃዳቸው መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ ነፃ ፈቃዳቸውም በሕዝበ-ውሣኔ ወይም በሕዝቡ አቋም ላይ በገለልተኛ ምሁራን በሚደረግ ሳይንሳዊ የዳሰሳ ጥናት ተጣርቶ ሲረጋገጥ ብቻ መሆን ይኖርበታል::

በአሁኑ ሰዓት የምንገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት አስቸኳይ ጊዜያዊ አዋጅ የታወጀበት በመሆኑ፣ መንግሥት ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ሕዝበ-ውሣኔ ለማሰጠት እንደሚቸገር ኢሶዴፓ ይገነዘባል፡፡ በመሆኑም ከዚህ በተጨማሪ፣ በራስ አስተዳደር አካባቢዎች የሚካለሉት ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የአሰፋፈር መስፈርት፣ አብላጫው ነዋሪው በሚናገረው ቋንቋ እንደመሆኑ፣ ይህ ደግሞ ሊረጋገጥ የሚችለው፣ እስካሁን ድረስ በሀገራችን ባለው ባልተመቻቸ ሁኔታ ምክንያት ጊዜውን ጠብቆ ማከናወን ባልተቻለው፣ በሕዝብና ቤት ቆጠራ ነው። እንደዚሁም ሌላው ክልል ከመሆን ጥያቄ ጋር ግኑኝነት ያለው፣ በዞን በመስተዳድሮች መሃል የድንበር ይገባኛል ጥያቄዎች ስለሚኖሩ ቅድሚያ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸው ናቸው። የዚህ እርምጃ አስፈላጊነቱ ዞኖቹ ክልሎች ከሆኑ በኋላም ውዝግቡ እንይቀጥል ነው። ለነዚህ ወሳኝ መረጃዎች የሕዝብና ቤት ቆጠራ እና የድንበር ኮሚሽኑ ጥናት ውጤቶች አስፈላጊ ይሆናሉ።

ኢሶዴፓ ከላይ የተጠቀሱት፣ ለተነሱት ክልልነት ጥያቄዎች የተሟላ ምላሽ ለመስጠት አስፈላጊ የሆኑ፣ ሆኖም በተጨባጩ ሁኔታ ምክንያት ያልተጠናቀቁ ተግባራት እንዳሉ ይገነዘባል። ስለሆም የክልልነት፣ የዞንነትና የልዩ ወረዳነት መብት ጥያቄዎችን ያቀረቡት ሁሉ፣ ሀገራችን ባለችበት በአሁኑ ሁኔታ ያሉብንን ውስንነቶች በመገንዘብ፣ ከፍጥጫ ርቀው በሰላማዊ መንገድ ያቀረቧቸው ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎች፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተነሥቶ፣ ሕዝቡ በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ የራሱን ተወካዮች ከመረጠ በኋላ ምላሽ እንደሚያገኙ በትዕግሥት እንዲጠብቁ ኢሶዴፓ በአጽንዖት ያሳስባል፡፡

መንግሥትም በአሁኑ ሁኔታ ማከናወን ያለበት በገለልተኛ ምሁራን የሚደረግ ሳይንሳዊ የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ፣ የተነሱት ጥያቄዎች ችላ ያለመባላቸውንና ለሚሰጠው ውሳኔ አስፈላጊ መረጃዎችን በማሰባሰብ፣ በሕገ መንግስቱ ድንጋጌ መሰረት መፍትሄ ለመስጠት እየሠራ መሆኑን ለሕዝቡ ማሳየት እንደሚኖርበት እናሳስባለን!!

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራስያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)
ሰኔ 19 ቀን 2012 ዓ/ም
አዲስ አበባ

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top