Connect with us

ከባርነት ቀንበር ያልወጡት የጥቁር አፍሪካ አሜሪካዊያን ሕይወት

ከባርነት ቀንበር ያልወጡት የጥቁር አፍሪካ አሜሪካዊያን ሕይወት
Photo: Social Media

ህግና ስርዓት

ከባርነት ቀንበር ያልወጡት የጥቁር አፍሪካ አሜሪካዊያን ሕይወት

ዓለም ‹‹ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ›› መልዕክትን እንካችሁ እያለች ባለችበት በዚህ ወቅት ዘረኝነትም ሌላ መልክ ይዞ ብቅ ብሏል። አፍሪካውያን ለባርነት ተግዘው ለህሊና በሚከብድ መንገድ መራራ የህይወት ጽዋን ተጎንጭተዋል። ለዘመናት በዘረኝነት አስተሳሰብ እንደተጨቆኑ፣ ከጭቆናቸው ነፃ ለመውጣት እንደታገሉ ከእዚህኛው ዘመን ደርሰዋል።

ከሰሞኑ በጆርጅ ፍሎይድ ሞት ለበርካታ መቶ ዓመታት የቆየውን ጭቆና፣ ታሪካዊ ኢ-ፍትሐዊነት፣ የፖሊስ ጭካኔና ሌሎችም መሠረታዊ ችግሮችን ፍንትው አድርጎ ያሳየ ክስተት ታይቷል። አሜሪካዊው ነጭ ፖሊስ ጥቁር አሜሪካዊውን ጆርጅ ፍሎይድን አንገቱን ከመሬት አጣብቆ ትንፋሽ እስኪያጥረው ድረስ ለአስር ደቂቃዎች ያህል ተንበርክኮበት በመቆየቱ ሕይወቱ አልፏል።

ታለቁ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ማርቲን ሉተር ኪንግ ከዛሬ ሃምሳ ሰባት ዓመት በፊት ይህ እንዳይሆን ህልም አለኝ ሲል ተደምጧል። ሰሚ ጆሮ ግን አላገኘም፤ ህልሙም ከአሁናዊው ዓለም የራቀውም ለዚህ ነበር። ማርቲን ሉተር እ.ኤ.አ.1963 በዋሽንግተን ዲሲ ህልም አለኝ በሚል ባስተላለፈው መልዕክት ዛሬም ድረስ ጥቁር ህዝቦች ያላለፏቸው ተግዳሮች ሆነዋል። በመልዕክቱ ጥቁር ህዝቦች ለነፃነት፣ ለሰብዓዊና እኩልነት እንዲሁም ለኢኮኖሚያዊ መብቶቻቸው እንዲታገሉ ነበር በአደባባይ ወጥቶ በፊት ቀላማቸውና በዘራቸው እየደረሰባቸው ያለው ጥቃትም እንዲያበቃ ጥሪ ያስተላለፈው።

ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ በአንድ የፖሊስ መኮንን እስትንፋሱን ሲያጣ፤ ለዘመናት ሰሚ ያጣው የዘረኝነት አበሳ ዛሬ በሺዎች የሚቀጠሩ ሰዎችን በቁጣ ወደአደባባይ አውጥቷል።

ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ነጮች ከጥቁር አክቲቪስቶች ጎራ መቀላቀላቸው ጉዳዩ የበለጠ አፅንዎትን እንዲያገኝ አድርጎታል ያሉት ከቢቢሲ ጋር ቆይታ የነበራቸው በኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አሜሪካዊያን ንቅናቄ መምህሩ ፍራንክ ሊዮን ሮበርትስ ናቸው።

እንደ ሮበርትስ ገለጻ “ቀደም ባሉት ጊዜያት በፖሊስ አመጽ የተከሰቱ አጋጣሚዎች አሻሚ ትረካ ሊኖራቸው ይችላል። በዚህ ሁኔታ ሰዎች ይህ ሰው (ፍሎይድ) ሙሉ በሙሉ መሳሪያ የሌለው እና አቅመ ቢስ ሆኖ ማየት የቻለበት አጋጣሚ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ኢ-ፍትሐዊ ተግባር ነው። አንድ የፖሊስ መኮንን ዴሬክ ቼቪን ሚስተር ፍሎይድ አንገት ላይ ለዘጠኝ ያህል ደቂቃ ተንበርክኮበት “መተንፈስ አልቻልኩም” እያለ ባለበት ወቅት ድርጊቱ በግልጽ በቪዲዮ ላይ ተመዝግቧል።

ከባርነት ቀንበር ያልወጡት የጥቁር አፍሪካ አሜሪካዊያን ሕይወት

 

