Connect with us

“ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ!” አዲሱ የፖለቲካ ፋሽን

"ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ!" አዲሱ የፖለቲካ ፋሽን
Photo: Social Media

ፓለቲካ

“ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ!” አዲሱ የፖለቲካ ፋሽን

• ደግነቱ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” የሚሉም ተፈጥረዋል
• የዘረኝነት ፖለቲካ ከኮሮና በላይ ጥፋት ያደርሳል!

መቼም የጦቢያ ፖለቲከኞች ጉድ ማለቂያ የለውም፤ ሁሌም እንዳስደመሙን እንዳስገረሙን ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ እዚህ ሆኑ አውሮፓና አሜሪካ ለውጥ የላቸውም፤የተማሩ ፕሮፌሰር ሆኑ ቀለም ያልጠለቃቸው የኔ ቢጤ ያው ናቸው:: ዲሞክራሲያዊ አገር ውስጥ ኖሩ አልኖሩ ቅንጣት አይለወጡም፡፡ ህዝብን እርስ በርስ የሚያፋጅ የጥላቻ ትርክት እየቀመሩና እየፈበረኩ የሚቀሰቅሱት እኮ ዕድሜ ልካቸውን በአውሮፓና አሜሪካ የኖሩና የዕድሜያቸውን ግማሽ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያሳለፉ ልሂቃን ናቸው፡፡ (ድንቄም ልሂቃን!)

ሁሌም እቺን አገር ፈጣሪ ጥሎ አይጥላትም:: በክፉ ቀን ይደርስላታል፡፡ ከመዓትና ከመከራ ያድናቸዋል – ይታደጋታል። ጦቢያን ከእነ ህዝቧ!!

ከሰሞኑ የአርቲስት ሃጫሉን ግድያ ተከትሎ፣ የተከሰተውን ተመልከቱ፡፡ የዳንነው እኮ በፈጣሪ ተዓምር ነው። ከእርስ በርስ እልቂት – ፍጅትና መጨራረስ! ለትንሽ ግን ተርፈናል – ድነናል። የታቀደውማ እንደነ ሶሪያና የመን የማያባራ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ እንድንገባ ነበር። በ24 ሰዓት ውስጥ የስንቱን ወገናችን ህይወት አጣን? በስንት ልፋትና ጥረት የተገኘ ሃብትና ንብረት ወደመ?! ስንት ሥራ አጦች ተፈጠሩ?

በሁከትና ግርግሩ የደረሰው ጥፋትና ውድመት ዘግናኝና አሰቃቂ ነው፡፡ ወደ 200 ገደማ ሰዎች እንደዘበት ህይወታቸውን ማጣታቸው በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ግን እንዳልኩት– ከታሰበውና ከታቀደው አንፃር፣ ፈጣሪ እንደ ሁልጊዜው ታድጐናል – አትርፎናል ባይ ነኝ። እንጂማ ያየነው አይነት ብሄርና ሃይማኖት ተኮር ጥቃቶች… እንዲህ በቀላሉ መች የሚበርዱ ሆኑና? በከፋ ሁኔታ ሊስፋፉ… ሊቀጣጠሉ… ይችሉ ነበር፡፡ ግን ከመጣው መአት በፈጣሪ ሃይል ተርፈናል – እኛና ጦቢያ!! ይታያችሁ… ኮሮና ቫይረስ በአራት ወራት ውስጥ ያላደረስብንን ጥፋትና ውድመት ነው (በህይወትም በኢኮኖሚም!) የዘር ፖለቲካ በ24 ሰዓት ውስጥ ያደረስብን!! ባለፉት 2 ዓመታት በነፃነትና ዲሞክራሲ ስም መረን የለቀቁ ፅንፈኛ የዘር ፖለቲከኞችና አክቲቪስት ነን ባዮች፤ በማህበራዊ ሚዲያና በቴሌቪዥን መስኮት ለወጣቱ ትውልድ ምን ሲግቱት እንደከረሙ አስታውሱ! በሰሞኑ ግርግርና ሁከት የተዘራውን ነው ያጨድነው፡፡

የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ሰሞኑን ለተቃውሞ አደባባይ ሲወጡ አስገራሚ መፈክር እያሰሙ ነበር አሉ፤ “ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ!” የሚል፡፡ እኔማ ለምትወድም አገር ምን አስጨነቸውና ነው የተቃውሞ ሰልፍ የወጡት? አልኩኝ፡፡ በውሃ ሙሌቱ የተበሳጨችው ግብጽ፤ “ዜግነት አደለቻቸው እንዴ?” ስልም ጠርጥሬአለሁ፡፡ (አገርማ ልትሰጣቸው አትችልም!) ግን የፈለገ ቢሆን፣ ሰው በጤናው የገዛ አገሩን ትውደም እያለ ይፎክራል እንዴ፤ያውም በባዕድ አገር በስደት ተቀምጦ፡፡ ዝንጀሮ እንኳን “መጀመሪያ መቀመጫዬን” አለች አሉ እኮ ነው የሚባለው::

በነገራችን ላይ “ዳውን ዳውን ዐቢይ!” ሲሉ የሰነበቱ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ናቸው አሉ “ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ!” ወደ ማለት የገቡት:: አገርና መሪ ተምታታባቸው እንዴ? እኔ ግን ዝም ብዬ ስጠረጥር፣ ኢትዮጵያን ትውደም ያሉት በሰሞኑ የጠ/ሚኒስትሩ አነጋገር በሽቀው ሳይሆን አይቀርም፡፡ የቱ መሰላችሁ? “እኛ እያለን ኢትዮጵያን ማፍረስ አይቻልም፤ መጀመሪያ እኛን አፍርሳችሁ ነው ኢትዮጵያን የምታፈርሱት፤ ማንም ቢሆን ከኢትዮጵያ በታች ነው!” ያሉትን፡፡ ይሄ እንዴት ሊያበሽቃቸው ይችላል እንደምትሉ እገምታለሁ፡፡ ከእናት ኢትዮጵያ ጋር ቂም የተያያዙ በርካታ ፖለቲከኞች እኮ አሉ፤ ከራሷ ማህጸን የወጡ! ወደ ሌላ ሳንሄድ ላለፉት 28 ዓመታት ጦቢያን እንዳሻቸው የገዟት የሕወሃት /ኢህአዴግ ባለሥልጣናት እኮ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም አይወዱትም ነበር::

ለዚህም ነበር ኢትዮጵያ ከማለት ይልቅ አገሪቱ ማለት ይቀናቸው የነበረው፡፡ ይታያችሁ — አገሪቷን እየገዙ “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር” የሚለው መፈክር የሚያበሳጫቸው ባለሥልጣናት ሁሉ ነበሩ:: እናላችሁ — ኢትዮጵያ ስትወደስና ስትነግስ በሽታቸው የሚነሳባቸው አያሌ ፖለቲከኞችና ልሂቃን ያሉባት ጉደኛ አገር ናት:: በተለይ ደግሞ የዘር ፖለቲካ የሚያራምዱ ጠባብ ፖለቲከኞች፣ ከኢትዮጵያ የሚወዱላት ሥልጣኗን ብቻ ነው፡፡ ታሪኳ ያንገሸግሻቸዋል፡፡ ድሏ አንገት ያስደፋቸዋል:: የድሮ ነገስታቶቿ ታሪክ ቢፋቅ ደስታቸው ነው፡፡ (ፖለቲከኛነታቸው ያከትምለት ነበር!) የህዝቦቿ አብሮነትና የእርስበርስ ትስስር ይጎረብጣቸዋል፡፡

