ቀና እንበል! ቀና እንሁን!
(ቢልለኔ ሥዩም)
ቀና የሚለው የአማርኛ ቃል ልዩ ልዩ ትርጓሜዎችን ይዟል፡፡ የሚሰጠን ትርጉም አንዳንድ ጊዜ እንደአነባበባችንም ይወሰናል፡፡ እንደ ዓውዱ ባህሪን፣ ተግባርን፣ ውጤትን ወይም ስሜትን ጠቅለል አድርጎ ይገልጻል፡፡
ቀና፡- ቀናነት፣ አዎንታዊ ባህሪንና ገንቢ አመለካከትን የማሳየት አቅም
ቀና፡- ሰውነትን ቀጥ አድርጎ፣ ሳያጎነብሱ ወይም ሳይጎብጡ መቆም
ቀና፡- ተቃና፣ ተሳካ፣ ተከናወነ
ቀና፡- የቅናት ስሜት
ይህ ባለ ሁለት ፊደል ቃል ተጨማሪ ትርጓሜዎችንም ሊያካትት ይችላል፡፡ የቃሉ በትርጓሜ መበልፀግ ከላይ የተዘረዘሩ ትርጓሜዎችን ከብሔራዊ ህብርና ውቅር አንፃር እንድቃኛቸው ጋብዞኛል፡፡
በግሌ ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ውስጥ ዳግመኛ መስቀለኛ መንገድ ላይ እንደተገኘች ይሰማኛል፡፡ የምትመርጠው መንገድና የምትጓዝበት ጎዳና የሚወሰነው፣ አመራሮችን ጨምሮ እያንዳንዱ ዜጋ ለማድረግ ወይም ላለማድረግ በሚመርጣቸው ተግባራት አማካይነት ነው፡፡
ባለፈው ሁለት ዓመት ከመንፈቅ፣ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ከምንጊዜውም በበለጠ ተተግብሮ፣ ለተጨባጭ ዴሞክራሲና ብልፅግና መሠረትን ሲጥል ተመልክተናል፡፡ በፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ተጠፍንጎ የቆየው ሕዝብ፣ ለብዙ ዓመታት የናፈቃቸው ዴሞክራሲያዊ እሴቶች እንዲሰፍኑ ይጠይቅ ይዟል፡፡ ባለፈው ሁለት ዓመት ተኩል የተካሄዱት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሕግ ማሻሻያዎች ትክክለኛው ዴሞክራሲ በምልዓት እንዲሰፍን የሚያስችልን ወጋገን ፈንጥቀዋል፡፡ ወደ ናፈቅነው ግብ የሚያደርሰን ጎዳና ረዥም ስለሆነ ጉዞው ቀና ይሆንልን ዘንድ ምኞቴ ነው፡፡
ለውጥ በመሠረታዊነት ያለማቋረጥ የሚመዘንና ተራማጅ ነው፡፡ ይህም በታሪካችን የተከናወኑና አገራዊ ዕድገታችንን ሲያሰናክሉ የቆዩ የሥርዓት መስተጓጎሎችንና ልንደርስበት ከምንፈልገው ውጤት ጋር የማመዛዘን ሒደትን የሚያመለክት ነው፡፡ የተሳሳተ፣ ብልሹና አጥጋቢ ያልሆነውን ሥርዓት ማረም ወይም ማሻሻል በእርግጥም ቁርጠኝነትን የሚሻ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የተሃድሶ ጉዞ፣ የፖሊሲ፣ የሕግና የተቋማዊ ማሻሻያዎች አንቀሳቃሽ ሞተር ሆኖ፣ በየሥርዓቱ የተሰገሰጉ አገራዊ ማነቆዎችን የማስወገዱን ጉዞ የጀመረው ይኼው ከምንጊዜውም በበለጠ ሁኔታ የታየ ከፍተኛ ቆራጥነት ነው፡፡
