Connect with us

የሰኔ 15 ግድያ በገለልተኛ ኮሚሽን ተጣርቶ ለሕዝብ እንዲገለጽ ለጠ/ ሚሩ ጥያቄ ቀረበ

የሰኔ 15 ግድያ በገለልተኛ ኮሚሽን ተጣርቶ ለሕዝብ እንዲገለጽ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ቀረበ
Photo: Social Media

ህግና ስርዓት

የሰኔ 15 ግድያ በገለልተኛ ኮሚሽን ተጣርቶ ለሕዝብ እንዲገለጽ ለጠ/ ሚሩ ጥያቄ ቀረበ

የሰኔ 15 ግድያ በገለልተኛ ኮሚሽን ተጣርቶ ለሕዝብ እንዲገለጽ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ቀረበ

~ የባለሥልጣናቱ ሙት ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች ተዘክሯል፣

ባለፈው ዓመት ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከተሞች በጥይት ተደብድበው ሕይወታቸው ያለፈው ከፍተኛ የአማራ ክልል ባልሥልጣናትና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ላይ የተፈጸመው የወንጀል ድርጊት፣ በገለልተኛ ኮሚሽን ተጣርቶ ለሕዝብ እንዲገለጽ የሟቾች ቤተሰቦች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ጻፉ፡፡

የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አምባቸው መኰንን (ዶ/ር)፣ አማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴና የክልሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ፣ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኰንንና የሜጀር ጄኔራል ገዛዒ አበራ ሙት ዓመት በተለያየ ቦታዎች በተለያዩ ዝግጅቶች ሰኔ 13 እና 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ተዘክሯል፡፡

የሦስቱ የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሙት ዓመት መታሰቢያ ‹‹ደም እንለግሳለን እንጂ፣ ደም አናፈስም›› በሚል መሪ ቃል ጤና ሚኒስቴር አጠገብ በሚገኘው የደም ባንክ ማዕከል ‹‹ደም በመለገስ›› ታስቦ ውሏል፡፡

በመታሰቢያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበልና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የከተማ ልማት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ዣንጥራር ዓባይ ሲገኙ፣ የሟቾቹ ቤተሰቦች ጓደኞቻቸው ተገኝተዋል፡፡ በሥራ ላይ እያሉ በጥይት ተደብድበው ስለተገደሉት የክልሉ ባለሥልጣናት የሚያወሳ ሰፋ ያለ መጣጥፍ የያዘ ‹‹አምባዬ የተካደው ፍትሕ›› የሚል መጽሔትም ታትሞ ለሥነ ሥርዓቱ ታዳሚዎች ታድሏል፡፡ በኅትመቱ ውስጥ ከተካተቱት መጣጥፎች ውስጥ የሟቾች ቤተሰቦች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቀጥታ ተጽፎ ለ15 ከፍተኛ የፌዴራል፣ የክልልና የሃይማኖት ተቋማት ግልባጭ የተደረገ ደብዳቤም ተካቷል፡፡

በሟቾች ቤተሰቦች በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጻፈው ‹‹ፍትሕ እንፈልጋለን›› ደብዳቤ እንደሚያብራራው፣ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በአማራ ክልል ባለሥልጣናትና በአገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ላይ የተፈጸመው የወንጀል ድርጊት እንደ ሕዝብም ሆነ እንደ አገር አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡ በወንጀሉ አፈጻጸም ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳታፊ የነበሩ ተዋንያን፣ በሐሳብ፣ በገንዘብና በቁሳቁስ የደገፉ አካላት እንዳሉ የፀና እምነት እንዳላቸው ሠፍሯል፡፡

በክስ ሒደቱም ቁንጮ ተጠርጣሪዎችን ዘንግቶ ጥቂት የሒደቱ ተጠርጣሪዎችን ብቻ ማካተቱ፣ ይባስ ብሎም የአብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች ክስ በፖለቲካ ውሳኔ መዘጋቱና ከእስር እንዲፈቱ መደረጉ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የፍትሕ ጠበቃዎችን እንዳሳዘነ ገልጸዋል፡፡