በነገራችን ላይ የዘር ፖለቲካ ከኮቪድ- 19 ወረርሽኝ በእጥፍ የሚያስከነዳ ጥፋትና ውድመት የሚያደርስ መሆኑን ከሰሞኑ አሰቃቂ ክስተት የተረዳን ይመስለኛል፡፡ (ወይስ አሁንም ገና አልተረዳንም!) ኮሮና በአራት ወራት ያላደረሰብንን ጉዳት እኮ ፖለቲካችን በሁለት ቀናት ውስጥ አድርሶብናል፡፡ የሥልጣን ጥመኛ የዘር ፖለቲከኞች፤ በዘሩት ክፉ ሃሳብ፣ በ24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ ከ200 በላይ ንጹሃን ዜጎቻችን ተነጥቀናል፤ በአሰቃቂ መንገድ፡፡ በሃብትና ንብረት ላይ የደረሰው ውድመት የትየለሌ ነው!! ለበርካታ የአገራችን ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ ሆቴሎች፣ የአበባ እርሻዎች፣ ባንኮች፣ ፋርማሲዎች፣ ክሊኒኮች፣ ፋብሪካዎች፣ ት/ቤቶች፣ የተለያዩ የንግድ ተቋማት እንዲወድሙ ተደርገዋል፡፡ የኮቪድ- 19 የለይቶ ማቆያ ማዕከላት ሁሉ ሳይቀሩ መውደማቸውንም ሰምተናል፡፡ (ይሄ ነው ክፉ የዘር ፖለቲካ ውጤት!)

የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከኮሮና በእጅጉ የከፋ የሚያደርገው ሌላው ጉዳይ ደግሞ ማስክ በማድረግ፣ ርቀትን በመጠበቅና እጅን በሳሙና በመታጠብ አደጋውን መከላከል አለመቻሉ ነው፡፡ ቤትን ዘግቶ መቀመጥም የዘር ፖለቲካ ሰለባ ከመሆን አይታደግም፡፡ (ስንቱ ነው ቤቱ በተቀመጠበት እሳት የተለቀቀበት!!) መቼም የዘር ፖለቲከኞችና የሥልጣን ጥመኞች በአጭር ጊዜ ውስጥ ያላሳዩን የአረመኔነትና የጭካኔ ትዕይንት የለም (አበስ ገበርኩ!)፡፡ በጭፍን የዘር ፖለቲካ ላይ የሥልጣን ጥመኝነት ተጨምሮበት — ይሄን ህዝብና አገር አበሳውን እያበሉት እኮ ነው፡፡ ክፋቱ ደግሞ እኛ ምስኪን ህዝቦች የእነዚህን የሥልጣን ጥመኞች ሴራ ጠንቅቀን አለማወቃችን ነው፡፡ ብናውቅማ ኖሮ ህዝብን እርስ በርስ ለማባላትና አገርን ለማፍረስ ተደብቀው ሳይሆን በአደባባይ፣ በህቡዕ ሳይሆን በግላጭ ሲዘጋጁ፣ መርዘኛ የመጨራረስ ሃሳባቸውን በትውልዱ ላይ ሲዘሩ ዝም ብለን ባልተቀመጥን ነበር፡፡ የጥፋት ሃሳባቸውንም በማህበራዊ ሚዲያ እየተቀባበልን ባላስፋፋንላቸው ነበር፡፡ ክፋቱ ግን አሁን ውድ ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡

ለፅንፈኛ የዘር ፖለቲከኞች ሁሉም ነገር የፈጠራ ድርሰት ነው፡፡ መጪውንና የነገውን ብቻ ሳይሆን የትላንቱንም ፈጥረው ይደርሳሉ:: አስገራሚ የጥላቻና የባህል ታሪክ እየደረሱ አይደለም እንዴ ህዝብን እርስ በእርስ የሚያባሉት – ያውም በማያገባውና ባልኖረበት ታሪክ! ለተረት የቀረበ ታሪክ እየተረኩ እኮ ነው ትውልዱን ለጥላቻና ለበቀል የሚያነሳሱት፡፡ (የሥራቸውን ይስጣቸው!)
በእርግጥ እንደ ዓላማቸው አልተሳካላቸውም እንጂ እስካሁን ኢትዮጵያ የምትባል አገርና ኢትዮጵያውያን የሚባሉ ህዝቦች እርስ በርስ ተላልቀው በታሪክ ብቻ የሚጠቀሱ በሆኑ ነበር:: (ግን ፈጣሪያቸው የት ሄዶ!)