ይህንን ቆራጥነት የተሞላበት ብርታት ሰጪ ከፍተኛ አመራር በቅርበትና በየዕለቱ የመመልከቱን ዕድልና ክብር አግኝቻለሁ፡፡ ትክክለኛና ተጨባጭ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ የቱን ያህል ውስብስብ እንደሆነ ልንዘነጋ አይገባም፡፡ በለውጥ አስተዳደር ጅማሬ፣ ሕዝባችንን ለብዙ ዘመናት ያሰቃዩት ችግሮች በአንድ ጀንበር ከመኖር ወደ አለመኖር ይሸጋገራሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት፣ አለፍ ሲልም የለውጥ ሒደትን ውስብስብነት ያለመገንዘብ ነው፡፡ በተጨማሪም ይህ ጅማሬ ለብዙ ዓመታት ሲብላሉ የነበሩ ጥያቄዎች በአንድ ጊዜ እንዲገነፍሉ መንገድ ከፍቷል፡፡ ለእነዚህ የረዥም ጊዜ ጥያቄዎች በአፋጣኝ መልስ የማግኘት ፍላጎትም ፀንቶ ተስተውሏል፡፡ ነገር ግን ሥርዓትን ከመቀየር አንፃር፣ አንድ አራስ ልጅ ተወልዶ ገና ድክ ድክ ለማለት በሚጀምርበት የሁለት ዓመት ተኩል አጭር ጊዜ ውስጥ፣ ሁሉም ፍላጎቶች ተሟልተው ችግሮች በሙሉ ይፈታሉ ብሎ ማሰብ የማይሆን ነገር ነው፡፡ ማለም የአንድ ጊዜ፣ ህልምን መተግበር ግን የዘመናት ሥራ ነው እንደሚባለው፡፡
በእርግጥ እንደ አገር ተጭነውን የቆዩትንና በሥርዓቶቻችንና በዕሳቤያችን ውስጥ ጠልቀው ሥር የሰደዱትን ችግሮች ወቅታዊ መፍትሔ ልናበጅላቸው ያስፈልጋል፡፡ ያስከተሉብን ጉዳት የማይቀለበስ ቢሆንም፣ በለውጡ ጅማሬ ወቅት ያገኘናቸውን ትርፎች የሚያጠናክር ጊዜ፣ አርቆ አሳቢነት፣ ገንቢ ተሳትፎና እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች ተጨምረውበት ሊጠገን ይችላል፡፡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በዚህ የአገር ግንባታ ሥራ ቢሳተፉ ያለ ጥርጥር ውጤቱ የቀና ይሆናል፡፡
በማቆጥቆጥ ላይ በሚገኘው ዴሞክራሲያዊ ባህላችን ሐሳብን በነፃነት መግለጽ እየተስፋፋ የመጣ ሲሆን፣ ለቁጥር የበዙ ትንተናዎችና ውይይቶችም በልዩ ልዩ መድረኮች እየተካሄዱ ነው፡፡ ነገር ግን ተንታኞቹና ሐያሲዎቹ ቀድሞ የነበሩ፣ እንዲሁም አዳዲስ ችግሮችን አስመልክቶ ትንተናቸውን ሲያካሂዱ ሥርዓት ተኮር ችግሮችን ለመፍታት ሰብዓዊ ተፈጥሮ የሚጫወተውን ሚና ያካተቱበት ጊዜ አልገጠመኝም፡፡ ላሉብን ችግሮች መፍትሔ ሆነው የሚሰነዘሩት ትንተናዎችና ክርክሮች በመዋቅር፣ በቅርፅና በፖሊሲ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ከዚያ ጀርባ ስላለው አንቀሳቃሽ ኃይል ብዙ አይነገርም፡፡
እያንዳንዱ ሥርዓት በተወሳሰበ የፍላጎት፣ የስግብግብነትና የድንጋጌዎች መረብ አማካይነት ስለሚተዳደር በዚያ ሥርዓት ውስጥ ለውጥ የሚካሄድበትን ቅርፅ፣ አካሄድና ፍጥነት ይወስናሉ፡፡ የሥርዓት ማነቆዎችን ገምግሞ ዋነኛ መንስዔያቸውን ነቅሶ ማውጣት፣ ተመጣጣኝ መፍትሔዎችን ማዘጋጀትና ከለውጡ መንፈስ ጋር በሚጣጣም መንገድ ማከናወን ወኔን የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡ እዲህ ባለው ሒደት፣ በፍጥነት ተለዋዋጭ በሆነ ነባራዊ ሁኔታና ሳያቋርጥ በሚቀያየረው ሉላዊ ሥርዓት ውስጥ ልዩ ልዩ ፍላጎቶች ቅርፅ ይይዛሉ፡፡ እነዚህ ፍላጎቶች በተገቢው ዕሳቤ ሊቀረፁ የሚችሉትን ያህል፣ በአቋራጭ ጥቅም በማካበትና የበላይነትን በማረጋገጥ መሻት ሊዋጡ ይችላሉ፡፡ ይህም በተራው የምንፈልጋቸውን ውጤቶች ቅርፅ፣ አካሄድና ፍጥነት ይለውጣል፡፡
