Connect with us

“ለመልካምነት አይረፍድም”

"ለመልካምነት አይረፍድም"
Photo: Facebook

ባህልና ታሪክ

“ለመልካምነት አይረፍድም”

“ለመልካምነት አይረፍድም”

(ፕሮፌሰር ሂሩት ወ/ማርያም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር)

የሁለት ተቃራኒ ጾታዎች አብሮ የመኖር ስምምነት ቤተሰብ ይመሰርታል፡፡ ልጆች ይወለዳሉ፡፡ የቤተሰብ ቁጥር ሲደመር ህብረተሰብ፤ የህብረተሰብ ስብስብ ደግሞ አገር ይሆናል፡፡ አገር ማለት የትውልድ ቦታችን፣ ማረፊያችን፣ መኖሪያችን፣ መመኪያችን፣ የኔ የምንላቸው ሰዎችና ትዝታዎች ማደሪያ ነው፡፡ አገር ማለት ተስፋችን ነው፡፡ እኛ ለአገራችን ተስፋ ነን፡፡

እንደማንኛውም የዓለም አገራት ታሪክ ኢትዮጵያም የጦርነት ታሪክ አላት፡፡ ከነዚህም መካከል የአድዋ ጦርነትን ማንሳት ይቻላል፡፡ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት በዚያን ዘመን የወረራውን ዜና ሰምተው በቤታቸው የተቀመጡ አንዳችም ኢትዮጵያውያን አልነበሩም፡፡ በንጉሱ የክተት አዋጅ ከታወጀበት ዕለት አንስቶ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘመናዊ የውጊያ ልምምድ ባይኖራቸውም የነበራቸውን ታላቅ ወኔ ይዘው ወደ ጦርነት ቦታ ተመሙ፡፡ ልጆቻቸው፣ ከብቶቻቸው፣ መሬታቸው፣ አየሩ፣ ወንዙና ሸንተረሩ እንዳይደፈርባቸው፡ የባዕድ እጅ እንዳያርፍበት ሊጠብቁ ሊመክቱ ዘመቱ፡፡ የአገራቸው የነፃነት አየር እንዳይጠፋ ተስፋዋ እንዳይጨልም ሞቱላት፡፡ አንድነታቸው ረድቷቸው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ይዞ የመጣውን የጠላት ወራሪ ጦር አሸነፉ፡፡ እነዚህን ጀግኖቻችንን ዛሬም ታሪክ በታላቅ አክብሮት ይዘክራቸዋል፡፡

እናትና አባቶቻችን ብዙ አድዋዎችን አልፈው አንድነቷ የተጠበቀ ሉዓላዊት አገር ኢትዮጵያን አስረክበውናል፡፡ እኛ የዛሬ ዘመን ትውልዶች እንደነሱ ጊዜ ነፍሳችንን ሊቀማን የመጣብን የውጭ ወራሪ ጠላት የለብንም፡፡ ስለዚህ ባለን አቅም ሁሉ በአንድነት ለልማት በመነሳት የአገራችን እውነተኛ ተስፋዎች ልንሆን ይገባናል፡፡

ዙሪያችንን ብንመለከት ብዙዎች በድህነት ውስጥ ይኖራሉ፡፡ እንደ አንድ የአገሩ ተስፋ በእጁ የሆነ ትውልድ እያንዳንዱ የአገራችን ችግር እንዴት ይፈታ፣ ምን ብናደርግ ወገኖቻችንን ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ህይወት እናላቅቃለን፣ ወደ ብልፅግና የሚደረገውን ጉዞ እናግዛለን፣ የጀመርናቸውን ታላላቅ ፕሮጀክቶች እንጨርሳለን ወዘተ ብሎ በጤና፣ በትምህርት፣ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የተሻለ እድገት ላይ ለመድረስ ማሰብና ለተፈፃሚነቱ መረባረብ ይገባናል፡፡