በነገራችን ላይ ፅንፈኛ የዘር ፖለቲከኞችና የሥልጣን ጥመኞች ሌላኛው መለያቸው ዋሾነታቸው ነው – የለየላቸው ቀጣፊዎች ናቸው፡፡ የስልጣን እድሜያቸውን ለማራዘምና ስልጣን ለመቆናጠጥ ሲሉ በማናቸውም ጉዳይ ላይ ይዋሻሉ፤ ይቀዳሉ፡፡ ለምን ቢሉ… ለእነሱ ከእውነት ይልቅ ስልጣናቸው – ይበልጥባቸዋልና፡፡

በ20ኛው ክ/ዘመን የእነሱን ያረጀ ያፈጀ ኋላቀር የዘር ፖለቲካ ተቀብሎ ለእርስ በርስ እልቂት ራሱን የሚያዘጋጅ ህዝብ የትም አይገኝም፡፡ እኛ ብቻ ነን የዋህና ተላሎች!! ይሄንን ስስ ብልታችንን በደንብ አግኝተውታል – የዘር ፖለቲከኞቹ!! ለምን ብለን ሳንጠይቅ በስሜት እየተነዳን በቀደዱልን ቦይ እንደምንነጉድ በደንብ ነው የገባቸው – የአራት ኪሎ ቤተ መንግስት የናፈቃቸው የስልጣን ጥመኞች!! ለዚህ ነው እንዳሻቸው እየጠመዘዙን ዓላማቸውን ለማሳካት ህይወታችንን የሚያስገብሩን፡፡

ለዚህ ነው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሊያደርስብን ከሚችለው ጥፋትና ጉዳት በብዙ እጅ የሚያስከነዳ ጥፋትና ውድመት እያደረሱብን የሚገኘው፡፡

ወዳጆቼ፤ ስልጣን ለተጠማ የዘር ፖለቲከኛ፤ ተማረ አልተማረ፤ አወቀ አላወቀ፤ አነበበ አላነበበ ብዙም ለውጥ የለውም፡፡ ለሱ ዋና ግቡ በባሌም ይሁን በባሌ ስልጣን መቆናጠጥ ነው፡፡ የአንድ አገር ህዝቦች እርስ በርስ ቢጨራረሱ፣ በድህነት አረንቋ ቢዳክሩ፣ በኮሮና ወረርሽኝ ቢፈጁ፣ ዜጎች በስደት ቢሰቃዩ፣ በድርቅና በረሃብ ቢጠቁ፣ ከቀያቸው ቢፈናቀሉ፣.. ለፅንፈኛ የዘር ፖለቲከኞች ጉዳያቸው አይደለም፡፡

ለአነሱ ዋና ጉዳያቸው በማናቸውም መስዋእትነት ቤተ መንግስት ገብተው የስልጣን ኮርቻን መቆናጠጥ ብቻ ነው:: ይሄን ህልምና ትልማቸውን ለማሳካት ደግሞ የማይሆኑትና የማያደርጉት የለም፡፡ ታሪካዊ ጠላታችን ከሚሉት አካል ጋር ግንባርና ትብብር ይፈጥራሉ፡፡ ህዝባችንን የፈጀና ያስፈጀ እያሉ ካወገዙት ወገን ጋር ስምምነት ይፈራረማሉ፡፡ አሸባሪ ብለው ከፈረጁት ጋር ቆመው መግለጫ ይሰጣሉ፡፡ ለምን ያላችሁኝ እንደሆነ — ህሊናቸውን የሸጡ ናቸዋ! (መጀመሪያውኑስ ህሊና አላቸው ወይ?!)
(እቺ አገር ለ27 ዓመታት ጣል ጣል የተደረገችውን ያህል፣ የሚያከብራትና ከፍ ከፍ የሚያደርጋት መሪና መንግስት ማግኘቷም ሌላው የፈጣሪ ተአምር ነው!)

