Connect with us

የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ አመራሮች የአቋም መግለጫ

የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ አመራሮች የአቋም መግለጫ

ፓለቲካ

የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ አመራሮች የአቋም መግለጫ

የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ አመራሮች በዛሬው እለት ሲካሄድ ውይይት ካካሄዱ በኃላ ባለ 5 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እነሆ:-

እኛ የትግራይ ተወላጅ የሆንን የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ አመራሮች፣ ባለፉት ቀናት ስለአጠቃላይ የአዲስ አበባ የፓርቲያችን መዋቅር እንዲሁም ኮቪድ 19፣ የምርጫ መራዘምና የህግ አማራጮች በሚል ርእስ ስናደርግ የነበረውን ውይይት በማጠናቀቅ የሚከተለውን የጋራ አቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡

ፓርቲያችን ብልፅግና የመላው ኢትዮጵያውያን ፓርቲ ሆኖ፣ ሁሉንም ህዝቦች በፍትሃዊነትና በእኩልነት የሚያሳትፍ አደረጃጀት ፈጥሮ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

እኛ በተለያየ የአመራር ቦታ ያለን የቀድሞ የሕወሓት አባላት፣ በብልፅግና ፓርቲ ታቅፈን ለመንቀሳቀስ እና የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ እውን ለማድረግ ካለን ፅኑ ፍላጎት በገዛ ፍቃዳችን ስንቀላቀል፣ ፓርቲያችን መላውን ህዝባችንን በተለይም ባለፉት አመታት ምንም ሳይጠቀም እንደተጠቀመ ተቆጥሮ በስሙ ሲነገድበት የነበረውን የትግራይ ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችልና የህዝቡንም ቀጣይ እጣ ፋንታ ብሩህ ማድረግ እንደሚችል ካለን ጠንካራ ልባዊ እምነት የተነሳ ነው፡፡

የትግራይ ህዝብ ለመብቱ እና ለነፃነቱ ውድ ዋጋ የከፈለ፣ ከኢትዮጵያዊ ወንድም እና እህቶቹ ጋር በጋራ መኖር የሚፈልግ ታላቅ ህዝብ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ትግሉ በጥቂት የራሳቸውን የግል ስልጣን ለማደላደል በሚፈልጉ ቡድኖች ታጥሮ፣ የታገለለትን መብት በሚገባ ሳይጎናፀፍ ዛሬም ታፍኖ እኔ አውቅልሃለው በሚል መርህ ከሌሎች ወንድሞቹ እና እህቶቹ ጋር የመገለል ስሜት እንዲያድርበትና በጥርጣሬ እንዲኖር እየተደረገ ይገኛል፡፡

የትግራይ ህዝብ ከታገለላቸው አላማዎች አንዱና ዋነኛው ህብረ-ብሄራዊ ፌደራሊዝም ስርዓት በሃገራችን እውን እንዲሆን ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ጥቂት እኩይ አላማ ያላቸው ቡድኖች “ብልፅግና አሃዳዊ ስርዓት ነው”! የሚል የተዛባ ፕሮፖጋንዳ እየነዙ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ወገኖቻችንን እያሳሳተ ይገኛል፡፡ ሆኖም ብልፅግና ለእውነተኛ ህብረ-ብሄራዊ አንድነት በመከባበር እና በመተማመን ላይ የተመሰረተ የህዝቦች ግንንነት ለማጠንከር የሚሰራ ፓርቲ እንጂ በፌደራሊዝም ስም የጥቂቶችን ፍላጎት ለማራመድ የማይሰራ ፓርቲ ነው፡፡

ህወሓት አሁንም የትግራይ ህዝብ የለውጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ የቀድሞ የማታለል ሴራውን እየተገበረበት ይገኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ህብረተሰብ እና መንግስት በሃገራችን የተከሰተውና ቁጥሩ እየጨመረ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ለመከላከል ከፍተኛ ርብርብ በሚደረግበት “ምርጫ ካልተደረገ የሚል ግትር አቋሙም ለህዝቡ ደህንነት ደንታ እንደሌለው በግልፅ አሳይቷል፡፡

ምርጫ የህዝብ ዲሞክራሲያዊ መብት መሆኑን እናምናለን፡፡ ነገር ግን የህዝብን ደህንነት ቅድሚያ መስጠት ስለሚገባ፣ በፓርቲያችንና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ መራዘም የተያዘውን አቋም ተገቢና ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን እናምናለን፡፡ ቀጣይ እርምጃዎችም ህገመንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ባከበረ መልኩ መካሄድ እንደሚኖርበትም የማያወላላል አቋም አለን፡፡

በነበረን የውይይትና የምክክር መድረክም የሚከተለውን ባለ አምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡

1ኛ መንግስት የምርጨውን መራዘም አስመልክቶ እየሄደበት ያለው ህጋዊና ህገመንግስታዊ የመፍትሄ አቅጣጫ ፤የህዝቡን ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጥ፤ አሁን የተጋረጡብንን አደጋዎች እንደ ሃገር ትኩረታችን ሳይዘነጋ እንድንከላከል የሚያግዝ በመሆኑ፣ የምንደግፈውና ለተግባራዊነቱም ከፓርቲያችን እና ህዝባችን ጎን በመሆን የምንታገል መሆኑን እንገልፃለን፡፡

2ኛ በክልል ደረጃ ምርጫ ማካሄድ የማይቻልና ኢ-ህገመንግስታዊ ነው፡፡ ስለሆነም ህወሓት በክልል ደረጃ ምርጫ አካሂዳለው ብሎ መነሳቱ ፍፁም ህገወጥና የሃገሪቱን ህጎች መናድ በመሆኑ በአስቸኳይ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ እናሳስባለን፡፡

3ኛ ብልፅግና የአዲሱ ትውልድ ፓርቲ ነው፡፡ ይህ ፓርቲ የትግራይን ህዝብ ከሌሎች ወንድምና እህት ህዝቦች በጋራ የልማት እና የእውነተኛ ዲሞክራሲ ተጠቃሚ ለማድረግ በከፍተኛ ሁኔታ እየሰራ ይገኛል፡፡ ነገር ግን በተለመደ የማጠልሸት ተግባራቸው ብልፅግና የትግራይን ህዝብ እንደሚጠላ በማስመሰል የራስን ስልጣን ለማቆየት የሚያደርጉትን ጥረት በመቃወም የብልፅግና ጉዞው ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

4ኛ የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ወንድም እህቶቹ ጋር በጋራ መኖር የሚያውቅ፣ ለኢትዮጵያዊ አነድነት ብዙ ዋጋ የከፈለ ነው፡፡ በመሆኑም ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በሰላምና በመከባበር በወንድማዊ ስሜት ሆነን፣ አብሮነታችንንና አገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴያችንን እንድናፋጥን እየጠየቅን፣ ይህን ከፋፋይ ተግባር በጋራ ሆነን እንድንታገለው ጥሪ እናቀርባለን፡፡

5ኛ በመጨረሻም፣ የህዳሴ ግድባችን ለሃገራችን የብልፅግና ጉዞ ወሳኝና እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ እኛ የትግራይ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች በግድቡ ላይ የሚደረግ ማንኛውም ውጫዊ ጫናና ጣልቃ ገብነት በፍፁም የማንቀበለውና ፤ለግድቡ እውን መሆን አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናችንን እንገልፃለን፡፡

ግንቦት 2012
አዲስ አበባ

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top