Connect with us

የአብን መግለጫ

የአብን መግለጫ
Photo: Social Media

ፓለቲካ

የአብን መግለጫ

የአብን መግለጫ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የሕወኃት ሕገ ወጥ ቡድን በወልቀይትና ራያ የአማራ ታሪካዊ ግዛቶች ላይ ሊያደርግ ያሰበዉ ምርጫ ተቀባይነት እንደሌለዉ ይገልፃል!

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የኢፌድሪ ሕገ መንግስትን በተመለከተ የሚያራምደዉን ወጥ አቋም በተለያዩ ጊዜያት በግልጽ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ የአብን አቋም የአማራ ሕዝብ ሕገ መንግስቱን በማርቀቅም ይሁን በማጽደቅ ሂደቶች በሴራ የተገለለ እና እንዳይሳተፍ የተደረገ በመሆኑ፤ ሰነዱም በአማራ ጠል ትርክት የተቃኘ፤ ኋላ ቀር፤ ለሀገር አንድነት እና ደኀንነት የስጋት ምንጭ በመሆኑ ሊቀየር(ሊሻሻል) ይገባዋል የሚል ነዉ፡፡

አብን የአማራ ሕዝብ እንዲሁም የመላዉ ሀገራችን ሕዝቦች ችግሮች የሚፈቱት ሕገ መንግስታዊ እና መዋቅራዊ ለዉጦችን በማድረግ እንደሆነ በመገንዘብ የትግል ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ነገር ግን አሁን ያለዉ ሕገ መንግስት፣ በሕገ መንግስቱ መሰረት የተደነገጉ ሕግጋና የተመሰረቱ ተቋማት በሥራ ላይ መሆናቸዉ የማይካድ በመሆኑ በሕገ መንግስቱ እና በሌሎች ሕግጋት መሰረት አቤቱታዎችን የማቅረብ ብሎም ክርክሮችን የመምራት ጉዳይ የሚታለፍ አይሆንም። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሕወኃት መራሹ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት በክልሉ ዉስጥ ምርጫ ለማድረግ የሰጠዉ ዉሳኔ ሕገ መንግስቱን የሚቃረን እንደሆነ ገልጾ እርምት ሲጠይቅ በዚህ አንድምታ እና ተግባቦት መነሻነት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

በታሪክ በአማራዉ ክፍል በጎንደር ክፍለ ሀገር ስር የነበሩት ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ጠለምት እንዲሁም በወሎ ክፍለ ሀገር ስር በዋግና የራያና ቆቦ አዉራጃ ስር የነበሩት ኮረምና ራያ(አላማጣ፣ መሆኒ፣ ዋጃ) አካባቢዎች ያለዉ ሕዝባችን የሕወኃት የጥፋት ኃይል ለበርካታ አስርት ዓመታት በከፈተባቸዉ የተቀነባበሩ የማሰደድ፤ የጅምላ ጭፍጨፋ፤ የዘር ማጽዳት እና ማጥፋት ወንጀሎች አማካኝነት በአካባቢዎቹ ከሚኖረዉ የአማራ ሕዝብ መካከል ከፊሉ ሕይወቱን በግፍ ጭፍጨፋ የተነጠቀ ሲሆን ከፊሉ ደግሞ በሀገር ዉስጥ እና በሀገር ዉጭ ለስደት ኑሮ እንደተዳረገ ይታወቃል፡፡ በዚህም በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 38(1) ድንጋጌ መሰረት ነጻ ገለልተኛና ፍትኃዊ በሆነ ሥርዓት በሚደረግ ምርጫ የመምረጥ የመመረጥ መብቱ ሊጠበቅለት የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ የለም፡፡

