Connect with us

ብልትን በመዝጋት የማይቋጨው የሶማሌ ሴቶች ግርዛት

ብልትን በመዝጋት የማይቋጨው የሶማሌ ሴቶች ግርዛት

ማህበራዊ

ብልትን በመዝጋት የማይቋጨው የሶማሌ ሴቶች ግርዛት

ብልትን በመዝጋት የማይቋጨው የሶማሌ ሴቶች ግርዛት
አምኃየስ ታደሰ amhayest@gmail.com

ሶማሌያዊቷ ሞዴል ዋሪስ ዲሪ ከገዛ ገጠመኟ ተነስታ በፃፈችው “ዴዘርት ፍላወር” የተሰኘ መጽሃፍዋ ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል ለማስተጋባት የሞከረችው ኡኡታ ዛሬም “ጆሮ ዳባ ልበስ” ከመባል አላለፈም፤ በሴቶች ላይ የማይሽር አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጠባሳ ትቶ የሚያልፈው ከግርዛት ጋር በልጃገረድነት የሚፈጸም ብልትን የመዝጋት ኢ-ሠብአዊ ድርጊት! ለ21ኛው ክፍለ ዘመን በበቃንበት በአሁኑ ወቅት ከመዲናችን በአማካይ አንድ ሺ ኪሎ ሜትር ያህል ርቀው ከሚገኙት የሶማሌ መንደሮች ወደ አንዱ ብትዘልቁ ከጥቂት ዓመታት በፊት እንዳገኘኋቸው በምስሉ ላይ የምታይዋቸው ዓይነት እምቦቀቅላዎች በቡድን ሆነው ሲያዘግሙ ሊገጥሟችሁ ይችላል፡፡

እነሱ ታዲያ በትር የመያዛቸው ምክንያት የቡሄን በዓል በ“ሆያ-ሆዬ” ለማክበር አስበው ወይም ራሳቸውን ከጥቃት ሊከላከሉ እንዳይመስላችሁ፡፡ ጐዴ ዞን ውስጥ ቀላፎ ወረዳ አፍዱብ በተባለ የገጠር ቀበሌ የሚኖሩት እኚሁ ጨቅላዎችም ሆኑ መሰሎቻቸው በምርኩዝ መደገፋቸው በግርዛት ስም ከሚፈጸመው ትልተላ ጋር በተያያዘ መሆኑን ስታውቁ ከሚሰማችሁ ድንጋጤ ይበልጥ የሂደቱ ዘግናኝነት እንዲሁም ለድርጊቱ የሚሰጠው ምክንያት ጭምር ቢረብሻችሁ አያስደንቅም፡፡

በአገራችንም ሆነ በጐረቤት ሶማሊያ በሚኖሩት ሶማሌዎች መካከል ፀንቶ እንደቆየው አስተሳሰብ ከሆነ “በሴቷ ጭኖች መካከል የሚገኘው አጓጓል” የሠውነት ክፍል ያልተወገደላት እንስት “ለትዳር የማትበቃ፣ አመንዝራና የወሲብ ጥማቷም ገደብ የሌለው” ነው፡፡ ላልተገረዘች የሶማሌ ሴት ባል ማግኘት የማይታለም ሲሆን የተፈጥሮ ድንግልናዋም ተአማኒነት የለውም፡፡ እናም “ከጋብቻ በፊት የሚፈጸምን ወሲብ ለመቆጣጠር” የሚያስችለው ብልትን መዝጋት እና የግርዛቱ ሂደት በተለምዶ በአንድነት የሚከናወኑበት የልጃገረዶቹ ዕድሜ አስር ዓመት አካባቢ ሲሆን ነው፡፡

ግርዛቱ ከአፋር ውጪ በተቀሩት የአገራችን ክፍሎችም ሆነ እንደ ግብጽና ጅቡቲ በመሳሰሉት አገራት በዘልማድ ከሚፈጸመው የሚለየው ለሴቷ ተራክቦና ሥነ-ተዋልዶ መሠረታዊ ፋይዳ ካለው “ቂንጥር” በተጨማሪ ትንሹ የብልት ከንፈር (ላቢያ ማይኖራ) ሙሉ በሙሉ እንዲወገድ በማድረጉ ብቻ አይደለም፡፡ በትልተላው ውጫዊው የብልት ከንፈር በከፊል ተከርክሞና ዙሪያው እንዲቆስል ከተደረገ በኋላ የልጃገረዶቹ ብልት ግራና ቀኙ በቀላሉ በማይበጠስ ጅማት መሰል ክር ቢያንስ ሶስት ቦታ እንዲያያዝ ይደረጋል፡፡

