Connect with us

ፀረ-ጦርነት መግለጫ!

ፀረ-ጦርነት መግለጫ!
Photo: Facebook

ፓለቲካ

ፀረ-ጦርነት መግለጫ!

ፀረ-ጦርነት መግለጫ!
==============

ትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ)

ጦርነት ማለት መግደልና መሞት፣ ማቁሠልና መቁሠል፣ ማቃጠልና መቃጠል ብሎም ማውደምና መውደም ያጠቃለለ እኩይ ሥራ ስለመሆኑ ማንም የሰከነ አእምሮ ያለው ሠው አይስተውም። ይህ እርባና የሌለው አሰቃቂ ድርጊት ጭራሽ እንዲቀር በየፈርጁ ያሉ የዓለም ልሂቃን ተግተው በሚጥሩበት ወቅት፣ ከመሐል ሃገር ሸሽቶ መቐለ የመሸገው የህወሓት አመራር ግን ጦርነት ውስጥ ካልገባሁ በማለት የጦርነት ቅስቀሳውና ዝግጅቱ እያጧጧፈ ይገኛል።

የህወሓት አመራር የጦርነት ቅስቀሳ በይፋ የጀመረው ታሕሳስ 25 ቀን 2012 ዓ/ም መቐለ ላይ «ጽናትና መክት» በሚል መርሕ ባካሄደው አስቸኳይ ድርጅታዊ ጉባኤው ላይ ነው። ከዛን ጊዜ ጀምሮ የትግራይ ህዝብ በሁሉም መዓዝን በጠላት የተከበበና ለጥቃት ዒላማ የሆነ ህዝብ በማስመሰል ‘ተነሥ!’ ‘ታጠቅ!’ ‘መክት!’ እያለ ህዝቡን ከባድ ጭንቅ ውስጥ ክመክተት አልፎ ከ250 ሺህ በላይ ወጣቶችን አሰልጥኖ ለጦርነት አዘጋጅቷል። «ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው» የሚለው የህወሓት መሪዎች ስነ-ሞጎታዊ ያልሆነ፣ ቁንጹል አስተሳሰብ እንዳለ ካልዋጥነው በስተቀር በህዝባችን ላይ የተካሄደ ከበባም ይሁን የተቃጣ ጥቃት ፈጽሞ የለም።

የትግራይ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያ ሃገሩን ሊወሩ የመጡትን ባእዳን ጠላቶች ግንባር ቀደም ተሠልፎ ሊመክት የከፈለው መስዋእትነት እንዳይበቃው፣ ከዛ በኋላም አምባገነኑ ደርግን ለማስወገድ ባካሄደው ጦርነት ሳብያ ቁስሉ ሳያገግም፣ አሁን ደግሞ አመራሩ በሳለው ብቻ፣ በሌለ ጠላት ላይ ጦርነት ለመጀመር ደፋ-ቀና ማለቱ ባእዳን ጠላቶቹ ካደረሡበት ስቃይ የማይተናነስ መከራና ሰቆቃ ለመጨመር ካልሆነ በስተቀር ሌላ መግለጫ ሊሰጠው አይቻልም። የሃገር ውስጥ ችግር ተደማምጦና ተወያይቶ ለመፍታት እየተቻለ፣ በዚህ ክፍለ ዘመን ለዛውም ጠላት እየፈጠረና እየተነኮሰ የጦርነት ነጋሪት መጎሰሙ ወደ ዕብደት የተጠጋ ጭንቀት የወለደው የአእምሮ በሽታ ከመሆን የሚያልፍ አይደለም።

ለመሆኑ የትግራይን ህዝብ እወጋለሁ ብሎ የተነሣ ጠላት አለ ወይ? አለ ካሉስ ማነው? ከየትስ ነው የሚነሳው? ራሱ ባጸደቀው ሕገ-መንግስት አልገዛም ብሎ ከፌዴራል መንግስት መቀመጫ ፈርጥጦ መቐለ ላይ የከተመው የህወሓት አመራር ቡድን መቸም የትግራይ ህዝብ እኔ ነኝ ሊል አይችልም። ሁሉም እንደሚከታተለው፣ እስካሁን ድረስ «በጠላት ተከበሀል» «ተነስ» «መክት» የሚሉት የጦርነት ቅስቀሳዎች ማዳመጥ ካልሆነ በስተቀር በትግራይ ህዝብ ላይ የተነሣ ተፃራሪ ሃይል ይሁን የከበበው አንድም ጠላት እንደሌለ ማረጋገጥ እንወዳለን። የህዝቡ ጠላት አለ ከተባለ እራሱ የህወሓት አመራር ስለመሆኑ ካንዴም ሁለቴም በራሱ ግምገማ ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም። ታድያ የዚህ ጦርነት ቅሥቀሳና ዝግጅት ዓላማው ምንድነው?