በቅርቡ የተቃውሞ ሰልፎችን ከተቀላቀሉ ብዙዎች የጆርጅ ፍሎይድን ሞት በማህበራዊ ሚዲያው ወይም በእጅ ስልካቸው ማየታቸው ከእንግዲህ ቤት ውስጥ መቆየት እንደማይችሉ እንዲሰማቸው እንዳደረጋቸው፤ የጥቁር ሕይወት ያገባኛል እንቅስቃሴን ስትደግፍ እንደነበር ሃሳቧን ለቢቢሲው ጋዜጠኛ የተናገረችው ዌንግፊይሁ፤ የጆርጅ ፍሎይድ ሞት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደጎዳናዎች እንድትወጣ ያነሳሳት ልዩ ትዕይንት እንደሆነ አንዱ አመላካች ነው።

ጥቁር አሜሪካውያን በባርነት ንግድ በግዞት ከመጡበት ዕለት ጀምሮ እየደረሰባቸው ያለውን ግፍ አሁን በአሜሪካ ማህበረሰብ ማእዘን ውስጥ ወድቆ እራሱ በገዛ ሀገሩ በግዞት የሚኖረውን አፍሪካ አሜሪካዊያንን ለመታደግ አንድ ብሎ የተጀመረው የአደባባይ ጥሪ ዛሬም ድረስ ሰሚ ጆሮ ያጣ ይመስላል።

የዓለም አቀፍ መንግሥታትና ማህበረሰብ ለጉዳዩ የሰጡት ምላሽ አጥጋቢ ባይሆንም የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቦሪስ ጆንሰን፤ ስለጥቁር ህይወት ጉዳይ ይገደኛል ብለዋል በመልዕክታቸው። ሚኒስትሩ የጆርጅ ፍሎይድ ሞት በሺህ ማይል ርቆ በሚገኝ ስፍራ ነው፤ በሌላ ሀገር፣ በሌላ ስልጣን ባለው ሀገር። በዚያ ትዕይንት አንድ ጥቁር ሰው ህይወቱን በሞት ሲያጣ ስሜቱን ችላ ማለት አንችልም። እናም ሁላችንም ለሰዎች ሞት በተለይም በጥቁር ሰዎች ላይ የሚደርሱትን የመብት ጥሰቶችን ማስቆም ይገባናል።

በዚህች ሀገር ታሪክ ውስጥ እጅግ ብዝሃነት ያለው መንግሥት በመምራቴ ኩራት ይሰማኛል። በፖሊስና በሌሎች የኑሮ ደረጃዎች ውስጥ ሰፊ ቁጥር ያለውን ጥቁር ወጣት እናሳትፋለን።

በጆርጅ ፍሎይድ ሞት ምክንያት በአፍሪካ ዙሪያ ያሉ ሀገራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቃውሞ ሰልፎችን ተቀላቅለዋል። ፖሊስ በአፍሪካዊያን ጥቁሮች ላይ እያደረሰ ያለውን ጭካኔ እንዲያቆም ጥሪ እያቀረቡ ነው። በሚኒሶታ ከተማ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የተገደለው ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ ከሞተ በኋላ በአሜሪካ ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ ኢ-ፍትሐዊ የሆኑ ድርጊቶች ተገቢነት እንደሌላቸው ነው በአፍሪካ ያሉ ባለሥልጣናት ስጋታቸውን እየገለጹ ያሉት።

የአፍሪካ ህብረት የፍሎይድ ሞት “ግድያ” እንደሆነ ሲገልጽ የደቡብ አፍሪካ ገዥ ፓርቲ በዓለም አቀፉ ግንኙነቶች ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ መግለፃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት የአሜሪካ መንግሥት ኃላፊነቱን ሊወስድ ይገባል። የህብረቱ ሊቀ መንበር “በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ በሕግ አስከባሪ መኮንኖች እጅ የተፈጸመውን አሰከፊውንና ሰብዓዊነት የጎደለውን የጆርጅ ፍሎይድ ግድያ በጥብቅ ያወግዛል፤ በአሜሪካ ጥቁር ዜጎች ላይ ‹የዘር መድልዎና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች› አፈጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጠይቀዋል። የኮሚሽኑ ሊቀመንበር በዘር ወይም በጎሳ ላይ የተመሠረተ ሁሉንም የመድልዎ ዓይነቶች ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።

የዓለም አመለካከትን በብዙ መልኩ የቀየረው የአሜሪካው የጎዳና ላይ አመፅ፤ በአሜሪካ ስላለው የዘረኝነት ክርክር ምንም አስተያየት አልሰጡም የሚል ትችት እየቀረበባቸው ያሉት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ የተለያዩ የፖሊስ ማሻሻያዎችን እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል።

በማሻሻያው አሜሪካውያን ሊያውቁትና ሊያምኑ ይገባል ያሉትን ሃሳብ ሲገልጹ፤ ተጠያቂነትን ከዚህ በበለጠ መተግበርና ማሻሻል፣ ግልጽነትን ከፍ ማድረግ፤ በፖሊስ ስልጠና፣ ቅጥር ምልመላ እንዲሁም በማህበረሰብ ተሳትፎ ለሚደረገው ማሻሻያ የበለጠ ሀብትን ማፍሰስ እንዳለብን ልትረዱ ተገቢ ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።

አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2012

Continue Reading
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top