እንደ እኔ አመለካከት በለውጥ ዓይነተኛ ተፈጥሮ ውስጥ ነባራዊ ሁኔታዎችን ማናወጥ ይስተዋላል፡፡ ይኼም ማለት በነባራዊው ጉዞ የተፈጠሩትን ችግሮች ብቻ ሳይሆን፣ ለችግሮቹ መፈጠር ገፋኢ ምክንያቶችንና መደላድሎችንም ጭምር ለውጡ ይነካቸዋል፡፡ ከፖሊሲ አንፃር ሲታይ፣ አስፈጻሚው አካል ለውጥ የሚያካሂደው የችግር መንስዔ ሆነው ባገኛቸው ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ ይህንን ውሳኔ ተከትሎ ነውጥ መከሰቱ ስለማይቀር፣ ከነባራዊው ሁኔታ ያልተገባ ጥቅምን ካገኙ አካላት ዘንድ ተቃውሞ ይገጥማል፡፡ ምናልባትም የ’ቀና’ን አንደኛውን ትርጉም (የቅናት ስሜት የሚለውን) ለመጠቀም ይህ ትክክለኛው ሥፍራ ነው፡፡ አጉል ጥቅሙ የተነካበት አካል በለውጡ ሌሎች ካገኙት ጥቅም አንፃር የሚገኝበትን ቦታ አወዳድሮ ያለመርካት ስሜት ይፈጠርበታል፣ ወይም በሌሎች ስኬት የተነሳ የምቀኝነትና የጥላቻ ስሜት ያድርበታል፡፡
ሰብዓዊ እንደ መሆናችን እንዲህ ያሉ ስሜቶች ሊገዙን ይችላሉ፡፡ የእነዚህ ስሜቶች አዝማሚያ በተሰማን ጊዜ በቶሎ ለመግራት ካልቻልን፣ ራስን ብቻ ሳይሆን አገርንም ጭምር የሚያወድም ውጤት ሊያስከትል ይችላል፡፡ የዚህ ስሜት ግላዊ ተፈጥሮን መላበስ፣ በፖለቲካና በአስተዳደር ላይ የሚያሳርፈውን ተፅዕኖ ሊጋርድብን ይችላል፡፡ ሆኖም በአግባቡ ሊፈተሽ የሚያስፈልገው ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በየምንሄድበት ማንነታችንና ሥነ ልቦናዊ ጓዛችን አብሮን መሄዱ ስለማይቀር፣ ስሜቶቻችን በፖለቲካና በአስተዳደር ውስጥ ያላቸው ሥፍራ ቸል ሊባል አይገባም፡፡
ፖለቲካዊ የበላይነትን ለማግኘት በሚደረግ ሽኩቻ ውስጥ ጎልቶ የሚታየው ቅናትና ተከትሎት የሚመጣው አድርባይነት፣ ለውጥን ከማደናቀፍ አልፎ አገርን ለውድቀት ይዳርጋል፡፡ ብሔራዊ አንድነትን ልንገነባ ስንነሳ የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልፅግና ሊያወድም የሚችለውን ይህንን ሞገደኛ ስሜት ልናሳልፍ የምንችልባቸውን ልዩ ልዩ መንገዶች ማሰብ እጅግ ያስፈልገናል፡፡ እንዲህ ያለው ስሜት በብዙኃኑ ዘንድ ገዝፎ መገኘቱ አገራዊ አንድነትን ለማጎልበት የሚደረጉ ጥረቶችን ይፃረራል፡፡ ጎጠኝነት፣ ወገንተኝነት፣ ጭፍን አክራሪነትና የመሳሰሉት ባህሪያትም መገለጫዎቹ ናቸው፡፡ እንዲህ ያለው በውስጥ የሚከሰት መፍረክረክ በውጭ ኃይሎች የተቀመሩ አደጋዎች ዘልቀው ገብተው አንድነታችን እንዲመርዙ መንገድ ያመቻችላቸዋል፡፡ ሁለተኛው የቀና ፍቺ የሚያስፈልገን እዚህ ላይ ነው፡፡ ቀና ማለት ሳይጎብጡ መቆም ያስፈልጋል፡፡
