Connect with us

ለተሰናበቱ ከፍተኛ የመንግሥት ሹማምንት የተሰጡ ቤቶች ተነጠቁ

ለተሰናበቱ ከፍተኛ የመንግሥት ሹማምንት የተሰጡ ቤቶች ተነጠቁ
Photo: Social Media

ፓለቲካ

ለተሰናበቱ ከፍተኛ የመንግሥት ሹማምንት የተሰጡ ቤቶች ተነጠቁ

ለተሰናበቱ ከፍተኛ የመንግሥት ሹማምንት የተሰጡ ቤቶች ተነጠቁ

የአቶ ሥዩም መስፍንና የአቶ ስብሃት ነጋ መኖሪያ ቤቶች ተነጥቀዋል

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በጡረታ ለተሰናበቱ ከፍተኛ የመንግሥት ሹማምንት የተሰጡ ልዩ ጥቅማ ጥቅሞችና መኖሪያ ቤቶች እንዲቀሩ በወሰነው መሠረት፣ በጡረታ ለተሰናበቱ የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች የተሰጡ የመንግሥት መኖሪያ ቤቶችን ማስመለስ ተጀመረ።

ከሁለት ዓመት በፊት በተላለፈ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ልዩ ውሳኔ በጡረታ ለተሰናበቱ ከፍተኛ የአገርና የመንግሥት አመራሮች ሲሰጥ የነበረ ልዩ ጥቅማ ጥቅም እንዲቀር፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰኔ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ሰሞኑን ዕርምጃ መወሰዱን ለማወቅ ተችሏል።

በዚህም መሠረት ለቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሥዩም መስፍንና ለቀድሞው የሰላምና ደኅንነት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስብሃት ነጋ የተሰጡ መኖሪያ ቤቶች፣ ሰሞኑን ተነጥቀው ለመንግሥት ገቢ ተደርገዋል።

ከሁለቱ የቀድሞ አመራሮች በተጨማሪም በቅርቡ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትርነታቸው የተነሱት ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር መኖሪያ ቤትም፣ በሰሞኑ ዕርምጃ ከተነጠቁት መኖሪያ ቤቶች መካከል ይገኝበታል።

ለእነዚህ የቀድሞ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች የተሰጡት መኖሪያ ቤቶች የሚገኙት በአዲስ አበባ ከተማ ሲሆን፣ አመራሮቹ ግን በወቅቱ በመኖሪያ ቤቶቹ በራሳቸው እየተገለገሉባቸው አይደሉም።

ሦስቱም የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች ኑሯቸውን በትግራይ ክልል ማድረጋቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ በተሰጧቸው መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የቅርብ ዘመዶቻቸው ይገለገሉ እንደነበር ቤቶቹ በተነጠቁበት ወቅት ታውቋል።

ቤቶቹን በመንጠቅ ለመንግሥት ገቢ እንዲሆኑ የማድረጉን ኃላፊነት እየተወጣ የሚገኘው የገንዘብ ሚኒስቴር ነው፡፡ ይህ ኃላፊነት ለገንዘብ ሚኒስቴር የተሰጠው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰኔ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ባሳለፈው ውሳኔ ነው።

የአገርና የመንግሥት አመራሮች፣ እንዲሁም ዳኞችና የፓርላማ አባላት ሊያገኟቸው የሚገቡ መብቶችና ጥቅሞች በአዋጅ ቁጥር 653/2001 መሠረት መወሰኑ ይታወቃል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰኔ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ፣ በጡረታ ለሚሰናበቱ የአገርና የመንግሥት አመራሮች በአዋጅ ከተፈቀደው ውጪ ተጨማሪ ልዩ ጥቅማ ጥቅሞች እንዲፈቀዱላቸው ወስኖ ነበር።

በዚህ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ልዩ ውሳኔ በጡረታ ለተሰናበቱ የአገርና የመንግሥት አመራሮች ተፈቅደው የነበሩት ተጨማሪ ጥቅማ ጥቅሞች ሦስት ጉዳዮችን የተመለከቱ ነበሩ።

እነዚህም በጡረታ የተሰናበቱ የአገርና የመንግሥት አመራሮች በኃላፊነት በነበሩበት ወቅት በተሰጣቸው ቤት መኖር እንዲቀጥሉ፣ አንድ አውቶሞቢልና አንድ የመስክ ተሽከርካሪ እንዲሰጣቸውና በኃላፊነት በነበሩበት ወቅት ያገኙ የነበረው የሕክምና አገልግሎት እንዲቀጥል የሚፈቅዱ ናቸው።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰኔ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ባሳለፈው ውሳኔ ከላይ የተገለጹት ሦስት ተጨማሪ ጥቅማ ጥቅሞች እንዲሻሩና በአዋጁ መሠረት ብቻ እንዲስተናገዱ የሚል ሲሆን፣ በዚህ ውሳኔ ቤቱ የተሰጣቸው በጡረታ የተሰናበቱ አመራሮች የተሰጣቸውን ቤትና የመስክ ተሽከርካሪ እንዲመልሱ የሚል ነው።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከሁለት ዓመት በፊት ያሳለፈው ውሳኔ በአዋጁ የተፈቀደ ባይሆንም በወቅቱ ከነበረው ሪፎርም አንፃር ተገቢ ቢሆንም፣ በዘላቂነት እነዚህን ጉዳዮች መፈጸምና ይዞ መቀጠል ወጥ አሠራር እንዳይኖር የሚያደርግና አገር ላገለገሉ ከፍተኛ አመራሮች የተለያየ የመብት ጥበቃ በመንግሥት እንዲደረግ የሚፈቀድ ያልተገባ አሠራር ሆኖ በመገኘቱ፣ ወጥ የሆነ የመብት ጥበቃና አሠራር መተግበሩ ተገቢ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለገንዘብ ሚኒስቴር የላከው ደብዳቤ ያስረዳል።(ሪፖርተር ~ ዮሐንስ አንበርብር)

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top