Connect with us

በትግራይ ይካሄዳል በተባለው ክልላዊ ምርጫ የሚሳተፉት አራት ፓርቲዎች ብቻ ናቸው

በትግራይ ይካሄዳል በተባለው ክልላዊ ምርጫ የሚሳተፉት አራት ፓርቲዎች ብቻ ናቸው
Photo: Facebook

ዜና

በትግራይ ይካሄዳል በተባለው ክልላዊ ምርጫ የሚሳተፉት አራት ፓርቲዎች ብቻ ናቸው

የትግራይ ክልል ከቀሪው የአገሪቱ ክፍል በተለየ በመጪው ነሐሴ ወር መጨረሻ ክልላዊ ምርጫውን ለማካሄድ ወስኖ ኮሚሽን ማቋቋሙ ይታወሳል።

ይካሄዳል በተበላው ምርጫ ላይ እንደሚሳተፉ በይፋ ካሳወቁት የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ህወሓት፣ ሳልሳይ ወያኔ፣ ባይቶና ትግራይና የትግራይ ነጻነት ድርጅት ይገኙበታል።

ነገር ግን አረና ትግራይ እና የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እስከ አሁን ድረስ ምንም አይነት ተሳትፎ እያደረጉ አለመሆናቸውን ቢቢሲ ያገኘው መረጃ ያሳያል።

አረና ትግራይ በክልሉ የሚካሄደው ምርጫ ላይ ለመሳተፍም አለመወሰኑን ለቢቢሲ አረጋግጧል። የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው በክልሉ የሚካሄደው ምርጫው ሕጋዊ ነው ብለው እንደማያምኑና እንደማይሳተፉ ተናግረዋል።

በክልሉ የሚካሄደው ምርጫ ላይ ተሳትፎ ለማድረግ የወሰኑትን ፓርቲ አመራሮች ለቢቢሲ በተደጋጋሚ እንደተናገሩት ህወሓት በሚያካሄዳቸው የተለያዩ ውይይቶች “ባለቀ ነገር ነው እየተጋበዝን ያለነው” የሚል ቅሬታእንዳላቸው ይናገራሉ።

እንዲሁም የምርጫ ሕጉንና ደንቡን እንዲሁም ኮሚሽኑን በማቋቋም ወቅት የአካሄድ ችግር ማስተዋላቸውንና ይህንንም ቅሬታቸውን መግለፃቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከቢቢሲ ትግርኛ ጋር ቃለምልልስ ያደረጉት የአሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዶሪ አስገዶም ድርጅታቸው በመጪው ነሐሴ ይካሄዳል ተብሎ በተቀጠረው ክልላዊ ምርጫ እንዳይሳተፍ እየተገለለ እንደሆነ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

እንደ ሊቀመንበሩ ከሆነ የምርጫ ሕግና የምርጫ ኮሚሽን ለማቋቋም በተደረገው ውይይት ላይ እንዳይሳተፉ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

“ህወሓት ከሚፈልጋቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ምርጫውን ለማካሄድ ነው የሚፈልገው” ሲሉም ይናገራሉ።

የአሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ለኢሮብ ሕዝብ ለመታገል የተቋቋመ ሲሆን ክልላዊ ምርጫው መካሄድ አለበት ብሎ እንደሚያምን ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።

ፓርቲያቸው ምርጫው ላይ ለመሳተፍ ዝግጅት ጀምሮ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ዶሪ የምርጫ ሕግና መመሪያዎችን ማውጣት የነበረበት የምርጫ ኮሚሽኑ እንደነበር ይገልጻሉ።

ኮሚሽኑ በቂ ጊዜ ተሰጥቶት ቀደም ብሎ መቋቀም እንደነበረበት፣ የሚዲያ ቅስቃሳም መደረግ እንደነበረበት በመጥቀስ ይህ ባልሆነበት የሚካሄድ ምርጫ ግን ፍትሃዊነቱና ተአማኒነቱ ላይ ጥያቄ ያጭራል ሲሉ ተናግረዋል።

ድርጅቱ በአንዳንድ የህወሓት አመራሮች የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደሚደረግበት ጠቅሰው በተለይ “ከብልጽግና ጋር ይሰራሉ” እንደሚባሉ ጠቅሰው የሚባለውም ሐሰት በማለት አስተባብለዋል።

ከብልጽግናንም ሆነ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳላቸው የሚናገሩት ሊቀመንበሩ “ማዕከላችን ሕዝብ ነው፤ ሕዝብን የሚጎዳ ስናይ እንቃወማለን የሚጠቅም ነገር ስናይ እንደግፋለን” ሲሉ የድርጅታቸውን አቋም ገልፀዋል።

በክልሉ ምርጫ የሚደረግ ከሆነ እምጃ እንወስዳለን በተባለበት ጊዜ “ቀድመን የተቃወምነው እኛ ነን፤ እርምጃ የሚወስድ ከሆነ እኛም ከህዝብ ጋር ሆነን እንዋጋለን ብለን መግለጫ አውጥተናል” ሲሉ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በትግራይ ክልል ውስጥ ያለው ፍትህ፣ ዲሞክራሲና የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ ችግር እንዳለ ይናገራሉ።

እነዚህም ችግሮች ምርጫ ወስጥ ከመገባቱ ቀድሞ መፈታት እንዳለባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በስተመጨረሻም በትግራይ ክልል ያለው ሰላምና መረጋጋት እንዲቀጥል የክልሉ መንግሥትን እንደሚደግፉና ሚናቸውን መጫወት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

BBC

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top