ይህ ቃል ከሚከስተው የአካላዊ አቋቋም ፍቺ ባሻገር፣ በብሔራዊ አንድነት ዓውድ ውስጥ ለሚገኘው የጋራ ዕድገታችን ሲባል፣ ትኩረታችንን በልዩነታችን ላይ ከማድረግ ይልቅ፣ በሚያመሳስሉንና በሚያስማሙን ጉዳዮች ላይ በመጽናት ቀና ብሎ መቆም እንደሚጠይቅ ያመለክታል፡፡ በአብሮነታችን ውስጥ እያንዳንዳችን ዋጋ እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ቀና ማለትን ብንመርጥ፣ ገንቢ በሆነ ሁኔታ ብናስብና ብንሠራ፣ አንድነትና ብልፅግና የእኛ መሆናቸው አይቀርም፡፡ ኅብረት እንጂ መከፋፈል ደረትን አያስነፋም፣ ቀና አያሰኝም፡፡
ምናልባትም ሁሉን አቀፍ የሆነው የቀና ትርጉም የሚከተለው ነው፡፡ አዎንታዊ ባህሪንና ገንቢ አመለካከትን ማሳየት ለብሔራዊ አንድነት ዓይነተኛ ጉዳይ ሲሆን፣ በመጨረሻ ከተቀመጠው የቀና ፍቺ (ተቃና፣ ተከናወነና ተሳካ) ጋር በቀጥታ የሚዛመድ ነው፡፡ ቀናነት የተዘጉ በሮችን የማስከፈት አቅም ያለው አስተሳሰብና አቋም ነው፡፡ ከፀጉር ስንጠቃ ይልቅ መፍትሔ መፈለግን ይመርጣል፣ በመላ ምት ከመዳከር ይልቅ ሐሳቦችን ያፈልቃል፣ የግል ምኞትን ከማስፈጸም ይልቅ በእጅ ላለው ኃላፊነት ሳይሰስቱ ራስን ለመስጠት ያስችላል፡፡ ለገጠሙን አንዳንድ የለውጥ መሽመድመዶችም መፍትሔው ይኸው ነው፡፡ ከምወዳቸው አባባሎች አንዱ፣ “የአንድ መፍትሔ ስኬት በመፍትሔ ሰጪው ውስጣዊ ሁኔታ ላይ ይወሰናል፤” የሚል ነው፡፡ የሚፈለገው ውጤት እንዲገኝ፣ ገንቢና ተስፋን የተሞላ አመለካከት የሚጫወተውን ሚና አጉልቶ ያሳያል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ መድረክ ላይ ጎልታ ትታያለች፣ በቀጣናዊ አንድነት ላይም ጠቃሚ ሚናን በመጫወት ላይ ትገኛለች፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ሰላማዊና የበለፀገ እንዲሆን የሚያስችለው ማስተሳሰሪያ፣ አገራዊ አንድነትና የጋራ ግብ ነው፡፡ ያለፈበትን አስተሳሰብና ለዘመናት ወደ ገነባነው ምሽግ የመሮጥን ቀንበር ከላያችን አሽቀንጥረን ካልወረወርን በስተቀር፣ እንዲህ ያለውን ዕሳቤ ልንገነዘበው አንችልም፡፡ ወጣት ሆነ አዛውንት፣ የተማረ ሆነ ያልተማረ፣ በግሉ ዘርፍ የተሰማራም ሆነ የመንግሥት ሠራተኛ፣ እያንዳንዱ ሰው በእያንዳንዷ ቅፅበት ቀና አሳቢ መሆናቸውን ይጠይቃል፡፡ ልዩነትን ከሚያጎሉ ይልቅ፣ መከፋፈልን የሚጠግኑ ሰዎችን ይፈልጋል፡፡ የምንመርጠው ጎዳና ይህኛው እንዲሆን ምኞቴ ነው!
ቀና ይሁንልን! ቀና እንበል! ቀና እንሁን!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊዋ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ቃል አቀባይ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
(ምንጭ:-ሪፖርተር)