ወዳጆቼ፤ “ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ!” የሚሉ ዘረኛ ፖለቲከኞች የተፈጠሩትን ያህል፣ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!” የሚሉ ፖለቲከኞችም መፈጠራቸው ያጽናናል፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

ምንጭ:- አዲስ አድማስ

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ፓለቲካ

 • የአብን ዕጩ ግድያ የአብን ዕጩ ግድያ

  ነፃ ሃሳብ

  የአብን ዕጩ ግድያ

  By

  የአብን ዕጩ ግድያ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ወንበራ ወረዳ ለክልል ምክር ቤት እጩ የነበረው አባላችን በሪሁን አስፈራው ላይ በመተከል ዞን በለስ ልዩ ቦታው ካርባር ግድያ የተፈፀመበት መሆኑን እያሳወቅን ፓርቲያችን በአባላችን ግድያ የተሰማውን መሪር ሐዘን ይገልጻል። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) በቀጣይ ግንቦት 2013 ዓ.ም በሚደረገው አገራዊ ምርጫ ተሳታፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሁሉም የአገራችን ክፍሎች በርካታ እጩ ተወዳዳሪዎችን ያስመዘገበ መሆኑ ይታወቃል። ይሁን እንጅ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በመንግስት ካድሬዎች በአባላቶቻችን ላይ ተደጋጋሚ ዛቻ፣ እስር እና ድብደባ እየፈተፀመ ይገኛል። በተለይ በኦሮሚያ ክልል እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በስፋት እንዲሁም አልፎ አልፎ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የአባላት ማጉላላት፣ እስር እና ድብደባ እየደረሰ ይገኛል ። በተደጋጋሚ ጊዜ ሰላማዊ ዜጎችን ከመጨፍጨፍ እስከ ጅምላ ማፈናቀል የዘለቀው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቀደም ብሎ የክልሉ ካድሬዎች የተወዳዳሪዎች ምዝገባ እንዳይሳካ ለማድረግ ብዙ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም በምርጫ ቦርድ ትብብር ምዝገባው ሊከናወን ችሏል። ከዚያ በኋላም የምርጫ ተወዳዳሪ እጩዎቻችን ቅስቀሳ ላይ በነበሩበት ወቅት ያለመከሰስ መብታቸውን በጣሰ መልኩ አስሮ በማጉላላት እና በማስፈራራት እጩዎቻችን ላይ አላስፈላጊ ጫና ለማሳረፍ ሞክሯል።  ይህ ሁሉ አልበቃ ያለው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ መንግስት የፀጥታ ሰወች ለክልል ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪያችን የነበረውን አቶ በሪሁን አስፈራው ከቻግኒ ወደ በለስ ጉዞ ላይ እያለ ልዩ ቦታው ካርባር ላይ ግድያ ፈፅሞበታል። አብን ግድያው ፖለቲካዊ መሰረት ያለውና ንቅናቄው በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለመገደብ ሆነ ተብሎ የተደረገ እንደሆነ ያምናል። ለዚህም የወንድማችንን ግድያ ጨምሮ በአሶሳ እና አካባቢው በተደጋጋሚ ጊዜ በእጩዎቻችንና አመራሮቻችን ላይ ሲፈፀሙ የነበሩ ምክንያት አልባ እስሮችና ወከባዎች ከበቂ በላይ አስረጂዎች ናቸው። በመላው ኢትዮጵያ በተለይም የግጭት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ምርጫ ሲቃረብ መሰል ግድያዎች፣ ጭፍጨፋዎች፣ ማፈናቀሎችና ወከባወች እንደሚኖሩ ደጋግመን ለመንግስት ያሳሰብን ቢሆንም ከስሕተቱ መማር ያልፈለገው መንግስት ዛሬም ድረስ ዜጎች በጅምላ እና በተናጥል ሲገደሉ፣ ሲፈናቀሉ እና ኃብት ንብረታቸው ሲወድም በዝምታ እየተመለከተ ይገኛል። ፓርቲያችን አብን ይህ ጉዳይ ቀስ በቀስ አገር የሚያፈርስ አደገኛ ጉዳይ መሆኑን ይገነዘባል። ሰላማዊ እና ፍትኃዊ ምርጫ ይደረጋል የሚለውን የዜጎች ተስፋም ከወዲሁ ያጨለመ ነው የሚል ግምገማ ላይ ደርሰናል። አስቸኳይ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድም አበክሮ የሚታገልበት ይሆናል። ስለሆነም አብን መንግስት በምርጫ እጩ አባላችን ላይ የተፈፀመውን ግድያ በአስቸኳይ እንዲመረምር እና ገዳዮችን ለፍርድ እንዲያቀርብ በአንክሮ እየጠየቀ፤ መሰል ነገሮች አፋጣኝ ምላሽ ተሰጥቶባቸው ለምርጫ እጩዎቻችን ተገቢው የጸጥታ ከለላ በመንግስት በኩል እንዲሰጥ እናስገነዝባለን። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በእንዝላልነት ተጨማሪ ሕይወት ቢጠፋ እና አገራችን ወዳልተፈለገ ምዕራፍ ብትገባ ተጠያቂነቱ ሙሉ ለሙሉ መንግስት የሚወስድ መሆኑን ከወዲሁ አብክረን ማሳሰብ እንወዳለን። ለሰማዕቱ ወንድማችንና ጓዳችን አቶ በሪሁን አስፈራው ቤተሰቦችና ለመላው የንቅናቄያችን አባላትና ደጋፊወች መጽናናትን እንመኛለን። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን)

