Connect with us

የእንግሊዝ ሃውልቶች አዲስ ፈተና …

የእንግሊዝ ሃውልቶች አዲስ ፈተና …
Photo: Facebook

ባህልና ታሪክ

የእንግሊዝ ሃውልቶች አዲስ ፈተና …

የእንግሊዝ ሃውልቶች አዲስ ፈተና …
(አለማየሁ ገበየሁ ~ እንግሊዝ)

ኤድዋርድ ኮልስቶን የብሪስቶል ነዋሪዋች ኩራት ነበር ። ሲበዛ ቅን ነው ይሉታል – ተወላጆቹ። ኋላ ላይ ከተማዋን እየተቀላቀሉ የመጡ ጥቁሮችና ሌሎች ግን የክፋት መጨረሻ እንደሆነ ነው የሚሰማቸው። ከነጋዴ ቤተሰቦቹ በ 1636 ተወልዶ በ 1721 ዓም አረፈ። እዚህ ከተማ ላይ ሃውልት የቆመለት በ 1895 ሲሆን መሰረታዊው ምክንያት በጎ አድራጊነቱ ነው። በኖረበት ዘመን ለበጎ አድራጊ ድርጅቶች ከ 71 ሺህ ፓውንድ በላይ ለግሷል። ለትምህርት ቤቶች፣ ለእምነት ተቋማትና ለሆስፒታሎችም በመርዳት ስሙ ይጠቀሳል። አንዳንዶች የገንዘብ ምንጩ ቱባ ነጋዴ በመሆኑ ነው ይበሉ እንጂ ብዙዋችን የሚያስማማው ጥቁሮችን በመሸጥ ያካበተው ነው።

የዚህ ሃውልት ህጋዊነት ለበርካታ ግዜ የብርስቶል ከተማን ህዝብ አወያይቷል ፣ አጨቃጭቋል ። የሰውየው ሌጋሲ ለምሳሌነት አይበቃም በሚል የሃውልቱን መቆም የሚቃወሙት ሰሚ ሳያገኙ ቆይተዋል ። ዛሬ ከ 125 አመታት በኋላ ‹ ታላቁ › ኤድዋርድ ኮልስቶን አደባባይ ላይ በትዝብት እንደቆመ አልቀጠለም ። ዘረኝነትን በሚቃወሙ / Black Lives Matter / ሰልፈኞች እንደ በሬ በገመድ ተጠልፎ እንዲወድቅ ተደርጓል ። ከወደቀ በኋላ እንደ ሳዳም ሁሴን ሃውልት ተረግጧል ፣ ተተፍቶበታል ፣ ተረግሟል ። እንደ ጆርጅ ፍሎይድ ገዳይ አንገቱ ተረግጦ ‹ መተንፈስ አልቻልኩም › እንዲል ተጠብቋል ። በመጨረሻም ድሮ ባህር አቋርጠው አውሮፓና አሜሪካ የመጡ ጥቁሮችን ያስታውስ ዘንድ ይመስል ወደ ባህር ተጥሏል ።

ኤድዋርድ ኮልስቶን በ1689 ጥቁሮችን እያስመጣ በመሸጥ በሚታወቀው / Royal African Company / ድርጅት ውስጥ ምክትል ሃላፊ ነበር ። በዚህ ካምፓኒ ውስጥ እየሰራ 84 ሺህ 500 የሚደርሱ ጥቁሮችን በመርከብ አጓጉዟል ። ከዚህ ውስጥ 23 ከመቶ ወይም 19 ሺህ 300 ያህሉ ወደብ ሳይደርሱ መንገድ ላይ በውሃ እጥረት ፣ በተቅማጥና በንጽህና ጉደለት ሞተዋል ። ይህ ሰው ሌላም የሚታወቅበት ጉዳይ አለ ። በ 70ቹ እድሜው የፓርላማ አባልነቱን ተጠቅሞ የባሪያ ንግድ እንዲስፋፋ ፔቲሽን እስከ ማሰባሰብ ደርሷል ።

እንግሊዝ ለህብረተሰቡም ሆነ ለሀገር ጥሩ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ተብለው የሚታሰቡ / በክፉም ሆነ በደግ / ስመጥር ዜጎችን ሃውልት በማቆም በቀጣዩ ትውልድ እንዲታወሱና እንዲዘከሩ የማድረግ የረጅም ግዜ ባህል አላት ። አንዳንድ መረጃዋች እንደሚጠቁሙት በመላው ሀገሪቱ ከ828 የሚበልጡ ሃውልቶች በተለያዩ ከተሞች ቆመዋል ። እስካሁንም አንዳቸውም ላይ በተቃውሞ መልኩ የመፍረስ አደጋ አላጋጠማቸውም ። ነገር ግን ከቅርብ ግዜ ወዲህ ያልተለመዱ ትችቶችን ያስተናገዱ ሃውልቶች ታይተዋል ። ሁለተኛ አለም ጦርነትን ለማስታወስ በተደረግ ዝግጅት ላይ አንዳንድ ሃውልቶች ላይ ACAB የሚል ጽሁፎች ተነበዋል – All Cops are Bastars የሚል ትርጉሙ እንደያዙ ተገምቷል ።በቅርቡ ለንደን ውስጥ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍም የቀድሞው የእንግሊዝ ጠ/ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል ሃውልት ላይ ዘረኛ ነበር የሚል ጽሁፍ ተለጥፎበት ነበር ።

በአንድ በኩል « የባሪያ ንግድ ውርስ ነው » በሌላ በኩል « አይደለም የበጎ አድራጎነት ምልክት ነው » እየተባለ ሲያጨቃጭቅ የኖረው ሃውልት መፍረሱ የእንግሊዝን መንግስት አስቆጥቷል ። የሆም ሴክሬቴሪ ሃላፊ ፕሪቲ ፓታል ድርጊቱን አሳፋሪ በማለት ተጠርጣሪዋቹን እንፋረዳለን ብለዋል ። በነገራችን ላይ ኤድዋርድ ኮልስቶን በብርስቶል ከተማ በስሙ የኮንሰርት አዳራሽ ፣ ጎዳና እና ትምህርት ቤት ተሰይመውለታል ። ትግሉ እነዚህም እንዲፈርሱ ይዋጋል ወይስ ባፈረሰው ሃውልት ተጠያቂ እስከመሆን ይደርሳል ? እየከረረ ከመጣው የእንግሊዝ ተቃውሞ አንጻር ይህን ጥያቄ በቀላሉ መመልስም ሆነ እንደዋዛ መተውም የሚቻል አይሆንም ።

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top