Connect with us

በደቡብ አፍሪካ ት/ቤቶች በድጋሚ እንዲዘጉ ተወሰነ

በደቡብ አፍሪካ ት/ቤቶች በድጋሚ እንዲዘጉ ተወሰነ
Photo: Social Media

ዜና

በደቡብ አፍሪካ ት/ቤቶች በድጋሚ እንዲዘጉ ተወሰነ

በደቡብ አፍሪካ በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ መባባስ ምክንያት ተከፍተው የነበሩ ት/ቤቶች ከሰኞ ጀምሮ በድጋሚ እንደሚዘጉ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፖሳ አስታወቁ ፡፡

ፕሬዝዳንቱ ይህን ያስታወቁት የትምህርት ተቋማትን በድጋሚ ስለመዘጋት፣ ኮሮና ቫይረስን ስለመከላከልና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ መልሶ ለማነቃቃት በመውሰድ ላይ ስላለው እርምጃ ለማብራራት ትናንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ ነው፡፡

ፕሬዚዳንቱ ከ11 ቀናት በፊት ከሰጡት የመጨረሻ ጋዜጣዊ መግለጫ ወዲህ 130ሺ ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፤ ዛሬ ላይ 408,052 ዜጎች በደቡብ አፍሪካ በቫይረሱ የተጠቁ ሲሆን ይኸውም ደቡብ አፍሪካ ከዓለም 5ኛ በቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ የተጠቃች ሀገር ያደርጋታል ብለዋል፡፡

በአፍሪካ በቫይረሱ ከተጠቁት መካከል ግማሹ በደቡብ አፍሪካ ይገኛሉ ያሉት ፕሬዝዳንቱ ከበሽታው ጋር በተያያዘ 6 ሺህ ያህል ሞት የተመዘገበ ሲሆን ይኸው የሞት መጠን በዓለም አነስተኛ ከሚባሉት የሚመደብ መሆኑንና በቀጣይ የሞት መጠንን ይበልጥ ለመቀነስ የሚቻለው ሁሉ እንደሚደረግ፤ ከተጠቂዎቹም 58 በመቶ የሚሆኑት ከበሽታው ማገገማቸው መልካም ዜና እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

የቫይረሱን ጥቃት ለመቋቋም የጤና ተቋማትን ማጠናከርና በሽታውን ለመቆጣጠር የሚደረጉ ጥንቃቄዎችን አጠናክሮ መቀጠል ወሳኝ መሆኑን ያስረዱት ፕሬዚዳንቱ ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ፣ የግል ንጽህናን ማሳደግና ማስክና ሌሎች የመከላከያ ቁሳቁሶችን ሳ,ያሰልሱ መጠቀም መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ኢስተርን ኬፕ፣ ክዋዙሉ ናታልና ሃውቴንግ በከፍተኛ ደረጃ በቫይረሱ እየተጠቁ ያሉ ፕሮቪንሶች ናቸው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በዌስተርን ኬፕ ሁኔታዎች መረጋጋት የጀመሩ መሆናቸው ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ መስፋፋትን ተከትሎ የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱና ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ መደረጉን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ በዚህም ት/ቤቶች የተከፈቱት የተማሪዎቹን እድገትና መጻኢ እድል ላለማጨናገፍና በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ እንቅፋት ላለመፍጠር ቢሆንም አሁን ባለው ከፍተኛ የበሽታው መስፋፋት ምክንያት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ ምክክርና ከዓለም የጤና ድርጅት በተገኘ ምክር መሠረት ሁሉም የመንግስት ት/ቤቶች ለሚቀጥሉት አራት ሳምንታት እንዲዘጉ ተወስኗል ብለዋል፡፡

በዚህም መሰረት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችና መምህራን ግን የአንድ ሳምንት እረፍት፣ የ7ኛ ክፍል ተማሪዎች ደግሞ የሁለት ሳምንት እረፍት አድርገው እንዲመለሱ ሌሎች ደግሞ እስከ ኦገስት 23 ድረስ እንዲዘጉ መወሰኑንና የአካዳሚክ ዓመቱም ከ2020 አልፎ እንዲሄድ እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ አዳክሞታል፣ የስራ አጥነትንም አባብሷል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ኢኮኖሚውን መልሶ ለማነቃቃት እንዲቻል እ.ኤ.አ ኤፕሪል 2020 ላይ የተመደበውን 500 ቢልየን ራንድ ከሀገር ውስጥና እንደ African Development Bank እና New Development Bank ከመሳሰሉ አጋሮች ለማሰባሰብ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ቫይረሱ የህይወታችን አካል ሆኖ ለተወሱ ጊዜያት መቀጠሉ የማይቀር በመሆኑ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት የሚሰሩ ስራዎች የቫይረሱን ሙሉ በሙሉ መወገድ ሊጠብቁ አይችሉም ብለዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን የኮሮና ቫይረስ መከላከልን በማስታከክ የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎችን ለመከላከል፣ ለማጣራትና ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ልዩ የምርመራ ማዕከል እንደተቋቋመና በየትኛውም ተቋምና ደረጃ መረጃ ያላቸው ዜጎች ጥቆማ በመስጠት ሁለቱን ብሔራዊ አደጋዎችን ለመቋቋም እንዲሳተፉ ፕሬዝዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ማህበረሱ ከበሽታው ራሱን ለመጠበቅ የሚያደርገው ጥረት እየተሻሻለ እንደመጣና መንግስትም ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበ ስራ ቢሰራም በቀጣይም ይህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ አሳስበዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡(በደቡብ አፍሪካ የኢት. ኤምባሲ)

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top