የአገረ መንግሥቱን ህልውና አደጋ ላይ ለጣሉበት ክህደታቸው ምንም ዓይነት የወንጀል ተጠያቂ ሳይሆኑ መቅረታቸው፣ አገራዊና ፖለቲካዊ የሽግግር ለውጡን ፍትሐዊነት አደጋ ላይ ጥሎታል የሚል እምነት እንዳላቸውም አክለዋል፡፡ የክልል ፕሬዚዳንትና ሁለት ወሳኝ ባለሥልጣናት፣ እንዲሁም በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሆነውን የአገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ከእነጓደኛቸው ሕይወት እንዲቀጠፍ ያደረጉ ሁሉ ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡

የሟቾች ቤተሰቦች የገዳይ አስገዳይ ቡድን የፈጸመው ወንጀል የመላው አገሪቱን የለውጥ አካሄድ ቅርቃር ውስጥ የከተተ፣ አገራዊ ተስፋን ያጨለመና ሕዝቡን እጅግ ያሳዘነ በብሔራዊ ክህደት የሚበየን አውዳሚ ተግባር መሆኑንም አበክረው ገልጸዋል፡፡ በወንጀሉ የተሳተፉ፣ በገንዘብና በተለያዩ መንገዶች ለግድያው ተባባሪ የነበሩ ተጠያቂ ካለመደረጋቸውም በላይ፣ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩትም ተጠያቂ ሳይደረጉ ክሳቸው በፖለቲካ ውሳኔ መቋረጡ የወንጀሉ ተዋንያንን የልብ ልብ እንዲሰማቸው እንዳደረጋቸውም አክለዋል፡፡ እነዚህ ተዋንያን ተጨማሪ ሴራ እንዲጎነጉኑ ሕዝባዊ አንድነትን እንዲሸረሽሩ ተጨማሪ ዕድል እንዲያገኙና ሕዝብ ሲታገለው ወደነበረው የቀድሞው አስከፊ ሥርዓት መመለስ እንዳይሆንም ሥጋታቸውን አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወንጀሉን ድርጊት አጣርቶ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እውነታውን የሚገልጽ ገለልተኛ ኮሚሽን እንዲቋቋም ትዕዛዝ እንዲሰጡላቸውና ወንጀሉን ያቀናበሩ፣ የተሳተፉ፣ ወንጀሉ እንዲፈጸም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሲያደርጉ በነበሩ መንግሥታዊ አካላትና ተባባሪዎች ላይ ተገቢው ፍትሕ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

የሟቾች ሙት ዓመት በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን ታች ጋይንት ወረዳ (የአምባቸው (ዶ/ር) የትውልድ ሥፍራ)፣ እንዲሁም በምሥራቅ ጎጃም ዞን በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶችና ለመታሰቢያቸው ችግኝ በመትከል ታስቦ ውሏል፡፡

በተመሳሳይ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በአጃቢያቸው በጥይት ተመትው የተገደሉት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኰንንና የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አመራር የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ገዛዒ አበራ የሙት ዓመት መታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል፡፡ ከአትላስ ወደ ሩዋንዳ የሚወስደው መንገድ ‹‹ጄኔራል ሰዓረ መኰንን ጎዳና›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶት መታሰቢያ ሆኗል፡፡

በተገደሉበት ሞተ ዕለት ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ታስቦ በዋለው የሙት ዓመት መታሰቢያ ዝግጅት ላይ ተገኝተው የመንገድ ስያሜውን ቀይ ሪባን የገለጡት፣ የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ናቸው፡፡ ምክትል ከንቲባው የመታሰቢያውን መንገድ ስያሜ ካበሰሩና ወደ ቢሮአቸው ከተመለሱ በኋላ፣ ‹‹ለአገር ለፍቶ ለአገር መሞት ከክብርም በላይ ክብር ነው፡፡ ይኼንን ደግሞ አገሩን ያለ እረፍት በፅናትና በብርታት እያገለገለ የተሰዋው ወንድሜ ጄኔራል ሰዓረ ሕይወቱ ከማለፉ ከሰዓታት በፊት በጋራ ችግኝ ተክለን ነበር፡፡ ለጄኔራሉ መታሰቢያነትም በጋራ ችግኝ የተከልንበት ቦታ የመታሰቢያ ፓርክ አስጀምረናል፡፡ ቦታው ላይ ያለው መንገድ ‹‹ከሩዋንዳ ወደ አትላስ›› የሚወስደውንም በጄኔራል ሰዓረ ስም ሰይመናል፤›› ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው አሥፍረዋል። (ታምሩ ፅጌ ~ሪፖርተር)

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top