ኢትዮጵያ ደሃ አገር ናት፡፡ “ደሃ ሆኖ መወለድ ያንተ ጥፋት አይደለም፣ ደሃ ሆኖ መሞት ግን የራስህ ጥፋት ነው” እንደሚባለው አገራችን ድህነቷ አብሯት እንዲቆይም ይሁን ከድህነት እንድትላቀቅ የሚያስችለው ሚስጥር ያለው እጃችን ላይ ነው፡፡ እኛ ከተባበርን የማንችለው ነገር የለም የዛሬ ዓመት በሁለት ወራት ብቻ 4 ቢሊየን ችግኞችን ተክለን ተባብረን ከቆምን ያሰብነው እንደሚሳካ ለዓለም አሳይተናል፣ ግብፅ ምንም እንኳን የትኛውም የገንዘብ ተቋም ብድር እንዳይሰጠን ብታስደርግም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ኪስ ብቻ በተዋጣ ገንዘብ መገንባት ችለናል፡፡

አሁንም አገራችን በእድገት ጎዳና የጀመረችውን ጉዞ እንድትቀጥል የኛ የዜጎቿ አዎንታዊ ተሳትፎ ያስፈልጋታል፡፡ ከመሃል ከተማዋ እስከ ጠረፍ ድንበሯ ድረስ የምንኖር ዜጎቿ ኢትዮጵያ የሁላችንም እንደሆነች ልንገነዘብ ይገባል፣ የሁላችንም እንድትሆንም ልንሰራ ግድ ይለናል፡፡ መንግስት ፀጥታና ፍትህን ለማስከበር በሚሰራው ስራ ሁሉ ዜጎች ተሳታፊ ልንሆን፣ ለጥፋት ሳይሆን ለልማት፣ ለፈረሳ ሳይሆን ለመገንባት፣ ለመገፋፋት ሳይሆን ለመተቃቀፍ ልንተባበር ያስፈልጋል፡፡

እናት አባቶቻችን ያወረሱንን ሉዓላዊት ኢትዮጵያ ክብሯን አስጠብቀን፣ ወራሪ ያላዋረደውን የዜጎቿን ክብር አስከብረን (ተከባብረን)፣ ለወለድናቸው ልጆች በሁሉም መስክ የምትመች ሰላማዊት እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ማስረከብ እንድንችል ዛሬ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡ የኃሳብ ልዩነትን ልንቀበል፣ በውይይት፣ መነጋገርና መመካከር ልናምን፣ ዜጎች በየትኛውም የአገራቸው ክፍል ተዘዋውረው እንዲማሩ፣ እንዲሰሩና እንዲያለሙ በዚያም ነፃነት እንዲሰማቸው ልናደርግ ንብረታቸውን በየኔነት ስሜት ልንጠብቅላቸው እና ለህግ መከበርና ፍትህ መስፈን ልንረባረብ ግድ ይለናል፡፡

እንቅስቃሴያችን ሁሉ በኃላፊነት የተሞላ፣ የትናንቱን፣ የአሁኑን እና የነገውን ጉዞና አካሄድ ሁሉ ያገናዘበ ሊሆን ይገባል፡፡ መማር የሰዎችን አስተሳሰብ ለማነፅ የራሱ አስተዋፅኦ የሚያበረክተውን ያህል የህይወት ልምድም የራሱ አበርክቶ አለውና የሰው ልጅ ከዘመናዊ ትምህርትም ከህይወት ልምዱም ያገኛቸውን መልካም ጉዳዮችን ቀምሮ የሕይወት መመሪያው በማድረግ ሊኖርና ሁልጊዜም ራሱን፣ ቤተሰቡን፣ ወገኑንና አገሩን ከሚጎዱ ማናቸውም አይነት እንቅስቃሴዎች ሊታቀብ እና ከሌሎች ጉዳት ሊማር ይገባል፡፡

በቅርብ ዓመታት በትንሽ ስህተት አገራቸውን አፍርሰው በአገራችን ጎዳናዎች ላይ ያሉ ከየመንና ሶርያ ዜጎች መማር ከባድ ሊሆንብን አይገባም፡፡ ይህ ትውልድ ለታልቋ አገር ሰላም፣ ልማት፣ ብልፅግና እና ለዜጎች አንድነት የራሱን ኃላፊነት ይወጣል፡፡ ይህ ከእያንዳንዳችን ይጀምራል፡፡ አሁን እንጀምረው!! ለመልካምነት አይረፍድም!

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top