ስፌቱ በእንቅስቃሴ ምክንያት እንዳይላቀቅም በግርዛቱ ዕለት የጨቅላዎቹ ሁለት እግሮች ከጭን አንስቶ እስከ ባታቸው ድረስ በአንድነት ታስሮ የሚቆይ ሲሆን ቁስሉ ጠፈፍ ማለትና ስፌቱ መጣበቅ ሲጀምርም ልጃገረዶቹ በአካባቢያቸው የሚላወሱት በምስሉ እንደምታዩት በምርኩዝ ተደግፈው ነው፡፡ ንጽህናው ባልተጠበቀ ስለት የበርካታ ህፃናት ሠውነት በአንድነት የሚተለተለው ስለ የወሲብ ክፍሎች በቂ ግንዛቤ በሌላቸው ግለሰቦች ሲሆን በሚፈሰው ደም፣ ከድንጋጤ የተነሳና በመመረዝ (ኢንፌክሽን) ምክንያትም በቁጥር ጥቂት የማይባሉት በእምቡጥነታቸው ሊቀጩ ይችላሉ፡፡

የታደሉት ደግሞ ሊመሩ የሚገደዱት ቀሪ ሕይወት እምብዛም ከሠቆቃ ያልራቀ መሆኑን በተለይም የድርጊቱን ዘግናኝነት ስታስታውስ ዋሪስ ዲሪ “አንዳችን እንኳ በህይወት ልንተርፍ መቻላችን በእጅጉ የሚደንቅ ነው” ትላለች፡፡ ለአቅመ ሄዋን የደረሱት ሶማሌዎችም ብልታቸው ሲዘጋ ለሽንት መውጫ ብቻ ታስቦ የሚተውላቸው “የክብሪት እንጨት የማያሳልፍ” ጠባብ ክፍተት የወር አበባቸውን በአግባቡ ስለማያስተናግድ በየዑደቱ ረግቶና ተቆራርጦ በሚወጣው ፈሳሽ ሳቢያ ልጃገረዶቹ ለሳምንት ያህል ሊሰቃዩና ራሳቸውን እስከመሳት ደርሰው ሊወድቁ ይችላሉ፡፡

ብዙዎቹ በተለይም መለስተኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ከመኖሪያ መንደሮች ርቀው መገንባታቸው አስተማማኝ ከማይባለው የክልሉ የመጠጥና የንጹህ ውሃ አቅርቦት ጋር ተዳምሮ የልጃገሮቹ ስቃይ እንዲባባስ የማድረግ አስተዋፅኦ አላቸው፡፡ “የሴትነት ወግ” የደረሳት ሶማሌ ተራክቦ ስትጀምርም የተጣበቀውን የሰውነት ክፍል ለማለያየት የሚደረገው ቀናትን የሚፈጅ ትንቅንቅ የወንዱን ብልት ጭምር በመፈግፈግ እንዲቆስል ምክንያት ይሆናል፡፡

ብዙሃኑን የሶማሌ ሴቶች የመጀመሪያው ፆታዊ ግንኙት ጠባሳማው የሠውነት ክፍል ከሚያስከትለው ስሜት አልቦነት ጋር ተዳምሮ ወሲብን ከደስታ ይልቅ የስቃይ ምንጭ አድርገው እንዲቆጥሩ ለሚያስገድድ የዕድሜ ልክ የሥነ-ልቦና ፈተና ይዳርጋቸዋል፡፡ የጤና ተቋማትና የህክምና ባለሙያዎች እንደ ብርቅ በሚታዩበት በዚሁ ክልል ለነፍሰ ጡርነት የበቁት ሶማሌዎች ደግሞ በተፈጥሮ አምጠው መውለድ ካልቻሉ ዕጣ ፈንታቸው በልምድ አዋላጆች በዘፈቀደ ለሚፈጸም አካልን ቆራርጦ ጽንሱን የማውጣት አደገኛ ትልተላ ሠለባ መሆንን ጭምር የሚያስከትል ነው፡፡

በዕምነት ሽፋን አንድ ቤተሰብ እንኳ የማስተዳደር አቅም የሌላቸው በርካታ የሶማሌ ወንዶች በመኖሪያ አካባቢያቸው እስከ አራት ሚስቶች የማግባት “መብት” ያላቸው ሲሆን በዚህም ላለመገደብ ከፈለጉ የሚጠበቅባቸው ነባሮቹን በማሰናበት በአዳዲስ ልጃገረዶች መተካት ብቻ ነው፡፡ የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ኒሪ ኒሪ በተባለ የገጠር ቀበሌ ያገኛት አንዲት ሴት ዛሬ በሕይወት የሌለ አጐቷ በማፈራረቅ ካገባቸው አስራ ሁለት ሚስቶች በድምሩ ሃምሳ አራት ልጆች ስለመውለዱ እንዳጫወተችው ያስታውሳል፡፡

