Connect with us

ስትሮክ ምንድን ነው? መንስዔውና ምልክቶቹስ?

ስትሮክ ምንድን ነው? መንስዔውና ምልክቶቹስ?
Photo: Facebook

ጤና

ስትሮክ ምንድን ነው? መንስዔውና ምልክቶቹስ?

ስትሮክ ምንድን ነው? መንስዔውና ምልክቶቹስ?

ስትሮክ ምንድን ነው?
“የስትሮክ በሽታ የአንጎል ውስጥ የደም መፍሰስ ሲሆን ለሞት የሚዳርግ አደገኛ በሽታ ነው። የአንጎል ሕዋሳት ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ በደም ስር አማካኝነት የማያቋርጥ የኦክስጅን አቅርቦት ያስፈልጋቸዋል፤ ይሄን ሂደት በማስተጓጎል ለሞት የሚያደርሰው በሽታ ስትሮክ ይሰኛል” ያሉት በደብረ ብርሃን ሪፈራል ሆስፒታል ጠቅላላ ሐኪም ዶክተር ከተማው አሰፋ ናቸው።

መጠነ ስርጭቱ ምን ያህል ነው?
በኢትዮጵያ የስትሮክ በሽታ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ መምጣቱን ለቁጥር የሚያታክቱ ጥናቶች ማረጋገጥ ችለዋል። አሁን ላይ በገዳይነቱ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያስረዳሉ። ዶክተር ከተማው እንደሚሉት በሽታው ከ35 ዓመት በላይ በሆናቸው ዜጎች ላይ በሰፊው ይከሰታል። አሁን ላይም በሽታው ከተማ ገጠር፣ ሕጻን አዋቂ፣ሐብታም ደሃ ሳይል በርካቶችን በማጥቃት የዜጎችን ሕይወት የሚቀጥፍ በሽታ መሆኑን ገልጸዋል።

የአለም የጤና ድርጅት ከሰባት አመት በፊት በጥናት አስደግፎ እንደገለጸው፣ በአለም ላይ ቀዳሚ የጤና ችግር ከሆኑት የካንሰርና የልብ በሽታ ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ የሚገኝ ገዳይ በሽታ መሆኑን አመላክቷል። በየአመቱ ከሃያ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በበሽታው የሚጠቁ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ስድስት ሚሊዮን ሰዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ።

ከእነዚህ መካከልም አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑት ችግሩ ካጋጠማቸው ጀምሮ እስከ አንድ አመት ባለው ጊዜ ውስጥ ለሕልፈት ይዳረጋሉ። በታዳጊ አገራት ደግሞ በእጅጉ ስርጭቱ የከፋ ነው። እ.ኤ.አ በ2020 በአለም ላይ ከሚከሰተው የስትሮክ በሽታ 3/4ኛው ወይም 75 በመቶው በታዳጊ አገራት ላይ ይከሰታልም ነው ያለው የአለም የጤና ድርጅት።

የበሽታው መንስኤ ምን ይሆን?
ዶክተር ከተማው እንዳሉት፤ በአንጎል ውስጥ ያሉት ጥቃቅን የደም ቅዳዎች መጥበብ ስትሮክ ሊያስከትል ይችላል። የአንድ የደም ቅዳ ተቀጥላ ሥር መዘጋት በአነስተኛ የአንጎል ክፍል ላይ ጉዳት ያስከትላል። በቦታው ያለው ሕብረ ሕዋስ እንዲሞት ያደርጋል። አንጎል ደም የሚያገኘው በአራት የደም ስሮች አማካኝነት ነው።

እነዚህ የደም ስሮች በስብ ክምችት፣ በኮሊስትሮል ሳቢያ ከጠበቡ በውስጣቸው ያለው አላስፈላጊ ነገር ይበተናል። በዚህም ከደም ጋር በመፍሰስ ወደ አንጎል የሚሄደውን የደም አቅርቦት እስከ መድፈን ይደርሳል። በአንዳንድ አጋጣሚዎችም በልብ ውስጥ የደም መርጋት ሊያጋጥም ይችላል። የረጋው ደም አንጎል ውስጥ ወደሚገኙ ደም ቅዳዎች በማምራት ስትሮክ ሊፈጥር እንደሚችል ተናግረዋል።

የበሽታው ምልክቶች ምንድን ናቸው?
የስትሮክ በሽታ ምንም አይነት ምልክቶች ሳያሳይ ረዥም ጊዜ ሊቆይ እንደሚችል በርካታ ጥናቶች ያሳያሉ። በተለይም አነስተኛ ስትሮክ ከሆነ የበሽታ ምልክት የለውም ይላሉ። ይሁን እንጂ የአንጎል ሕብረ ሕዋስን ሊጎዳ እንደሚችልም ጥናቶች ይጠቁማሉ።