 • ብዙ የሀገር ዋርካዎች እንዳቀረቀሩ አልፈዋል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እናመሰግናለን ብለው እውቅና ስለሰጧቸው የጥበብ አንጋፋዎች እኛም እርስዎን እናመሰግናለን፤ ብዙ የሀገር ዋርካዎች እንዳቀረቀሩ አልፈዋል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እናመሰግናለን ብለው እውቅና ስለሰጧቸው የጥበብ አንጋፋዎች እኛም እርስዎን እናመሰግናለን፤

  ነፃ ሃሳብ

  ብዙ የሀገር ዋርካዎች እንዳቀረቀሩ አልፈዋል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እናመሰግናለን ብለው እውቅና ስለሰጧቸው የጥበብ አንጋፋዎች እኛም እርስዎን እናመሰግናለን፤

  By

  ብዙ የሀገር ዋርካዎች እንዳቀረቀሩ አልፈዋል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እናመሰግናለን ብለው እውቅና ስለሰጧቸው የጥበብ አንጋፋዎች እኛም እርስዎን...

 • የአፋር ክልል ምላሽ የአፋር ክልል ምላሽ

  ዜና

  የአፋር ክልል ምላሽ

  By

  የአፋር ክልል ምላሽ የአፋር ክልል መንግስት ንጹሀንን እየገደለና እያፈናቀለ ነው ሲል የሱማሌ ክልል ያወጣው መግለጫ ጥፋተኝነትን...

 • የሰባት ቁጥር ምስጢርና የይባቤ አዳነ አዲስ ሥራ፡፡ የሰባት ቁጥር ምስጢርና የይባቤ አዳነ አዲስ ሥራ፡፡

  ነፃ ሃሳብ

  የሰባት ቁጥር ምስጢርና የይባቤ አዳነ አዲስ ሥራ፡፡

  By

  የሰባት ቁጥር ምስጢርና የይባቤ አዳነ አዲስ ሥራ፡፡ ሰባት ቁጥርና ሕይወት፤ (አፈወርቅ ልሣኑ ~ ድሬቲዩብ) ሰባት ቁጥር...

 • ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ (Press Release) ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ (Press Release)

  ነፃ ሃሳብ

  ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ (Press Release)

  By

  ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ (Press Release) “መንግስት የህግ...

To Top