ይህን መሠሉ ተጠያቂነት የሌለበት የጋብቻ ሂደትም ያለ በቂ ኒክሃ ወይም የፍቺ ካሣ ከትዳራቸው የሚፈናቀሉ የሶማሌ ሴቶችን አሃዝ እንዲያሻቅብ ሲያደርግ ባል አልቦ የሆኑትም በለስ ቀንቷቸው ዳግም እስኪዳሩ ድረስ ብልታቸው ተመልሶ እንዲጣበቅ ሊገደዱ ይችላሉ፡፡ በጐሳዎች መካከል የሚፈጠርን ቅራኔ ለማብረድ የሶማሌ ልጃገረዶች በዕርቅ ወቅት እንደ ስጦታ ተቆጥረው ለፀበኛው ወገን ሲበረከቱ ወይም በዕድሜ አያቶቻቸው ለሚሆኑ አዛውንቶች ተድረው ማየትም በአካባቢው ፈጽሞ እንግዳ የሚባል ገጠመኝ አይደለም፡፡

በሶማሌዎች ዘንድ የተንሰራፋው ፆታዊ መድልዎ ለሙታን ሴቶችም እንደሚተርፍ ዋቢ የሚሆነው ደግሞ ህልፈተ ሕይወትን ባስከተለ አደጋ ሳቢያ ለሴት ሟች ቤተሰቦች የሚሰጠው የ5ዐ ግመሎች የካሣ ክፍያ መጠን ለወንድ መሠል ተጠቂ ቤተሰቦች ከሚደርሰው በግማሽ የሚያንስ ማካካሻ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ ከጨለማው ዘመን እምብዛም ያልተላቀቁትን ድሪአቸው ቁስላቸውን የማይሽፍነውን የሶማሌ ሴቶች ውስብስብ ማኀበራዊ ውጣ ውረድ መዘርዘር በቀላሉ አይታሰብም፡፡

ነገር ግን ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ “የሴቶች ግርዛት ይቁም!” ሲባልና ይኸው ድርጊት ከወንጀል በተቆጠረባት አሜሪካም “የገዛ ልጁን ገርዟል” በሚል ኢትዮጵያዊው ካሊድ ከጥቂት አመታት በፊት መቀመቅ መውረዱን የሰማነው በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ የሶማሌ ሴቶች ላይ የገዛ ወገኖቻቸው የሚፈጽሙት ኢ-ሠብአዊ ትልተላ ከሕጋዊነት ያልተናነሰ ከለላ ተሰጥቶት ባለበት በአሁኑ ወቅት መሆኑ ሊረሳ አይገባውም፡፡

“ግርዛት በተንሰራፋባቸው አገራችንን በመሳሰሉት አካባቢዎች በሂደቱ የተሳተፈውን ሕብረተሰብ ሰብስበህ በማጐር ለችግሩ መፍትሄ ማምጣት አትችልም፡፡ ማድረግ የምትችለው የድርጊቱን አስከፊነት በማስረዳት የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ማስተማር ብቻ ነው” ሲሉ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በካሊድ የፍርድ ሂደት ዙርያ በወቅቱ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ከሰጡ እነሆ የልጃገረዶችን እድሜ የሚስተካከሉ ተጨማሪ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ግን መፍትሄ የተባለው ትምህርት መዲናችንን ካደመቁት ማስታወቂያዎች አልፎ የችግሩ ማዕከል ወደሆነው የሶማሌ ክልል መቼ ይሆን የሚደርሰው?

በየዓመቱ በጐዳና ላይ ሩጫ ጭምር ታጅቦ የሚዘከረው “የሴቶች ቀን”፣ በየደረጃው በሥነ-ፆታና ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ዙርያ የሚደረጉት ስብሰባዎችና ወርክሾፖች፣ ፆታዊ ጥቃትንና የሴት ልጅ ግርዛትን በመቃወም የሚስተጋቡ ንግግሮች፣ በጉዳዩ ዙርያ ሊሰሩ የተቋቋሙ ድርጅቶች እና ሕልውናቸውን በሴቶች ላይ ያደረጉትን ግለሰቦች የመሳሰሉት ሁሉ 2 ሚሊዮን ያህሉ የሶማሌ ሴቶች ከሚገኙበት ሠው ሠራሽ አረንቋ ለማውጣት የተሳናቸው የቦታው ርቀት ገድቧቸው፤ ድርጊቱ የቀድሞው የክልሉ ኘሬዝዳንት አብዲ ኢሌ ፈጸሙ ከተባለው ወንጀል አንሶ ወይስ “የሴቶች ጉዳይ” እነሱን ሳይመለከት ቀርቶ?

Click to comment

More in ማህበራዊ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top