የህወሓት አመራር ሐሙስ ሐምሌ 2 ቀን 2012 ዓ/ም ይፋ ባደረገው መግለጫ ላይ እንዳዳመጥነው የትግራይ ህዝብ «ከአሃዳዊው መንግስት ጋር ለማይቀረው ጦርነት ተዘጋጅ!» ብሎ አውጇል። ከዚህ አዋጅ ጋር በተያያዘ ከመሐል ሃገር ጋር የሚያገናኙ መንገዶች ሁሉ በመዝጋት ላይ ይግርኛል፤ በኤርትራ ድንበር በኩልም ተመሣሣይ የጦርነት ግፊት እያደረገ መሆኑን ይስተዋላል። ሲመለምል የከረመውን የልዩ ኃይል ሠራዊትና ሚሊሻ በገፍ ወደ ክልሉ ድንበሮች አስጠግቶና በጦርነት ስነ አአምሮ እንዲዘጋጅ እያደረገው ይገኛል። አሉላ ዮሃንስ በመሰሉ ጭፍን ካድሬዎች አማካኝነት «ጦርነት ለትግራይ ህዝብ የባህል ጨዋታ ነው» እያሉ የጦርነትን አስከፊ ገጽታ እያሞካሹ ህዝቡን ለእርስበርስ አሰቃቂ እልቂት እያዳረጉት ናቸው። ዳሩ የጦርነቱ ወላፈን የሚለበልበው ተራው ህዝብና በግንባር የሚጋፈጡት ልጆቹ እንጂ እነሱና ዘመዶቻቸው እንደሆን የጥይት ድምጽ በማይሰማበት የምቾት ሰፈር ነው የሚኖሩት።

በዚህ የጦርነት ሁኔታ ውስጥ አስገብቶ፣ ህዝቡን እያስጨነቀ ባለበት ወቅት ጎን ለጎን ደግሞ ሕገ-መንግሥቱን እና የምርጫ ቦርድ ደንቦችን የጣሰ ምርጫ እናካሄዳለን ብሎ በመወሰን የተናጠል ክልል ምርጫ ትያትር ለመስራት ሽር ጉድ ሲል ይታያል። መቼም ምርጫና ጦርነት አብሮ ማስኬድ በዓለም ታይቶም ተሰምቶም የማያውቅ ለመጀመሪያ ግዜ በህወሓት አመራር ሊካሄድ ማየቱ ከአግርሞት አልፎ የጭንቀት አልያም የዕብደት ሥራ እንደሆነ ይታየናል።

ጦርነትና ምርጫ የመሰሉ የማይጣጣሙ ድርጊቶችን በአንድ ጊዜ ለማስኬድ ያቀዱበት ምክንያት ምንድን ነው? ብሎ መጠየቅ አግባብነት አለው እንላለን። ከለውጡ ማግሥት ከአዲስ አበባ ሸሽተው መቐለ ከተማ ከመሸጉበት ጊዜ ጀምሮ ሲያካሂዱት የነበረው ቅስቀሳ ለተከታተለው ሁሉ ግልፅ ነው። ለውጡ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና የህግ የበላይነት ምሥረታ እያቀና በመሄዱ፣ ይህ ሂደት እነሱ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ላደረሱት አፈናና ብዝበዛ እንዲሁም በህዝቡ መካከል ለፈጠሩት ግጭትና እልቂት ተጠያቂ የሚደርጋቸው መሆኑ ስለገባቸው ከዚህ ተጠያቂነት ለማምለጥ ከፌደራል ስርዓቱ ተነጥለው እራሱን የቻለ መንግሥት (de-facto state) መሥርተው ያለጠያቂ ለዘልዓለሙ መኖር ስለፈለጉ ብቻ ነው። የጦርነቱ ዳንኪራና የምርጫ ጋጋታው ዓላማ ከዚህ ያለፈ አይደለም።

ለዚህ ደንባራ ዓላማቸው ግብ መምቻ የመረጡት መንገድ ከፌደራል መንግሥቱ ያለውን ሕገ-መንግስታዊ ትሥሥር በጦርነት አሳብበው መቆራረጥና ከተቆራረጡም በኋላ «በምርጫው» አማካኝነት የተገነጠለ የክልሉ መንግሥት ራሱን ችሏል ብለው ለማወጅ እንዲያመቻቸው ነው። ይህ ሰንካላ ዓላማቸው ለአያሌ ዓመታት ሲንገዳገድ የቆየ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ዕርቃኑ ወጥቶ ጣረ-ሞት ላይ በመሆኑ በወንድማማች ህዝብ መካከል ጉዳት ሳይደርስ ቶሎ እንዲቀጭ ገፈት ቀማሹ የትግራይ ህዝብ ይሁን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ተባብሮ እንዲያከሽፈው ይገባል እንላለን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!
ውድቀት ለከፋፋዮች !!
ት.ዴ.ፓ.
ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ/ም

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top