Connect with us

ዱርን ያንቀጠቀጠው አንጋፋው የጨበራ ጩርጩራ ዝሆን ሞተ

ዱርን ያንቀጠቀጠውና "ሹሉሬ" አንጋፋው የጨበራ ጩርጩራ ዝሆን ሞተ

አስገራሚ

ዱርን ያንቀጠቀጠው አንጋፋው የጨበራ ጩርጩራ ዝሆን ሞተ

ዱርን ያንቀጠቀጠውና “ሹሉሬ” በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው አንጋፋው የጨበራ ጩርጩራ ዝሆን ሞተ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሙ ለቅሶ እንደሚደርሱ አልጠራጠርም፤ እሳቸው በጨበራ ጩርጩራ ውበት በፍቅር ወድቀዋልና፤
ከሄኖክ ስዩም ተጓዡ ጋዜጠኛ በድሬቲዩብ

እርግጥ ነው ዱር ውስጥ አሳዶኛል፡፡ እሱን ፍራቻ ርጃለሁ፡፡ ሩጫለሁ፡፡ ግን ጠላቴ አይደለም፡፡ እሱ የጨበራ ጩርጩራ ደን ውበትም ግርማም ነው፡፡ ቁጡው አመሉ ደኑን ባለ ግርማ አድርጎታል፡፡ ዛሬ ሩቅ ነኝ፡፡ የአዳነን ስሜት አለሁበት ኾኜ እረዳዋለሁ፡፡ የኡቴ ትካዜ ይገባኛል፡፡ የሞተው የአፍሪቃ ዝኆኖቹ ግርማ የጨበራ ጩርጩራ ግዙፍ ፍጡራን አውራ ነውና፤
ሹሉሬ በሚለው ስሙ ይታወቃል፡፡ አድብቶ የሚመጣ ድምጹ የማይሰማ ማለት ነው፡፡ አንድ ቢኾንም እንደ ሠራዊት ያስፈራል፡፡ የአረጋዊነት ዘመኑ የቁጣ ነው፡፡ ክርኑን ለማቅመስ የሚያደባ ኾኖ ኖሯል፡፡ እንግዲህ ያ ዱር ያለ ሹሉሬ ቁጣ ምን ይመስል ይኾን?

የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ቺፍ ዋርደን አዳነ ጸጋዬ የአንጋፋውን ዝኆን ሞት በፌስቡክ ገጹ ይፋ አድርጓል፡፡ ወደ አዳነ ደውዬ
“ምን ገጠመው?” አልኩት፤
“እርጅና አለኝ” እርግጥ ነው አንድ ዝኆን ያለ መንጋጋ ጥርሱ ምንም ነው፡፡ ተፈጥሮ ለዝኆን መንጋጋው ያለውን ፋይዳ አውቃ ስድስት ግዜ የመቀየርን እድል ሰጥታዋለች፡፡ ስድስተኛው መንጋጋ ከ39 እስከ 65 ዓመት እድሜው ድረስ የሚያገለግል ነው፡፡ ከዚያ ይወልቃል፡፡ ከወለቀ እንደልብ መመገብ የለም፡፡ እርጅናና መንጋጋ ማጣት አንድ ላይ ከተፍ ይላሉ ሹለሬ እንዲህ ያለ እጣ ገጠመው፡፡ ሞቱን ሰማሁ፡፡

ሹሉሬ የኬኒያ ዝኆን ቢኾን ኖሮ ዛሬ ሰበር ዜና ነበር፡፡ የታንዛኒያ ቢኾን መገናኛ ብዙኃኑ ሌላ ርዕስ ባልነበራቸው፡፡ እኛ የእነሱ ተቀባይ ነን፡፡ ከአመት በፊት ነጩ አውራሪስ ሲሞት ምዕራባውያን ሲቀባበሉት የእኛ ሚዲያዎች ገልብጠው ነግረውናል፡፡ ያም ኾኖ ሹለሬ ሚዲያ ሞኒተሪንግ ሰርቶ የሚቆጭ ዘመድ የለውም፡፡ እሱ የዱር ንጉሥ ነው፡፡ በክብር ኖሮ አልፏል፡፡

ዘመኑ አልጋ ባልጋ እንደማይኾን ገምቱ፤ ሲወለድ የኖረበት ምድር በብሔራዊ ፓርክነት አልተከለለም፤ ረዥም ዘመኑን ጥርሱን ነክሶ ጥርሱን ፍለጋ ከሚያደባ ሽፍታ ጋር የተናነቀ ዝኆን ነው፡፡ በማረፊያው ሞተ አልለው ነገር እንዲህ ያለው የሰው ወግ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሙ ለቅሶ እንደሚደርሱ አልጠራጠርም፤ እሳቸው በጨበራ ጩርጩራ ውበት በፍቅር ወድቀዋልና፤

ሹሉሬ ከነክብሩ ሞተ፡፡ ጥርሱን ሳያስነካ፤ ዱሩን ሳያስደፍር፡፡ እንደተፈራ ኖሮ አለፈ፡፡ ጨበራ ጩርጩራን እንዳስከበረ፡፡ ከፍል ውሃ እስከ ሾሺማ ዘንጦበት፤ ከጨበራ እስከ ጩርጩራ ተንጎማሎበት፡፡ ለሀገሬ ዝኆኖች የሹሉሬን ተመኘሁ፡፡ ከህገ ወጥ ክፋት ተጠብቀው፤ ከአዳኝ ጭካኔ ድነው እንዲህ የተፈጥሮን ሞት እንዲሞቱ፤

Click to comment

More in አስገራሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top