የስትሮክ በሽታ አምስት ዋነኛ ምልክቶች እንዳሉት የሚናገሩት ዶክተር ከተማው፣ በአንድ የሰውነት ጎን የሚያጋጥም ድንገተኛ የፊት፣ የእጅ፣ ወይም የእግር ድንዛዜ (ዝለት) ናቸው። እነዚህን የሰውነት ክፍሎች ማንቀሳቀስ አለመቻል ወይም ስሜት አልባ መሆን፣ ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል የመንዘር ስሜት እንዲሰማ ያደርጋል።
በድንገት በአንድ ወይም በሁለት አይኖች ማየት አለመቻል፤ ለመራመድ መቸገር፣ ራስ ማዞር ወይም ሚዛን መጠበቅ አለመቻል፤ መንስኤ የሌለው የራስ ምታት መፈጠር እና ግራ መጋባት፣ ለመረዳት ወይም ለመናገር መቸገር አንዳንዴም በፊት ጡንቻዎች ላይ የሚፈጠር ዝለት (መንቀጥቀጥ) ሊያስከትል እንደሚችል አስረድተዋል።

ለበሽታው የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
በሽታው በማንኛውም የእድሜ ክልል ዘር፣ ቀለምና ጾታ ሳይለይ የሚያጠቃ ቢሆንም የበለጠ ተጋላጭ የሚሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች አሉ። ለምሳሌ፡- ለረዥም ጊዜ የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች ሳይቆጣጠሩ በሚቆዩበት ጊዜ፣ በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ከመጠን ያለፈ ክብደት፣ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ በደም ውስጥ ከፍ ያለ የቅባት መጠን መኖር፣ ተጓዳኝ የሆነ የልብ ሕመም (የደም ግፊት መጨመር)፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ከመጠን ያለፈ መጠጣት፣ በስኳር ሕመም መያዝ ተጠቃሾች ናቸው ይላሉ ዶክተር ከተማው።

ከላይ የተጠቀሱትን አጋላጭ ምክንያቶች በመቆጣጠር ብቻ ከ80 እስከ 90 በመቶ ስትሮክን መከላከል እንደሚቻል ጥናቶች ያሳያሉ። በተጨማሪም በሕክምና የሚታዘዙ መድሐኒቶችን በተገቢው መውሰድ (ለምሳሌ፡- ለደም ግፊት የሚወሰዱ)፣ አለማቋረጥ፣

የሕክምና ምርመራዎችን አስቀድሞ የማድረግ ልምድ ማዳበር ባለሙያዎች በመፍትሄነት ይመክራሉ።

***ሲጠቃለል
በአጠቃላይ የስትሮክ ምልክቶች በሁለት ተከፍለው ሊታዩ እንደሚችሉ ጥናቶችም ያሳያሉ። ደም ሲፈስ አንጎል ውስጥ ወይም በድንገት በሚረጋው ደም ምክንያት የደም ግፊት ይጨምራል። በዚህ ምክንያት ያለማቋረጥ ማስታወክ ሊከሰት ይችላል። ከማንቀጥቀጥም ባለፈ ሕይወትን ጥያቄ ውስጥ ሊጥል ይችላል። በደም ግፊቱ ምክንያት የሚሆን ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የተቋረጠበት የአንጎል ክፍል በቂ ምግብና ኦክሰጂን ባለማግኘቱ የተነሳ የተለያዩ ምልክቶች ይታያሉ።

ለምሳሌ፡- የንግግርን ክፍል ከሆነ የተቋረጠበት የንግግር መዘበራረቅ፣ ምንም ቃላትን ያለማውጣት ችግር ሊከሰት ይችላል። እንቅስቃሴን የሚቆጣጠረው የአካል ክፍል ከሆነ የተጎዳው ግማሽ ጎን ፊትንም ጨምሮ መስነፍ ሊያጋጥመው ይችላል።
ሰምቶ የመመለስ ችግር ከሆነ የገጠማቸው የሚሰጡት ምላሽ ሊዘበራረቅ ይችላል።

እየነገርኩት ለምንድን ነው የማይረዳኝ በማለት ለብስጭት ይዳረጋሉ። እይታን የሚቆጣጠረው የአንጎል ክፍል በሚጎዳበት ወቅት ደግሞ በግማሽ ማየት ሊከሰት ይችላል። ምልክቶች በሚታዩበት ጊዜ በቶሎ መታከም የሚያስፈልግ ቢሆንም ወደ መጀመሪያው አቋም ላይመለስ ይችላል።

ከስድስት ደቂቃ በላይ ወደ አዕምሮ የሚሄዱ ነገሮች እንደተቋረጡ የሚቆዩበት ሁኔታ ከተፈጠረ ሕይወታቸውን ሊያሳጣ ይችላል።

በስትሮክ ሰዎች ሲጎዱ ችግሩ በራሳቸው ላይ ብቻ የሚቀር ሳይሆን ለአስታማሚዎቻቸውና ለቤተሰብ ጭምር ከፍተኛ ችግር የሚያስከትል ነው። ከዚህም ባሻገር በበሽታው የተያዘ ሰው ህይወትን በአግባቡ ለመምራት ይቸገራል። ስራን ለመስራትም ሆነ ለመንቀሳቀስ ጭምር ከፍተኛ እንቅፋት የሚፈጥር በመሆኑም ከራስ አልፎ ለአገር ጭምር ችግር የሚያስከትል እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ምንጭ አዲስ ዘመን አርብ ጥር 15 ቀን 2012 ዓ ም

Click to comment

More in ጤና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top