አብንን ጨምሮ ከተፅእኖ ነጻ በሆነ መንገድ ለምርጫ የሚቀርቡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በማይኖሩበት ኂደት የሚካሔድ ምርጫ የመመረጥን ይሁን የመምረጥ መብትን የሚጠብቅ ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህም የሕወኃት ዉሳኔ እቆምለታለሁ የሚለውን የሕገ መንግስቱን አንቀፅ 38(1) በግልጽ የሚቃረን ነዉ፡፡ በአጭሩ ምርጫዉን በማንአለብኝነት አካሂዳለሁ በማለት ሕወኃት በደረሰበት ዉሳኔ መሰረት የሚከናወን ኂደት በግልጽ የመመረጥ መብታችንን የሚገድብና የሕዝባችንን ጥቅም በዘላቂነት የሚፃረር በመሆኑ አብን የዚህ ሕገ ወጥ ተግባር ተባባሪ አይሆንም፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ስለፌደራል መንግስቱና ክልሎች ስልጣን በሚደነግገዉ የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 52(1) ስር ለፌደራል መንግስቱ በተለይ(በግልጽ) ወይንም ለፌደራል መንግስቱና ለክልሎች በጋራ ያልተሰጠ ስልጣን የክልል መንግስታት ስልጣን እንደሆነ የተደነገገ ሲሆን ሀገራዊም ሆነ ክልላዊ ምርጫን የተመለከቱ ጉዳዮችን የመወሰንና የምርጫ ሕጎችን የማዉጣት ስልጣን እንደ ቅደም ተከተላቸዉ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 55(መ) እና 51(15) ላይ ለፌደራል መንግስቱ የተሰጡ ናቸዉ፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በሕገ መንግስቱ 52(2) ሥር በተለየ ሁኔታ የክልሎች ስልጣን ተዘርዝሮ ይገኛል፤ ነገር ግን በዚህ ዝርዝር ዉስጥ ምርጫን የማካሔድ ስልጣን አልተካተተም፡፡

በዚህም መሰረት በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 102(1) ድንጋጌ ሀገርአቀፍና ክልላዊ ምርጫን እዲያካሂድ ስልጣን ተሰጥቶት እንደ አንድ በሕገ መንግስት የተጠቅሰ አካል ሆኖ የተቋቋመዉ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሕግ መንግስቱ አንቀጽ 102(2) መሰረት የኃላፊዎች ሹመት የሚሰጠዉ፣ ስልጣንና ተግባሩን የሚወስን አዋጅ የሚወጣለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመሆኑ ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የማካኄድ ስልጣን ከክልሎች የስልጣን ማዕቀፍ ዉጭ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ነዉ፡፡

በመሆኑም ክልላዊ ምርጫን የማካኄድ ስልጣን በግልጽ ለፌደራል መንግስቱ የተሰጠ ስለሆነና በልዩ ሁኔታም ቢሆን ለክልሎች ያልተሰጠ ስለሆነ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በክልሉ ምርጫ የማካኄድ ስልጣን ስለሌለዉ የክልሉ ምክር ቤት የሰጠዉ ዉሳኔና ይህንኑ ተከትሎ የሚከናወኑ ምርጫን የማስፈጸም ድርጊቶች የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 52(1)፣ 55(መ)፣ 102(1) የሚቃረን በመሆኑ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 9(1) መሰረት ተፈጻሚነት ሊኖረዉ ስለማይችል ዉሳኔዉ ተቀባይነት የለዉም፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በሕወኃት ኃይል ተዘርፈዉ ወደ ትግራይ በተካለሉት የአማራ ርዕስቶች ዙሪያ ያሉትን የወሰን ጥያቄዎችን በተመለከተ መላዉን የአማራ ሕዝብ እንዲሁም ፍትኅ እና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን ከጎኑ በማሰለፍ በተዛማጅ የሕግ እና የፖለቲካ ትግሎች ዳር እንደሚያደርስ ለማሳወቅ ይወዳል፡፡

በዚሁ አጋጣሚ ከአማራ ሕዝብ ተዘርፈዉ በሀይል የተያዙትን እነዚህን ግዛቶች ወደነበሩበት ከመመለስ ዉጭ ሆነዉ የተቃኙ ማናቸዉም የፖለቲካ ግንኙነቶች እና ድርድሮች ተግባራዊ ሊደረጉ እንደማይችሉ ድርጅታችን ከወዲሁ ለማስገንዘብ ይፈልጋል፡፡

በመጨረሻ ሕወኃት ከዚህ ኃላፊነት ከጎደለዉ በሀገር አንድነት እና ሉአላዊነት ላይ አደጋን ሊያስከትል ከሚችል እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲታቀብ እያሳሰብን የሀገሪቱ መንግስት ይሄን ያልተገራ፤ የማንአለብኝነት ሕገ ወጥ ኂደት በሕግ አግባብ እንዲያስቆም እንጠይቃለን፡፡

መላዉ የአማራ ሕዝብና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዉያን የዚህን ሕገ ወጥ ቡድን ሀገር አፍራሽ እንቅስቃሴ በአንክሮ በመከታተል የሕዝባችንና የሀገራችንን ኅልዉና ለማስጠበቅ ድርጅታችን በሚያደርገዉ እንቅስቃሴ ከጎናችን እንድትቆሙ ስንል ሀገራዊ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ !
አዲስ አበባ ፣ ሸዋ ፣ ኢትዮጵያ
ሰኔ 19 ቀን 2012 ዓ.ም

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top